በባንግላዴሽ ባለቤቱን አስገድዶ ፀጉሯን የላጨው በቁጥጥር ስር ዋለ

የሕንድ ሂንዱ እምነት ተከታዮች ሀይማኖታዊ ስርዓት ለመፈፀም ሲላጩ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በባንግላዴሽ የቀረበለት ቁርስ ላይ ፀጉር በማግኘቱ ምክንያት የባለቤቱን ፀጉር በግድ የላጨው በቁጥጥር ስር ዋለ።

የ35 ዓመቱ ባብሉ ሞንዳል በቁጥጥር ስር የዋለው የሚኖርበት መንደር ነዋሪዎች ሚስቱ ላይ የፈፀመውን ለፖሊስ ካመለከቱ በኋላ ነው።

በባንግላዴሽ በወግ አጥባቂ ሙስሊሞች ዘንድ የሚደርሱ ጾታዊ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን የመብት ተሟጋቾች ይናገራሉ።

" ቁርስ ላይ ባለቤቱ አብስላ ባቀረበችለት ሩዝና ወተት ላይ ፀጉር በማግኘቱ ነው ፀጉሯን ሙልጭ አድርጎ የላጨው" ብለዋል የአካባቢው ፖሊስ ኃላፊ ሻህሪር ካሃን ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል።

አክለውም " ምግቡ ላይ ፀጉር በማግኘቱ በጣም በመቆጣት ምላጭ አንስቶ በግድ ፀጉሯን ሙልጭ አድርጎ ላጭቷታል" ብለዋል።

የፖሊስ አዛዡ እንዳሉት ከሆነ የ35 ዓመቱ ባብሉ ሞንዳል የ23 ዓመቷ ሚስቱ ላይ "ሆን ብሎ ጉዳት በማድረስ" መከሰሱን የተናገሩ ሲሆን ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ እስከ 14 ዓመት በሚደርስ እስር ሊቀጣ ይችላል ተብሏል።

በአካባቢው ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል የሚሰራ ቡድን እንዳለው ከሆነ በግማሽ ዓመቱ ብቻ በየቀኑ ቢያንስ ሦስት ሴቶች ተደፍረዋል።

ድርጅቱ አክሎም ከታህሳስ እስከ ሐምሌ ባለው ጊዜ ውስጥ 630 ሴቶች ሲደፈሩ፣ 37 ተገድለዋል፣ ሰባቱ ደግሞ ከደረሰባቸው ጥቃት በኋላ ራሳቸውን አጥፍተዋል።

105 የመድፈር ሙከራዎችም በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ መፈፀሙን ተናግረዋል።

በሚያዚያ ወር ላይ የ19 ዓመቷ ተማሪ መምህሯ ትንኮሳ እንዳደረሰባት ከተናገረች በኋላ በእሳት በመቃጠሏ ምክንያት ትልቅ ተቃውሞ ሠልፍ ተካሂዶ ነበር።