የዓለማችን ለኑሮ ምቹ የሆኑ 10 ከተሞች ይፋ ሆኑ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በዓለማችን ለኑሮ ምቹ የሆኑ 10 ከተሞች ይፋ ሆኑ። ከተሞቹ ምርጥ የተባሉት ለኑሮ ባላቸው ምቹነት መሠረት ነው።
አውሮፓዊቷ አገር የኦስትሪያ ዋና ከተማ ቪዬና ቀዳሚዋ የዓለማችን ምቹ ከተማ ተብላለች።
በተከታይነት ደግሞ የዴንማርክ ኮፐን ሃገን እና የስዊትዘርላንድ ዙሪክ ከተሞች ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
የካናዳ ከተማ የሆኑት ካልጋሪ እና ቫንኩቨር ደግሞ በአራተኝነት በቀጣይ ደረጃ ላይ የተቀመጡ ሲሆን፤ የስዊትዘላንዷ ጄኔቫ፣ የጀርመኗ ፍራንክፈርት፣ የካናዳዋ ቶሮንቶ፣ የኔዘርላንድስ አምስተርዳም፣ የጃፓን ኦሳካ እና የአውስትራሊያዋ ሜልበርን ቀዳሚዎቹን አስር ደረጃዎች ለመያዝ በቅተዋል።
ይህንን ደረጃ ይፋ ያደረገው ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት እንደሚለው ከሆነ ከተሞች ለኑሮ ያላቸው ምቹነት ቢጨምርም ዓለም አቀፉ አማካይ ግን አሁንም ዝቅተኛ ነው ብሏል።
ለኑሮ ምቹነት ከታዩት ጉዳዮች አንዱ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ተጽዕኖ መሆኑን ተጠቁሟል።
የዩክሬን ጦርነት ደግሞ ኪዬቭ ከጥናቱ ውጪ እንድትሆን ሲያስገድዳት፣ በሩሲያዎቹ ሞስኮ እና ሴንት ፒተርስበርግ ውጤት ላይም ተጽዕኖ አሳድሯል።
በዚሁ ጦርነት ምክንያት የምሥራቅ አውሮፓ ከተሞች ደረጃም ዝቅ ብሏል።
የምዕራብ አውሮፓ እና የካናዳ ከተሞች ደረጃውን በመምራት ቀዳሚ ሆነዋል።
ደማስቆ፣ ትሪፖሊ እና ሌጎስ ደግሞ ከማኅበራዊ አለመረጋጋት፣ ሽብር እና ግጭት ጋር ተተያይዞ በደረጃው መጨረሻ ላይ ለመገኘት ተገደዋል።
በዘንድሮው ጥናት 33 አዳዲስ ከተሞች ተካተዋል።
በዝቅተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ከተሞች ብዙ መሻሻል አላሳዩም ተብሏል።
የሶሪያዋ ደማስቆ በደረጃው የመጨረሻው ስፍራን ይዛለች።
ቴህራን፣ ዱዋላ፣ ሃራሬ፣ ዳካ፣ ፖርት ሞርስባይ፣ ካራቺ፣ አልጀርስ፣ ትሪፖሊ፣ ሌጎስ እና ደማስቆ ናቸው የመጨረሻዎቹን አስር ደረጃዎች የያዙት።
ለኑሮ ባላቸው ምቹነት መሻሻል ያሳዩ ከተሞችም ታይተተዋል።
እነዚህ ከተሞች በአብዛኛው በምዕራብ አውሮፓ የሚገኙ የጀርመን፣ የዩናይትድ ኪንግደም እና የፈረንሳይ ከተሞች ናቸው።
ፍራንክፈርት ካለፈው ዓመት 32 ደረጃዎችን በማሻሻል ሰባተኛ ደረጃ ላይ ለመቀመጥ በቅታለች።
ሃምቡርግ ደግሞ ከ31ኛ ወደ 16ኛ ተመንድጋለች።
የኒውዚላንድ እና የአውስታራሊያ ከተሞች ደግሞ ደረጃው ላይ ማሽቆልቆል አስመዝግበዋል።
በዚህም ዌሊንግተን እና ኦክላንድ 46 እና 33 ደረጃዎችን ለመውረድ ተገደዋል።
ድርጅቱ ይህን ደረጃ ለማውጣት የከተሞቹን መረጋጋት፣ የጤና ዘርፍ፣ ባህል እና አካባቢ፣ ትምህርት እና መሠረተ ልማት ከግምት ያስገባል።
ይህንን ደረጃ ይፋ ያደረገው ተቋም የዩክሬን ጦርነት እና ኮቪድ በሚቀጥለው ዓመት በሚኖረው የከተሞች ለኑሮ ምቹነት ደረጃ ላይ ተጽዕኖ ይኖራቸዋል ብለዋል።
ኢኮኖሚስት ኢንተለጀንስ ዩኒት ላለፉት 70 ዓመታት ኢኮኖሚያዊ ትንታኔዎች በመስጠት የሚታወቀው ሲሆን የዘ ኢኮኖሚስት ጋዜጣ እህት ኩባንያ ነው።












