አይቮሪኮስት በሙስና ሰበብ የአሽከርካሪ ፈታኞችን በሙሉ ከሥራ አገደች

አይቮሪኮስት ውስጥ ያሉ መንገዶች ከብዙ የአፍሪካ አገራት የተሻሉ ናቸው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አይቮሪኮስት ውስጥ ያሉ መንገዶች ከብዙ የአፍሪካ አገራት የተሻሉ ናቸው

የአይቮሪኮስት መንግሥት በሙስና የተበላሸ ነው ያለውን የአሽከርካሪዎች ምዘና ዘርፍ ለማስተካከል በአገሪቱ ያሉ የአሽከርካሪ ፈታኞችን በሙሉ ከሥራ አገደ።

መንግሥት እንዳለው በዘርፉ ያለው ማጭበርበር፣ ሙስናና እየጨመረ ያለ የተሽከርካሪ አደጋ ለዚህ እርምጃው ዋናኞቹ ምክንያቶች ናቸው።

በዚህም ምክንያት ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት በአገሪቱ ውስጥ የሚደረጉ የአሽከርካሪዎች ፈተናዎች በሙሉ በፖሊስ መኮንኖች የሚሰጥ እንደሆነ የትራንስፖርት ሚኒስትሪ አማዱ ኮኔ ተናግረዋል።

ጨምረውም አገሪቱ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ አፍስሳ "የተሻለ ጥራት ያላቸው መንገዶችን ብትገነባም" አብዛኞቹ አደጋዎች በአሽከርካሪዎች ችግር ምክንያት የሚከሰቱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

አይቮሪኮስት ውስጥ በየዓመቱ 1,400 ሰዎች በመንገድ ትራፊክ አደጋ ለሞት ይዳረጋሉ።

ቢያንስ 38 ሰዎች በዚህ በሚያዚያ ወር ብቻ በመኪና አደጋ ሲሞቱ፤ ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ ስምንት ሰዎች ከዋና ከተማዋ አቢጃን 149 ኪሎ ሜትር ርቆ በሚገኝ ቦታ ላይ አንድ ሚኒባስና አንዲት መኪና ተጋጭተው በተነሳ እሳት ተቃጥለው ሞተዋል።

አይቮሪኮስት ከሌሎች የአፍሪካ አገራት በትራፊክ አደጋ የተሻለች ብትሆንም፤ የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው ከ183 የዓለም አገራት የከፋ የትራፊክ አደጋን በማስመዝገብ 50ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በአይቮሪኮስት የመንጃ ፍቃድ ለማውጣት ያለው ሂደት በሙስና ተሞላ እንደሆነ ይነገራል። በዚህም የተለያዩ አካላዊና የማሽከርከር ብቃት ምዘናዎችን ለማለፍ ገንዘብ ከተከፈለ ያለምንም ፈተና ማለፍ ይቻላል።

ከዚህ ባሻገርም ምንም አይነት የአሽከርካሪነት ምዘና የፈተና ሂደቶች ውስጥ ሳይታለፍ ገንዘብ በመክፈል ብቻ የመንጃ ፈቃድ ማውጣት እንደሚቻል ተገልጿል።