በህንድ በቡድን ተደፍራ የተገደለችው የ27 ዓመቷ ዶክተር ጉዳይ ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ

በህንድ በደቦ ተደፍራ የተገደለችው ዶክተር ከፍተኛ ቁጣን ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በህንድ ሃይደራባድ በምትባል ግዛት አንዲት የ27 ዓመት የእንስሳት ዶክተር ተደፍራ መገደሏ ከተሰማ በኋላ ከፍተኛ ቁጣ ተቀስቅሷል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በከተማዋ የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ አካባቢ ሰልፍ በመውጣት ግለሰቦቹ የሞት ቅጣት ይገባቸዋል በሚል ተቃውሟቸውን እያሰሙ ነው።

የሟች ቤተሰቦች ልጃቸው ጠፍታ በነበረበት ወቅት ፖሊስ ኃላፊነቱን በሚገባ አልተወጣም በማለታቸውም እስካሁን ሶስት የፖሊስ አባላት ከስራ ታግደዋል።

የሟች ቤተሰቦችም ሊጎበኟቸው የሚመጡ ፖለቲከኞችንም ሆነ የፖሊስ ኃላፊዎች ገዳዮችዋን ለፍርድ እስካላቀረቡ ድረስ ወደ ቤታቸው ዝር ማለት እንደማይችሉ አሳውቀዋል።

የግለሰቧ የተቃጠለና የጠቆረ አስከሬን የተገኘው ባለፈው ሃሙስ ዕለት ነው።

ከመሞቷም በፊት በቡድን እንደተደፈረችም ፖሊስ ይፋ ያደረገ ሲሆን ከግድያዋ ጋር ተያይዞ አራት ወንዶች በቁጥጥር ስር ውለዋል።

የሁለቱ ወንዶች እናቶችም ጥፋተኛ ከሆኑ እንዲቀጡ መንግሥትን በመማፀን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

"ማንኛውንም ቅጣት ይቀጡ፤ እኔም ሴት ልጅ አለችኝ" በማለት አንደኛዋ እናት 'ለትረስት ኦፍ ኢንዲያ ሚዲያ' ተናግረዋል።

የግለሰቧ ሞት ብሔራዊ ቁጣንም ቀስቅሷል፤ ብዙዎችም ጥቃት አድራሾቹ በሞት እንዲቀጡ እየጠየቁ ነው። በአብዛኛው የሃገሪገቷ ክፍል ከተቃውሞ ሰልፍ በተጨማሪ የሻማ ማብራት ስነስርዓትም ተካሂዷል።

ተቃውሞ በህንድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በሃይደራባድ ግዛትም በሟቿ መኖሪያ ቤት በር ላይ ማህበረሰቡ "ፖሊስ፣ ሚዲያ፣ የውጭ ሰውም አንፈልግም፤ ሃዘን አያስፈልገንም፤ ፍትህ ብቻ ነው የምንሻው" የሚሉ መፈክሮችንም ይዘው ታይተዋል።

የሻማ ማብራት ስነስርዓት በደልሂ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታዋቂ ፖለቲከኞችም ሴቶች በየቀኑ የሚያልፉበትን ጥቃት ልንቀበለው አይገባም በሚል መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ እስካሁን ዝምታን መርጠዋል።

ተቃውሞ በህንድ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ሟቿ ረቡዕ ዕለት የዶክተር ቀጠሮ ስለነበራት ከቤቷ የወጣችው አስራ ሁለት ሰዓት ላይ ነበር። ትንሽ ቆይታም ለቤተሰቦቿ ደውላ የሞተር ሳይክሏ ጎማ መተንፈሱንና አንድ ጭነት መኪና ሊረዳት መሆኑን ነግራቸው ነበር።

ያም የስልክ ልውውጥ የመጨረሻ ነበር፤ ከዚያ በኋላ ድምጿም አልተሰማም። አስከሬኗም በድልድይ ውስጥ ተጥሎ አንድ ወተት በሚሸጥ ሰው አማካኝነት ሐሙስ ጥዋት ተገኘ።

ምንም እንኳን በህንድ ህግ መሰረት በመደፈር ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ማንነት እንዳይገለፅ የሚያዝ ቢሆንም አርብ እለት የግለሰቧን ስም በትዊተር ሰዎች ሲቀባበሉት ነበር።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ፍትህን በመሻት ቁጣቸውን በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።

በመዲናዋ ደልሂ ከሰባት አመታት በፊት በአውቶብስ ውስጥ በቡድን ተደፍራ የተገደለችው አንዲት ተማሪን ተከትሎ መንግሥት ትኩረት ቢያደርግም አሁንም ቢሆን መደፈርና ግድያ በከፍተኛ ቁጥር እያሻቀበ እንደሆነ ሪፖርቶች ያሳያሉ።

ከሁለት አመታት በፊት ፖሊስ ባወጣው መረጃ 33 ሺ 658 የመደፈር ኬዞች የተመዘገቡ ሲሆን፤ ይህም በየቀኑ የምትደፈረውን ሴት ቁጥር ወደ 92 ያደርሰዋል።