በነፍስ ግድያ ወንጀል ለ38 ዓመታት የታሰረ ግለሰብ በዘረ መል ማስረጃ ነፃ ወጣ


አራት አስርታትን በእስር ቤት ያሳለፈው ፒተር ሱሊቫን ነጻ መሆኑ ሲነገረው በመደነቅ እጁን በአፉ ላይ ጭኗል

በብሪታንያ በአንድ ሴት ግድያ 38 ዓመታት ተፈርዶበት በእስር የቆየው ግለሰብ በዘረ መል (ዲኤንኤ) ማስረጃ በይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በነፃ ተለቀቀ።

ፒተር ሰልቫን እ.አ.አ በ1986 የ21 ዓመቷ ዳያን ሲንዴል ከስራ ወደ ቤቷ ስትመለስ ፆታዊ ጥቃት በማድረስ እና በመግደል ወንጀል ተከስሶ ጥፋተኛ ተብሏል።

የወንጀል ጉዳዮች መርማሪ ኮሚሽን ባለፈው ዓመት መዝገቡን ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው በዘር ፈሳሽ ዘረ መል ናሙና ላይ በተደረገ አዲስ ምርመራ ያልታወቀ አጥቂ መለየት በመቻሉ ነው።

በቪድዮ ፍርድ ቤት የቀረበው ፒተር ከእስር እንደሚለቀቅ ሲነገረው በእንባ እና በበድንጋጤ ታጅቦ ዜናውን ተቀብሏል።

68 ዓመት እድሜን የያዘው የፒተር ሰልቫን ጉዳይ በብሪታኒያ የሕግ ታሪክ የረጅም ዓመት የፍትሕ መጓደል ተጎጂ እንደሆነ ይታመናል።

በጠበቃው በኩል በተነበበው መግለጫው ፒተር "አልተበሳጨሁም፤ አማራሪ አይደለሁም" ብሏል።

"እኔ ላይ የተፈፀመው በጣም ስህተት ነበር። ነገር ግን የሆነው ነገር ዘግናኝ እና እጅግ አሳዛኝ የሕይወት መጥፋትን አይቀንስም" ሲል መግለጫው ጠቅሷል።

"እውነት ነፃ ያወጣችኋል" በማለትም አክሏል።

ከፍርድ ቤት ውሎው በኋላ የፒተር እህት ኪም ስሚዝ "ማንም አላሸነፈም" ያለች ሲሆን ለሟቿ ዳያን ሲንዴል ቤተሰቦች ሀዘኗን ገልፃለች።

"ልጃቸውን አጥተዋል። መልሰው ሊያገኟት አይችሉም። እኛ ፒተርን መልሰን አግኝተነዋል፤ ከእርሱ ጋር ሕይወታችንን በድጋሚ ለመገንባት እንሞክራለን" ብላለች።

ፖሊስ እና ዐቃቤ ሕግ የዘር ፈሳሽ ናሙናውን የሚመረምር ቴክኖሎጂ በግድያው ወቅት እንዳልነበረ ገልፀዋል።

ዳኞች የዘረ መል ማስረጃውን መቀበል ለፍትሕ አስፈላጊ እና ጠቃሚ መሆኑ ጥርጥር የለውም ብለዋል።

"ከቀረበው ማስረጃ አንፃር የይግባኝ አቅራቢውን የጥፋተኝነት ውሳኔ አስተማማኝ አድርጎ መቀበል ይቻላል" ብለዋል።

የዘር ፈሳሹ በእውነተኛ አጥቂው እና ገዳዩ የተተወ ማስረጃ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከአንድ ሰው በላይ በግድያው መሳተፉን የሚያሳይ ማስረጃ የለም ያሉት አንድ ዳኛ፤ የዘር ፈሳሽ ማስረጃው በፈቃደኝነት ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈፀሙን አያሳይም ብለዋል።

በዘረ መል ማስረጃው ነፃ የወጣው ፒተር ሰልቫን ከ38 ዓመታት ከሰባት ወራት እና ከ21 ቀናት እስራት ወይም ከ14 ሺህ 113 ቀናት የእስር ቤት ቆይታ በኋላ ተለቋል።

የዘረ መል ናሙናው በወቅቱ የሟቿ ዳያን እጮኛ የነበረው ግለሰብ አለመሆኑንም መርማሪዎች ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።

ፖሊስ የግድያ መዝገቡን ዳግም የከፈተ ቢሆንም ናሙናውን ከብሔራዊ የዘረ መል ቋት ፍለጋ አካሂዶ ውጤት አለማግኘቱን ገልጿል።

ዳያን ጭንቅላቷ ላይ በደረሰባት ተደጋጋሚ ድብደባ ምክንያት ሕይወቷ ያለፈ ሲሆን፤ በማግስቱ ልብሶቿ ተቃጥለው ተገኝተዋል።

ምስክሮች ፒተር ሰልቫንን በአካባቢው ማየታቸውን ተከትሎ ነበር ተጠርጣሪ የሆነው።

በምርመራው ወቅት የት እንደነበር የሚጣረስ ቃሎችን በመስጠት እና ግድያውን መናዘዙ ታውቋል።

ይኹን እንጂ ጠበቃም ሆነ ወላጆች በወቅቱ አብረውት ባለመገኘታቸው የሰጠው ማስረጃ አስተማማኝነት ጥርጣሬ ውስጥ ገብቷል።