የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የአሜሪካ ዜግነታቸውን በይፋ መለሱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ፋርማጆ በይፋ የአሜሪካ ዜግነታቸውን መተዋቸውን ከፕሬዝዳንቱ ጽህፈት ቤት የወጣ መግለጫ አመለከተ።
ምንም እንኳን የሶማሊያ ሕገ መንግሥት ጥምር ዜግንትን የሚፈቅድ ቢሆንም ፕሬዝዳንቱ ከሁለት ዓመት በፊት የሶማሊያን የመሪነት መንበር ሲረከቡ የአሜሪካ ፓስፖርታቸውን ለመመለስ መወሰናቸው ተገልጿል።
ከ28 ዓመታት በፊት ሶማሊያ ውስጥ የአርስ በርስ ጦርነት በተጀመረበት ጊዜ ሞሃመድ ፋርማጆ ትምህርታቸውን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ እየተከታተሉ ነበር። ግጭቱ ለዓመታት በመቀጠሉ ጥገኝነት ጠይቀው እዚያው በመኖራቸው ዜግነትን ለማግኘት ችለው ነበር።
ሞሃመድ ፋርማጆ አሜሪካ ውስጥ በምትገኘው የቡፋሎ ከተማ የትራንስፖርት መስሪያ ቤት ውስጥ በመስራት ላይ ሳሉ ነው የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ጥሪ የቀረበላቸው።
ከአስር ዓመት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ቦታ ላይ ለስምንት ወራት ብቻ አገልግለው ወደ አሜሪካ ተመልሰው ነበር።
ሞሃመድ ፋርማጆ ከሦስት ዓመታት በፊት ቤተሰቦቻቸውን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ትተው እንደገና ወደ ሶማሊያ በመመለስ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር እጩነታቸውን አሳወቁ።
ሶማሊያ ለሦስት አስርት ዓመታት በጦርነትና በግጭት ስትታመስ በመቆየቷ የተነሳ የወቅቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች ጥምር ዜግነት አላቸው።
ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ዜግነታቸውን የተዉት የተለያዩ ጥቅሞችን በሚያስገኘው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የአሜሪካን ዜግነት ይዘው መሳተፍ ባለመቻላቸው ይሁን ወይም በሌላ ግልጽ አልሆነም።
ሞሃመድ ፋርማጆ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሆነው ከተመረጡ ጊዜ አንስቶ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ኒው ዮርክ ውስጥ በየዓመቱ በሚያካሂደው ጉባኤ ላይ ተሳትፈው አያውቁም።












