የታዳጊዋ የማኅበራዊ ሚዲያ መልዕክት አሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደርሰ

የፎቶው ባለመብት, ACLU
በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያስተላለፈችው ቁጣ የቀላቀለበት ረዥም መልዕክት ምክንያት ከትምህርት ቤቷ የሕብረ ዝማሬ የስፖርት ደጋፊዎች ቡድን እንድትባረር የተደረገችው ታዳጊ ጉዳይ ወደ አሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ደረሰ።
ብራንዲ ሌቪ እአአ በ2017 በቡድኗ እና በትምህርት ቤቷ ላይ ቁጣና ስድስብ የተቀላቀለበትን መልዕክት 'ስናፕቻት' በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ማቅረቧን ተከትሎ ነው መነጋገሪያ የሆነችው።
የፔንሲልቬንያ ትምህርት ቤት ስፖርት ቡድን አሰልጣኞች መልዕክቷን ከተመለከቱ በኋላ ለአንድ ዓመት ያህል ከቡድኑ አባልነት አግደዋታል።
ፍርድ ቤቱ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎቻቸው ከግቢያቸው ውጪ በሚናገሩት ጉዳይ የመቅጣት መብት ይኑር አይኑራቸው የሚለውን ይወስናል።
ይህም ጉዳዩ በነጻነት የመናገር መብቶችን ለሚጠብቀው የአሜሪካ ሕገ መንግስት የመጀመሪያ ማሻሻያ እንደ ፈተና ተደርጎ እየተወሰደ ነው።
በጉዳዩ ላይ የግራ ቀኝ ክርክሮች ረቡዕ መሰማት ይጀምራሉ።
መልዕክቱ ምን ነበር?
የ14 ዓመቷ ሌቪ ለሕብረ ዝማሬ የስፖርት ደጋፊዎችቡድኑ ባለመመረጧ መበሳጨቷን በፎቶ እና በጽሁፍ የገለጸችበት መልዕክት ከ24 ሰዓታት በኋላ ከማኅበራዊ ሚዲያው ገጽ ላይ ጠፍቷል።
በዕለተ ቅዳሜ በማሃኖይ ከተማ በሚገኝ አንድ ሱቅ ሳለች ነበር መልዕክቱን ያስተላለፈችው። ሱቁ ደግሞ የትምህርት ቤቱ አካል አይደለም።
የመሐል ጣቷን በማሳየት አራት ቃላት ተጠቅማ ቡድኑን፣ ስፖርቱን እንዲሁም ትምህርት ቤቱን ጨምሮ ስለ"ሁሉም ነገር" አስጸያፊ መልዕክት አስተላልፋለች።
መልዕክቱንም አንድ ጓደኛዋ ፎቶ አንስታ አስቀርታው ኖሮ በማሃኖ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የዳንስ አሰልጣኝ ለሆኑት ግለሰብ ልጅ ታሳያታለች።
አሰልጣኞቹም ሌቪን ለአንድ ዓመት ከቡድኑ አግደዋታል።
ሌቪ የማሃኖይ ትምህርት ቤት የመናገር ነጻነትን የሚደነግገውን የመጀመርያው የሕገ መንግሥት ማሻሻያን የጣሰ ነው በማለት ካሳለች።
ሌቪ ክርክር ምንድነው?
አሁን 18 ዓመት የሞላት ሌቪ መልዕክቱ የተላለፈው በእረፍት ቀኗ ከትምህርት ቤቱ ግቢ ውጪ እንደሆነ ትናገራለች። በዚህም ትምህርት ቤቱ እኔን የመቅጣት ስልጣን አልነበረውም ትላለች።
የጠቅላይ ፍርድ ቤት የተማሪዎች ንግግር የተጠበቀ መሆኑን 1969 ወስኖ ነበር። በወቅቱ የቬትናም ጦርነትን በመቃወም ጥቁር የእጅ ልብስ ለብሰው የመጡ ተማሪዎች ጉዳይን ነበር ፍርድ ቤቱ የተመለከተው።
ፍርድ ቤቱ በጉዳዩ ላይ በሰጠው ውሳኔ የተማሪዎቹ ንግግር በትምህርት ቤቱ ላይ "ቁሳዊ" ጉዳት እስካላስከተለ ድረስ የተፈቀደ ነው ብሏል።
የሌቪ ጉዳይ ባለፈው ዓመት በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ቀርቦ የፊላዴልፊያ ፍርድ ቤት እርሷን በመደገፍ ውሳኔ አስተላልፏል።
በዚህም በ 1969 የተሰጠው ፍርድ ተማሪዎች ከግቢው ውጪ ለሚናገሯቸው ነገሮች ትምህርት ቤት ተማሪዎችን የመቅጣት ስልጣንን አልሰጣቸውም ብሏል።
ፍርድ ቤቱ ውሳኔው "ከትምህርት ቤቱ ግቢ ውጭ የሚደረግ የተማሪ ንግግርን አመጽ የሚያስቀይር ወይም ሌሎችን የሚጎዳ ስለመሆኑ በመጀመሪያ አሜንድመንት" እንዳላየ አፅንኦት ሰጥቷል።
ሌቪ ለአሶሺየትድ ፕሬስ "እንደ እኔ ያሉ ወጣት ተማሪዎች ስሜታቸውን በመግለጽ እና ሌሎች ስሜታቸውን እንዲያውቁላቸው በማድረጋቸው ቅጣት ሊደርስባቸው እንደማይገባ ለማሳየት እሞክራለሁ" ብላለች።
ትምህርት ቤቱስ ምን ይላል?
ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ባለፈው ዓመት ከሰጠው ውሳኔ በኋላ የትምርት ቤቱ ክሱ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስዶታል።
ከግቢው ውጪ ለሚፈጠሩ ንግግሮች እና ድርጊቶች ሠራተኞቹ በተለምዶ ተማሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ተከራክሯል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ይህ አስፈላጊ ሆኗል ይላል።
በኮቪድ -19 ምክንያት በርቀት ተማሪዎች በበይነ መረብ መማራቸው ትምህርት ቤቶች ከግቢ ውስጥ እና ውጪ ያላቸውን ኃላፊነት አደብዝዞታል ሲል በምክንያትነት አስቀምጧል።
የካምፓስ ግንኙነቶች
በተጨማሪም የሌቪ የ "ስናፕቻት" መልዕክትም ለትምህርት ቤት ጓደኞቿ እና አብረዋት ለሚደንሱት በመላኩ የትምህርት ቤቱን ማኅበረሰብ እንዳወከም ይናገራል።
ወጣቷን የሚደግፈው ውሳኔ ትምህርት ቤቶች ከትምህርት ሰዓት ውጪ የሚከሰተውን ትንኮሳ፣ ዘረኝነት እና ማንቋሸሽን እንዳይከላከል የበለጠ አስቸጋሪ ያደርገዋልም ብለዋል።












