ፖሊስ ሆን ብለህ በአደባባይ 'ፈስተሃል' ያለውን ግለሰብ 550 ዶላር ቀጣ

መናፈሻ ቦታ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ከታች አየር ማስወጣት ማኅበራዊ ነውር እንደሆነ ይታሰብ ይሆናል እንጂ በሕግ ያስቀጣል ተብሎ አይጠበቅም።

በኦስትሪያ ግን ፖሊስ ነገሩ ላይ አምርሮ "አላግባብ ፈስተሃል" ያለውን ግለሰብ 564 ዶላር መቀጮ ጥሎበታል።

መቀጮው ይህን ያህል ተመን የተደረገበት ባስከተለው መጥፎ ጠረን ወይም ርዝማኔ አልያም የድምጽ ምጣኔ ይሁን የታወቀ ነገር የለም።

ሰውየው ድርጊቱን የፈጸመው ፖሊሶች ፊት መሆኑ ቅጣቱን ሳያከብድበት አልቀረም።

የቪይና ፖሊስ ግን ሰውየው የተቀጣው "ጋዝ በታች በኩል በማስወጣቱ" ብቻ አይደለም ሲል በትዊተር ሰሌዳው ተከላክሏል።

"መቼስ በታች በኩል ለምን ተነፈስክ ብለን ዜጋችንን አንቀጣም. . . " ይላል የፖሊስ የትዊተር መግለጫ።

ፖሊስ ሰውየው ላይ ያቀረበው ክስ ግልባጭ በማኅበራዊ ድር አምባው ከታተመ በኋላ ኦስትራዊያን ነገሩን ማኅበራዊ ቧልት አድርገውት ቆይተዋል።

የክሱ ርዕስ "የሥነ ምግባር ጥሰት እና ሥርዓት ማጣት" የሚል ሲሆን ድርጊቱ የተፈጸመው በሰኔ 5 እንደሆነ ይገልጻል። ፖሊስ ግን ተከሳሹ ድምጽ ያለው ጋዝ ከማስወጣቱም በላይ ለፖሊስ ተባባሪ አልነበረም ብሏል።

ተከሳሹ ድርጊቱን የፈጸመው ፖሊስ በቁጥጥር ሊያውለው ወደ ነበረበት የሕዝብ መናፈሻ በመጣ ጊዜ ከተቀመጠበት የሕዝብ መናፈሻ አግዳሚ ወንበር ተነስቶ ነገርየዋን ሆን ብሎ፣ አስቦና አቅዶ፣ ድምጽ እንዲኖረው በማድረግ "ከባድ ጋዝ ማስወጣቱ" ተብራርቷል።

ተከሳሹ የተጣለበትን ቅጣት ይክፈል አይክፈል፣ አልያም ይግባኝ ስለማለቱ የተባለ ነገር የለም።