ሳይንቲስቶች የምድራችን ሰሜን ዋልታ ጫፍ የሆነውን ደሴት አገኙ

ግሪንላንድ ደሴት

የፎቶው ባለመብት, MORTEN RASCH, UNIVERSITY OF COPENHAGEN

የምስሉ መግለጫ, ግሪንላንድ ደሴት

ሳይንቲስቶች የምድራችን ሰሜን ዋልታ ጫፍ የሆነ ደሴት ማግኘታቸውን አሳወቁ።

ደሴቱ የሰሜን ዋልታ ጫፍ እንደሆነ የታወቀው በአጋጣሚ ነው።

ሳይንቲስቶቹ ኦዳቅ ከተባለ ደሴት ናሙና እየሰበሰቡ ነበር። ይህ ደሴት እአአ ከ1978 ጀምሮ በሳይንስ ማኅበረሰቡ ዘንድ ይታወቃል።

ሳይንቲስቶቹ ከኦዳቅ ደሴት ናሙና እየሰበሰቡ ሳሉ ያሉበትን አካባቢ በቅርበት ያስተውሉ ጀመር። አካባቢው በሰሜናዊ ዋልታ 2,625 ጫማ ላይ እንደሆነ ተገዘነቡ።

60 በ30 ሜትር ስፋት ያለው ይህ ደሴት ግሪንላንድ ነው። ለሰሜን ዋልታ እጅግ ቅርብ እንደሆነም ሳይንቲቶቹ ተናግረዋል።

ግሪንላንድ የዴንማርክ ግዛት ውስጥ የሚገኝ የአርክቲክ ክፍል ነው።

የሳይንሳዊ ጥናቱ መሪ ሞርተን ራሽ እንደሚሉት፤ ይህ ደሴት የተገኘው በዴንማርክ እና ስዊዘርላንድ ጥምር ምርምር ወቅት ነው።

በግሪንላንድ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ተመራማሪ የሆኑት ሞርተን የምርምሩ አጋር መስራች ነበሩ።

"እቅዳችን ኦዳቅ ደሴትን ማጥናት ነበር። ይህ ደሴት በምድር ሰሜን ዋልታ ጫፍ ላይ የሚገኘው ደሴት ተብሎ ነበር የሚታወቀው" ሲሉ ተናግረዋል።

በኦዳቅ ደሴት ላይ የሚገኙ አዲስ ዝርያዎችን ለማግኘት ናሙና እየሰበሰቡም ነበር።

ስድስት ሆነው በሂሊኮፕተር ኦዳቅ ደሴት ሲደርሱ ግን ደሴቱን ማግኘት አልቻሉም። በዚያ አካባቢ ካርታ በትክክል ስለማይሠራ ደሴቱን እንዳጡት ነበር ያሰቡት።

"እናም ደሴቱን መፈለግ ጀመርን። ከደቂቃዎች በኋላ እጽዋት ያልበዛበት፣ በጭቃ የተሞላ መሬት አገኘን። በባህር ዳርቻ እና በበረዶ የተከበበ ደሴት ነበር" ሲሉ ያስታውሳሉ።

ከዚህ ጉዟቸው በኋላ ሳይንቲስቶቹ ስለ ደሴቱ ተወያዩ።

"በዚህ ጊዜ ነው የምድር የሰሜን ዋልታ ጫፍ የሆነውን ደሴት በአጋጣሚ እንዳገኘን ያወቅነው" ይላሉ ተመራማሪው።

ይህ ግኝት ከሳይንስ አንጻር "እምብዛም ትልቅ ግኝት አይደለም" ሲሉ ተመራማሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ነገሩ ከሳይንቲስትነታቸው ይልቅ እንደ ግለሰብ የበለጠ እንዳስደሰታቸው ይናገራሉ።

"በምድር ሰሜን ዋልታ የመጨረሻው ጫፍ ላይ ደርሰው ጫማቸው በጭቃ ከተለወሰ ስድስት ሰዎች አንዱ መሆን ያስደንቃል" ይላሉ።

ሳይንቲስቶቹ ያገኙት ደሴት 'ኳከርታክ አቫንራልክ' የሚል ስያሜ እንዲሰጠው ይፈልጋሉ። ይህ ስም በግሪንላንድ ቋንቋ የሰሜን ጫፍ ደሴት ማለት ነው።

ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ 2019 ላይ አሜሪካ ይህንን ግዛት ልትገዛው እንደምትችል ሲናገሩ ዴንማርክ ነገሩን አጣጥላው ነበር።

ነገር ግን ዓለም በግሪንላንድ ጉዳይ ላይ ፍላጎቱ እየጨመረ መጥቷል።