ያለፈቃዳችን የእርግዝና መከላከያ እንድንጠቀም ተደርገናል ያሉ የግሪንላንድ ሴቶች ካሳ ጠየቁ

ግሪንላንድ

በግሪንላንድ እንደ አውሮፓውያኑ በ1960ዎቹ የእርግዝና መከላከያ ያለፈቃዳችን እንድንጠቀም ተደርገናል ያሉ 67 ሴቶች የዴንማርክ መንግሥት ካሳ እንዲከፍላቸው ጠየቁ።

በግሪንላንድ ነባር ሕዝቦች መካከል ያለውን የውልደት ምጣኔ ለመገደብ በታቀደው መርሃ ግብር በአስራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊዎችን ጨምሮ ቢያንስ 4 ሺህ 500 ሴቶች የእርግዝና መከላከያ እንዲጠቀሙ ተደርገዋል።

ይህንንም ተከትሎም ሴቶቹ ያቀረቡትን ጥያቄ የሚመረምር ኮሚሽን የተቋቋመ ሲሆን ምርመራውም እንደ አውሮፓውያኑ 2025 ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።

የተወሰኑት በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙት እነዚህ ሴቶች ግን ካሳው አሁን እንዲከፈላቸው ይፈልጋሉ።

ሴቶቹ ለእያንዳንዳቸው 42 ሺህ 150 ዶላር ካሳ እንዲከፈላቸው ነው ጥያቄ ያቀረቡት።

በከፊል ራሷን የምታስተዳድረው የዴንማርክ ግዛት የሆነችው ግሪንላንድ እስከ 1953 ድረስ የዴንማርክ ቅኝ ግዛት ነበረች።

በወቅቱ በግዛቷ የተፈፀመው ዘመቻ የተጋለጠው ባለፈው ዓመት በዴንማርክ መገናኛ ብዙኃን ዲአር የፖድካስት ፕሮግራም ነው።

በብሔራዊ የመረጃ ቋት የተገኘው ማስረጃ እንደሚያሳየውም በ1966 እና 1970 ባሉት ዓመታት ብቻ አይዩዲ የተባለው የእርግዝና መከላከያ መሣሪያ ከሴቶቹ እውቅና ውጭ በማህጸናቸው እንዲቀመጥ ተደርጓል።

የተወሰኑት ሴቶች ከ13 ዓመት ዕድሜ የሚያንሱ ናቸው።

የግሪንላንድ መንግሥት በ1969 መጨረሻ ላይ በግዛቷ የሚገኙ 35 በመቶ የሚሆኑ መውለድ የሚችሉ ሴቶች በማህጸናቸው የአይዩዲ የእርግዝና መከላከያ እንደነበራቸው ዲአር ዘግቧል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጉዳዩ ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ በግሪንላንድ እና ዴንማርክ የተቋቋመው ኮሚሽን ግኝቱን እስከ ግንቦት 2025 ድረስ ባሉት ጊዜያት ማቅረብ አይችልም።

ሆኖም የካሳ ጥያቄውን እቅስቃሴ የጀመረችው የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ናጃ “ የምርመራውን ውጤት መጠበቅ አንፈልግም” ብላለች።

“እያረጀን ነው። እኛ በ1960ዎቹ አይዩዲ በማህጸናችን የተቀመጠብን ሴቶች የተወለድነው በ1940ዎቹ ነው። አሁን ወደ 80 ዓመት ዕድሜ እየተጠጋን ነው። በመሆኑም ጥያቄያችን አሁኑኑ መልስ እንዲያገኝ እንፈልጋለን” ብላለች።

ሊይበርዝ ጨምራም በአንዳንድ ሁኔታዎች ለታዳጊ ሴቶች የእርግዝና መከላከያ መሣሪያው ትልቅ በመሆናቸው መካንነትን ጨምሮ ውስብስብ የሆነ የጤና ችግር አስከትሎባቸዋል። ሌሎች ሴቶች ደግሞ በቅርቡ በማህጸን ሐኪም እስኪነገራቸው ድረስ የእርግዝና መከላከያው በማህጸናቸው እንዳለም እንደማያውቁ ተናግራለች።

በወቅቱ የነበረው የዴንማርክ መንግሥት ገንዘብና ሐብት ለመቆጠብ ሲል የግሪንላንድን ሕዝብ መጠን ለመቆጣጠር ፈልጓል ስትልም ከሳለች።

“ መንግሥት የሰብዓዊ መብታችንን በመጣስ እና ለከፋ የጤና ችግር እንድንጋለጥ በማድረግ ሕግ መጣሱ መቶ በመቶ ግልጽ ነው” ብላለች ሊይበርዝ።

የሴቶቹ ጠበቃ ሆኑት ማደስ ፕራሚንግ ሴቶቹን በመወክል ቅሬታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍርደሪክሰን ጽ/ቤት አቅርበዋል።

ሊይበርዝ መንግሥት የኮሚሽኑን ውጤት በመጠባበቅ ጥያቄያቸውን እንደማይቀበል የምትጠብቅ ሲሆን ይህንን ካደረገ ግን ጉዳዩን ወደ ፍርድቤት ይዘውት እንደሚሄዱ ተናግራለች።

ባለፈው ዓመት ዴንማርክ በግሪንላንድ የዴንማርክ ቀንቋ የሚናገሩ ልሂቃን ለማፍራት በሚል በ1950ዎቹ ከቤተሰቦቻቸው ለተወሰዱ ስድስት ሰዎች ይቅርታ ጠይቃ ካሳ ከፍላለች።

ግሪንላንድ 57 ሺህ የሚሆን ሕዝብ ያላት ሲሆን በዓለማችን በሰሜን ዋልታ ጫፍ የምትገኝ ትልቋ ደሴት ናት።

ግዛቷ የመገበያያ ገንዘቧ፣ የፍትሕ ሥርዓቷ እና የውጭ እና የደኅነንት ጉዳዮች አሁንም በዴንማርክ ቁጥጥር ሥር ቢሆንም የራሷ ሰንደቅ ዓላማ፣ ቋንቋ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አላት።