በዚምባብዌ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ተደርምሶ ሰዎችን ገደለ

በዚምባብዌ የደረሰ የማዕድን ቦታ አደጋ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በዚምባብዌ የደረሰ የማዕድን ቦታ አደጋ

በዚምባብዌ የወርቅ ማዕድን ሲያወጡ የነበሩ ሰዎች የመደርመስ አደጋ ደርሶባቸው ሕይወታቸውን አጡ።

የአገሪቱ ሄራልድ ጋዜጣ እንዳስነበበው ከሆነ በደረሰው የመሬት መደርመስ ምክንያት ሁለት ሰዎች ወዲያውኑ ሕይወታቸው አልፏል። 20 የሚሆኑት ደግሞ በተደረመሰው አፈር ተቀብረው እስካሁን መውጣት አልቻሉም።

ማዕድን አውጪዎቹ ከመዲናዋ ሐረሬ በስተምዕራብ በኩል 120 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቃ በምትገኘው ክዌክዌ ከተማ ነው ማዕድን ሲያወጡ የነበረው።

የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣንን ውሳኔን ተከትሎ የማዕድን ማውጫ ስፍራው በ2007 እ.አ.አ እንዲዘጋ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን ሰዎች በሕገ ወጥ መልኩ ወደቦታው በማምራት በምሽት ማዕድን ሲያወጡ ቆይተዋል።

"ከምሽቱ 4 ሰዓት አካባቢ እየሰራን እያለ በሌላኛው የማዕድን ማውጫ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የጩኸት ድምጽ ሰማን፤ ከዚያ ወጥተን ስንመለከት የተደረመሰ ድንጋይ ጓደኞቻችን ላይ እየተጫነ መሆኑን አየን" በማለት በቦታው የነበረ አንድ የማዕድን ሠራተኛ ምስክርነቱን ሰጥቷል።

"አንዱን ጓደኛችንን ተረባርበን በሕይወት ማትረፍ ብንችልም ሁለቱ ግን ወዲያው ነበር የሞቱት። ከተቀበሩበት ለማውጣት ብንሞክርም የተጫናቸው አለት ከባድ በመሆኑ እርሱን ማንሳት አልቻልንም። ከሟቾቹና በሕይወት ከተረፉት ተጎጂዎች በተጨማሪ 20 የማዕድን ሠራተኞች ከመሬት በታች መውጫ አጥተዋል" ብሏል።

ከአደጋው የተረፉት ተጎጂዎች ወደ አካባቢው ሆስፒታል ተወስደው ህክምና እየተደረገላቸው ነው።

ባለፈው ዓመት 22 የማዕድን ሠራተኞች በተመሳሳይ አደጋ በዚምባብዌ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የአገሪቱ መንግሥትም በአሁኑ ወቅት በሕገ ወጥ ማዕድን ማውጣት ሥራ ተሰማርተዋል ያላቸውን ግለሰቦች በብዛት እያፈሰ በማሰር ላይ ይገኛል።