ኢራን የአሜሪካ ሰላይ ነው ባለችው ግለሰብ ላይ ሞት ፈረደች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የኢራን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሲአይኤ ይሰልል ነበር ተብሎ የተወነጀለውን ግለሰብ ሞት ፈረደበት።
የሞት ፍርድ የተፈረደበት አሚር ራሂምፖር የኢራንን የኒውክሊየር ፕሮግራም መረጃ ለሲአይኤ በማቀበል ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ተቀብሏል በማለት የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ ጎላምሆሴይን እስማኤል ተናግረዋል።
ሰላዮች ናቸው ተብለው የተወነጀሉ ሁለት አሜሪካውያንም በመሰለል ወንጀል አስር ዓመት እንዲሁም በተጨማሪ ብሔራዊ ጥቅምን በመተላለፍና ደህንነትን አደጋ ላይ በመጣል ሌላ አምስት ዓመት ተፈርዶባቸዋል።
ቃል አቀባዩ የሁለቱን ግለሰቦች ማንነት ከመግለፅ ተቆጥበዋል፤ በዚህ ጉዳይ ላይም ከአሜሪካም ሆነ ከሲአይኤ የተሰማ ነገር የለም።
ነገር ግን በሐምሌ ወር ኢራን ለሲአይኤ ሲሰልሉ ነበር ያለቻቸውን አስራ ሰባት ሰዎች የሞትና ሌሎችም ቅጣቶች ወስኘባቸዋለሁ ብትልም አሜሪካ ጥርጣሬ አላት።
"መዋሸት የአያቶላህ ባህርይ ነው" በማለት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔዮ የኢራኑን ታላቁን መሪ አያቶላህ አሊ ኻሚኒን ወርፈዋቸዋል።
ከወር በፊት ለኢራን መከላከያ ሚኒስትር ተቀጥሮ ይሰራ የነበረው ጃላል ሃጂዛቫር በስለላ ወንጀል ጥፋተኛ ተብሎ በሞት ፍርድ ተቀጥቷል።
ጃላል ከሲአይኤ ከፍተኛ ገንዘብ ተቀብያለሁ ሲል ተናዞ ነበር።
ኢራን እንደ ጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር በ2016 የኒውክሊየር ሳይንቲስቷን ሻሃራም አሚሪን ለአሜሪካ ይሰልላል በሚል ገድላዋለች።
ሳይንቲስቱ ከኢራን አምልጦ ወደ አሜሪካ በ2009 ሄዶ የነበረ ሲሆን፤ በዓመቱ ታፍኜ ያለፈቃዴ ነው የተወሰድኩት በማለት ወደ ኢራን ተመልሶ የነበረ ቢሆንም ከሞት አላደነውም።
የሳይንቲስቱ ሞት በኢራንና በዋሽንግተን መካከል ያለውን የተበላሸ ግንኙነት የበለጠ አካሮታል።
ከወራት በፊት በፕሬዝደንት ትራምፕ ትዕዛዝ በሰው አልባ አውሮፕላን ተተኩሰው የተገደሉት የጀነራል ቃሲም ሱለይማኒ ጉዳይ ሁለቱን አገራት የበለጠ አይንና ናጫ አድርጓቸዋል።
በምላሹ ኢራን የአሜሪካ ይዞታ ነው በሚባል የጦር ሰፈር ላይ በባሌስታይክ ሚሳይል ጥቃት መፈጸሟ ይታወሳል።












