"የሰው ነገር በቃኝ" ብለው ለ32 ዓመት ብቻቸውን የኖሩት ሽማግሌ ከኖሩባት ደሴት ተባረሩ

ማውሮ ሞራንዲ

የፎቶው ባለመብት, Mauro Morandi

የምስሉ መግለጫ, ማውሮ ሞራንዲ

ለሰላሳ ዓመታት በላይ በአንዲት የጣሊያን ደሴት ላይ ብቻቸውን ደስተኛ ህይወት ሲመሩ የነበሩት ሽማግሌ ከሚኖሩባት ደሴት ተባረሩ።

ማውሮ ሞራንዲ ይባላሉ። አሁን የ81 ዓመት ሽማግሌ ናቸው። የጣሊያ ዜጋ ሲሆኑ ወደ ቡዴሊ፣ ሰሜን ሳርዲኒያ የሄዱት እንደ በ1989 (እአአ) ነበር።

ቡዴሊ በሜዲታራኒያን ባሕር ውብ ከሚባሉ ሰው አልባ ደሴቶች እንዷ ናት።

ቡዴሊ በዚህች ደሴት የሚኖሩ ብቸኛው የሰው ልጅ ናቸው። ሌላው በሙሉ ውብ ተፈጥሮ ነው።

ባለፈው ዓመት ግን የደሴቲቱ ባለቤቶች "ይልቀቁ" ብለዋቸው ትካዜ ገብቷቸው ቆይቷል።

አማራጭ አልነበራቸውም። ለ32 ዓመታት በብቸኝነት ከኖረባት ደሴት መልቀቅ ግድ ሆኖባቸዋል።

"ችግር የለም መልቀቁንስ እለቃለሁ። ቡዴሊ ደሴትን ለ32 ዓመታት እንደተንከባከብኳት አዲስ የሚመጡ ነዋሪዎችም እንደሚንከባከቧት ቃል ይቡልኝ" ሲሉ እሁድ ዕለት በፌስቡክ ገጻቸው የስንብት ቃላቸውን አስፍረዋል።

ሽማግሌው ለእነዚህ ሁሉ ዓመታት ከሰው ጋር ተቆራርጠው ሲቆዩ ኤሌክትሪክ ያገኙ የነበረው ከሶላር [ፀሐይ ብርሃን የሚመነጭ ኃይል] ነበር።

በክረምቱ ወቅት ከ30 እስከ 40 መጻሕፍትን ያነቡም ነበር።

"እንዴት ያለ ጓደኛ ትኖራለህ ይሉኛል፤ ብዙ ጓደኛ ነበር ያለኝ። እነሱም መጻሕፍት ናቸው" ሲሉ በሕይወታቸው ዙርያ በተሠራ አንድ ዘጋቢ ፊልም ላይ ተናግረዋል።

"ደግሞም ጓደኞቼ ክደውኝ አያውቁም…" በማለት ለመጻሕፍት ያላቸውን ፍቅር ገልጠዋል።

የቡዴሊ ደሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የቡዴሊ ደሴት

ከአራት ዓመት በፊት እኚሁ ግለሰብ ከቢቢሲ 'አውትሉክ' ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ በሕይወት ዘመናቸው ሁሉ አማጺና ያልተመለዱ ነገሮችን ማድረግ ይወዱ እንደነበር ጠቀስ አድርገው ነበር።

ሚስተር ሞራንዲ በሙያቸው የስፖርት አስተማሪ ናቸው።

በዚያ ቃለ መጠይቅም ለምን ዓለም በቃኝ ብለው ወደ ደሴቲቱ እንዳመሩ ተጠይቀው ነበር።

"በኅብረተሰባችን የሞራል ዝቅጠት ተሰላቸሁ። ሕዝቡ ለብልጭልጭ ሕይወት ያለው መስገብገብ፣ እንዲሁም በተጨማለቀው የጣሊያን ፖለቲካ ተከፋሁ። አንገሸገሸኝ። ስለዚህ ከተፈጥሮ ጋር ይበልጥ ለመቀራረብና ከብልጭልጩ ዓለም ለመራቅ ወሰንሁ። ሰው አልባ ወደሆነው ደሴት የሄድኩትም ለዚያ ነው" ሲሉ ነበር ሞራንዲ ለቢቢሲ የተናገሩት።

ከሰው ሁሉ ተለይቶ ለመኖር ሲያስቡ እሳቸውና ጓደኞቻቸው በቅድሚያ ላ ማዴላና ወደተባለው ስፍራ በመሄድ ሥራ በመሥራት ለተቀረው ጊዜ የሚሆን ገንዘብን ለመቋጠር ነበር የወሰኑት።

ሆኖም ቡዴሊ ደሴት ሲደርሱ የደሴቲቱ ጠባቂዎች ከደሴቷ እየለቀቁ እንደሆነና ጡረታ እንደሚወጡ ሲያውቁ ሞራንዲ እዚያው እቀራለሁ አሉ። ብቻቸውን። አሁን ወደ ሕዝብ የተቀላቀሉት ከ32 ዓመታት የብቸኝነት ሕይወት በኋላ መሆኑ ነው።

"በደሴቲቱ ከሰው ጋር ሳልገናኝ ለ32 ዓመታት ስኖር አንድም ቀን አሞኝ አያውቅም፤ በክረምቱ አንድም ቀን አስሎኝ አያውቅም፤ ውብ ሕይወት ነው ያሳለፍኩት" ብለዋል።

ሞራንዴ ከዚህ ደሴት ሊባረሩ በነበረ ጊዜ ጣሊያናውያን እንዳይባረሩ የድጋፍ ፊርማ አሰባስበው ለመንግሥት ማቅረባቸው ይታወሳል።

መንግሥት ሽማግሌውን እንዳያባርር ከ70ሺህ በላይ ሰዎች በድጋፍ ፊርማ ጠይቀው ነበር።

እሁድ ዕለት ሚስተር ሞራንዴ ለጋርዲያን ጋዜጣ እንደተናገሩት የተቀረ ሕይወታቸውን በትንሽዬ አፓርትመንት ውስጥ እንደሚያሳልፉና ክፍሏም ወደ ባሕር የምታሳይ መስኮት ስላላት ባሕሩን እያዩ እንደሚውሉ ተናግረዋል።