በሞቃዲሾ የተከሰተው ውጊያ የለየለት ጦርነት እንዳይቀሰቅስ አስግቷል

ተቃዋሚዎችና ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ በሁለት ተጻራሪ ኃይሎች መካከል ውጊያ ተካሄደ።

ትናንት እሁድ ከአገሪቱ ቤተ መንግሥቱት አቅራቢያ የከባባድ መሣሪያዎች ድምጽና የተኩስ ልውውጥ እንደነበረ ከስፍራው የሚወጡ መረጃዎች አመላክተዋል።

ሞርታር ጭምር የፕሬዝዳንቱ መቀመጫ ወደሆነው ቤተ መንግሥት ስለመተኮሱ ተሰምቷል።

ውጊያው ምናልባትም ፕሬዝዳንት ፋርማጆን በሚደግፉና በሚቃወሙ የሠራዊት አካላት አልያም በታጣቂዎች መካከል ሳይካሄድ እንዳልቀረ ተጠርጥሯል።

ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ ወይም (ይበልጥ የሚታወቁበት ስማቸው ፋርማጆ) የሥልጣን ዘመናቸውን በሁለት ዓመት ማራዘማቸው እያነጋገረ ነበር።

የፋርማጆ የሥልጣን ዘመን ባለፈው የካቲት ወር ማብቃት ነበረበት።

የፋርማጆ ሥልጣናቸውን ማራዘም በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ እየተወገዘ ይገኛል። የአፍሪካ ሕብረትም ሆነ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፋርማጆ ውሳኔ እንዳሳሰባቸው ከመግለጽ አልተቆጠቡም።

ትናንት እሁድ በወጡ አንዳንድ ዘገባዎች እንደተመላከተው በአንዳንድ አካባቢዎች የተነሱ አለመግባባቶች እየሰፉ ሄደው ማዕከላዊ ሞቃዲሾን ሲያምሱ ውለዋል።

አንዳንድ የአገሬው መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት ከሆነ ግጭቱ በዋናነት የፋርማጆን መንግሥት በሚደግፉና በሚቃወሙ ታጣቂ ኃይሎች መካከል የተደረገ ነበር። የጎሣ መሪዎችም በግጭቱ ተሳትፎ ነበራቸው።

እስከአሁን በትናንቱ ግጭት ስለደረሰው ጉዳት የተባለ ነገር የለም።

የግል የሆነው 'ካሲማዳ' የወሬ ድረ ገጽ እንዳለው ጸረ ፋርማጆ ሰልፈኞች ወደ ጎዳና ወጥተው ጎማ ያቃጠሉ ሲሆን፤ አማጺ ወታደሮችም የተወሰኑ የሞቃዲሾ ሰሜናዊ ሰፈሮችን መቆጣጠር ችለው ነበር።

የቀድሞው የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ማህሙድ እና የተቃዋሚ መሪው አብዱራህማን አብዲሺኩር የመንግሥት ደጋፊ ታጣቂዎች ቤቶቻቸው ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተናግረዋል።

በተለይ አብዱሺኩር በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንደጻፉት መከላከያ ኃይሉን ፖለቲካ ውስጥ ማስገባት አደጋ አለው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ትናንት ከሰዓት የሶማሊያ ደኅንነት ሚኒስትር ሐሰን ሐነደበይ ጂማሌ ስማቸውን ያልጠቀሷቸው አገሮች ከግጭቱ ጀርባ እንዳሉ አስታውቀዋል። እጃቸውን እንዲሰበስቡም አሳስበዋል።

የደኅንነት ሚኒስትሩ በቴሌቪዥን ወጥተው እንደተናገሩት ታጣቂ ቡድን ወደ ሞቃዲሾ ተሰማርቶ አገሪቱን ለማመስ ተልዕኮ ተሰጥቶት ነበር። ሆኖም አክሽፈነዋል ብለዋል።

ሶማሊያ ለአስርታት በጦርነት ስትታመስ የቆየች አገር ናት።

ከፈረንጆቹ 2011 ጀምሮ ግን የመረጋጋት ዝንባሌን ስታሳይ ቆይታለች። የፋርማጆ መንግሥትም የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ያለው ሆኖ ቆይቷል።

ሆኖም የፋርማጆ ሕጋዊ የግዛት ዘመን በየካቲት ማብቃቱን ተከትሎ ምርጫ መዘግየቱ ያቺን አገር ወደለየለት ግጭት ውሰጥ እንዳይከታት ተሰግቷል።

በሶማሊያ ምርጫ የሚካሄድበት መንገድ ከተመለደው ወጣ ያለና የተወሳሰበ ነው።

በሶማሊያ የቀጥታ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሳይሆን የሚደረገው የጎሳ መሪዎች የሕዝብ ተወካዮችን ከመረጡ በኋላ የተመረጡት የሕዝብ ተወካዮች ናቸው ፕሬዝዳንቱን የሚመርጡት።