በህንድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ የ5 ዓመት ልጅ ተደፈረች

ህንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በህንድ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የአምስት ዓመት ልጅ መደፈሯን ተከትሎ በወንጀሉ የተጠረጠረ የ25 ዓመት ወጣት በቁጥጥር ሥር ዋለ።

ግለሰቡ በወንጀሉ ተጠርጥሮ የታሰረው የህጻኗ ወላጆች ለፖሊስ ጥቆማ ከሰጡ በኋላ ነው።

ሃኪሞች ታዳጊዋ ቅዳሜ ጠዋት ላይ መደፈሯን አረጋግጠው፤ የጤናዋ ሁኔታ ለክፉ የሚሰጥ ደረጃ ላይ አይደለም ብለዋል።

የታዳጊዋ ወላጆች የኤምባሲው ሠራተኛ መሆናቸውና በኤምባሲው ቅጥር ግቢ ውስጥ እንደሚኖሩ ተነግሯል።

የህንድ መገናኛ ብዙሃን ወላጅ አባቷ የኤምባሲው የጽዳት ሰራተኛ መሆናቸውን እየዘገቡ ይገኛሉ።

በወንጀሉ የጠረጠረው ግለሰብም ወላጆች የኤምባሲው ሰራተኛ መሆናቸውን እና ከወላጆቹ ጋር በቅጥር ግቢው ውስጥ እንደሚኖር ተነግሯል።

በብዙ ስልጡን ጠባቂዎች የሚጠበቀው የኤምባሲ ቅጥር ግቢ ውስጥ እንዴት ይህን መሰል ወንጀል ይፈጸማል በማለት በርካቶች እየጠየቁ ይገኛሉ።

እንደመርማሪዎች ከሆነ የተጎጂና የተጠርጣሪው ወላጆች የሚተዋወቁ ሲሆን፤ ታዳጊዋ ስትጫወት ከተመለከታት በኋላ አባብሎ ወላጆቹ በሌሉበት ወቅት በታዳጊዋ ላይ ጥቃቱን ፈጽሟል።

ታዳጊዋ ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ ወደ መኖሪያ ቤቷ ተመልሳ ያጋጠማትን ለእናቷ መናገሯን መርማሪዎቹ ተናግረዋል።

የህንድ መንግሥት ከሁለት ዓመታት በፊት ታዳጊዎችን አስገድደው የሚደፍሩ ወንጀለኞች የሞት ቅጣት እንዲበየንባቸው ወስኗል።

በህንድ ከሚፈጸሙ አራት የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች መካከል ቢያንስ አንዱ የሚፈጸመው እድሜያቸው ከ18 ዓመታት በታች በሆኑ ታዳጊዎች ላይ ነው።