እውን ኮሮናቫይረስ ከቻይና የምርምር ቤተ ሙከራ ያመለጠ ይሆን?

የዉሀን ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የዉሀን ከተማ

የአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት በቻይና የአሜሪካ ኤምባሲ ውስጥ የነበሩ ባለስልጣናት በዉሃን ከተማ በሚገኝ የቫይረስ ላብራቶሪ የደህንነት ስጋት ነበራቸው ብሏል።

የደህንነት ጥራት ችግር አለበት የተባለው የቫይረስ ላብራቶሪው ኮሮና ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘባት ዉሃን ከተማ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ደግሞ ነገሮችን አጠራጣሪ አድርጎታል።

ይህ ሀሳብ ግን አሁን ስለኮሮናቫይረስ ያለን እውቀት ላይ ምን ይጨምርናል?

ጋዜጣው እንደዘገበው በአውሮፓውያኑ 2018 ጥቂት የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በዉሃን የሚገኘውን ላብራቶሪ ለመጎብኘት ተልከው ነበር። የዲፕሎማቲክ ልኡካን ቡድኑም በቤተ ሙከራው የደህንነት ችግር እንዳለ ገልጸው ነበር።

በዉሃን የሚገኘው የቫይረስ ምርምር ላብራቶሪም አቅሙ ደካማ እንደሆነ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ይላል ጋዜጣው ከሌሊት ወፍ የሚመጣው የኮሮናቫይረስ ላይ እየተደረገ ያለው ምርምር እንደ ሳርስ አይነት ወረርሽኝ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸው ነበር።

የአሜሪካ መንግስትም የኮሮናቫይረስ በዚህ ላብራቶሪ ወይም በዉሃን የሚገኝ ሌላ ማዕከል መነሻው ሊሆን እንደሚችል ውይይት አድርጎ ነበር ብሏል ጋዜጣው።

ምንም እንኳን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በዉሃን በሚገኝ የምግብ ገበያ ውስጥ ባለፈው ዓመት ቢከሰትም በአሁኑ ሰዓት ዓለምን እያስጨነቀ ያለው ቫይረስ በስህተት ከላብራቶሪ ስለማምለጡ የተገኘ ማረጋገጫ የለም።

ዋሽንግተን ፖስት አገኘሁት ያለው መረጃ ለዚህ ሀሳብ ማረጋገጫ የሚሰጥ አይነት አይደለም። ነገር ግን አንድ ቫይረስም ሆነ ማንኛውም ጎጂ ነገር ከላብራቶሪዎች በተለያየ መንገድ ሊያመልጥ ይችላል።

በአውሮፓውያኑ 2014 በአንድ የምርምር ላብራቶሪ ውስጥ ተረስተው የቀሩ የፈንጣጣ ናሙናዎች ተገኝተው ነበር። በ2015 ደግሞ የአሜሪካ መከላከያ የሞቱ የአንትራክስ ናሙናዎችን መላክ ሲገባው በስህተት በህይወት ያለ የአንትራክስ ናሙና ልኮ ነበር።

እነዚህ የስህተት አጋጣሚዎች በተገቢው መንገድ በቁጥጥር ስር ባይውሉ ኖሮ ሌላ ወረርሽኝ መነሳቱ አይቀርም ነበር።

አንድ በወርሃ ጥር ላይ በበይነ መረብ አማካኝነት በተለቀቀ ጽሁፍ መሰረት የኮሮናቫይረስ ሆን ተብሎ ለባዮሎጂካል የጦር መሳሪያነት የተሰራ እንደሆነ ያትታል።

ተመራማሪዎች ይህንን ሃሳብ አምርረው ሲከራከሩት ነበር። የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን ቫይረሱ መነሻው ከእንስሳት በተለይም ከሌሊት ወፎች መሆኑን ጥናቶቼ አሳይተውኛል ብሏል።

ነገር ግን ቫይረሶች እንዴት እንደሚያድጉ ለማወቅ ሌላ ቫይረስ በላብራቶሪ ውስጥ አይፈጠርም ማለት አይደለም። ምክንያቱም ተመራማሪዎች ከከፍተኛ ጥንቃቄ ጋር ቢሆንም የተለያዩ ቫይረሶችን ላብራቶሪ ውስጥ ይፈጥራሉ።

ይህም ቫይረሶች ወደፊት ምን አይነት ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማወቅና ቀድሞ ለመከላከል ይረዳል።

አንድ አሜሪካ ውስጥ በተሰራ ጥናት መሰረት የኮሮናቫይረስ ላብራቶሪ ውስጥ ስለመፈብረኩ ምንም ማስረጃ ላገኝለት አልቻልኩም ብሏል።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ደግሞ ይህንን ሀሳብ እንደ ቀላል የምንመለከተው አይደለም፤ ማጣራት እናደርግበታለን ብለዋል።

ኮሮና