እስራኤል በጋዛ ሆስፒታል ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 28 ሰዎች ተገደሉ

እስራኤል ካሀን ዩኒስ በተባለ አካባቢ በሚገኘው የአውሮፓ ሆስፒታል ላይ ባደረሰችው የአየር ጥቃት 28 ሰዎች መገደላቸውን እና በርካታ ሰዎችን መቁሰላቸውን በሃማስ የሚመራው የሲቪል መከላከያ ኤጄንሲ ገለፀ።
የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች በሆስፒታሉ ስድስት ቦንቦችን በተከታታይ በመጣል የሆስፒታሉን ቅጥር ግቢ እና ዙሪያ መደብደባቸውን የአካባቢው ምንጮች ተናግረዋል።
የእስራኤል መከላከያ ከሆስፒታሉ ስር በነበሩ "የሃማስ አሸባሪዎች ማዘዣ እና መቆጣጠሪያ ጣቢያ" ላይ "ትክክለኛ ዒላማ" ያለው ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አስታውቋል።
በጋዛ የሚሰራ የቢቢሲ ጋዜጠኛ በአየር ጥቃቱ ከቆሰሉት መሀል ሲሆን፤ የሕክምና ክትትል እየተደረገለት ይገኛል።
የአየር ጥቃቱ በሆስፒታሉ ውስጥ በርካታ ጥልቅ ጉድጓዶችን የፈጠረ ሲሆን፤ ትልቅ አውቶብስን ጨምሮ በርካታ ተሽከርካሪዎችንም አውድሟል።
የዓይን እማኞች የእስራኤል ድሮኖች የሆስፒታሉ ሕንፃን በመክበብ የነፍስ አድን ሠራኞች ወደ አካባቢው እንዳይገቡ ከልክለዋልም ብለዋል።
ለረድኤት ድርጅት የሚሰሩ ዶ/ር ቶም ፖቶካር ጥቃቱ ሲፈፀም በሆስፒታሉ እንደነበሩ ለቢቢሲ የተናገሩ ሲሆን፤ ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ "ስድስት ከባድ ፍንዳታዎች ተከታትለው" ሆስፒታሉን በቀጥታ መምታታቸውን ገልፀዋል።
"ሙሉ ለሙሉ ድንጋጤ ነበር" ሲሉም አክለዋል።
ሟቾች እና ቁስለኞች በአካባቢው ወደሚገኝ ናስር ሆስፒታል የተወሰዱ ሲሆን፤ የሆስፒታሉ ድንገተኛ ክፍል አስቀድሞ በአየር መደብደቡን የዓይን እማኞች እና ምንጮች ተናግረዋል።
በዚህ ጥቃት ታዋቂ የሆነው ፍልስጤማዊ የፎቶ ጋዜጠኛ ሀሰን አስሊህ ከተገደሉ ሁለት ሰዎች መሀል መሆኑን ተናግረዋል።
ጋዜጠኛው ከዚህ ቀደም በአየር ጥቃት ለደረሰበት ጉዳት በሕክምና ላይ ሳለ በሆስፒታሉ ቀዶ ሕክምና ክፍል ላይ በደረሰ የድሮን ጥቃት ሕይወቱ ማለፉን ገልፀዋል።
የእስራኤል መከላከያ ጋዜጠኛው ሃማስ ጥቅምት 7 በእስራኤል ላይ ባደረሰው ጥቃት ተሳትፎ እንዳለው አስታውቆ ነበር።
የእስራኤል መከላከያ ኃይል እና የእስራኤል ደኅንነት ባለስልጣን በጋራ በሰጡት መግለጫ ሃማስ በጋዛ ሆስፒታሎችን ለእንቅስቃሴው መጠቀም መቀጠሉን ገልፀዋል።
ይህን የእስራኤል የረጅም ጊዜ ውንጀላ ሃማስ ያጣጥላል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙኃን የአየር ጥቃቱ ዒላማ መሀመድ ሲንዋር የተባለ የሃማስ መሪ እና የቀድሞው የቡድኑ መሪ ያህያ ሲንዋር ታናሽ ወንድም መሆኑን ዘግበዋል።
ሃማስ እስካሁን ተገደለ ስለተባለው መሪው ያለው ነገር የለም።
መሀመድ ዲፍ በእስራኤል የአየር ጥቃት መገደሉን ተከትሎ መሀመድ ሲንዋር የቡድኑ ወታደራዊ ክንፍ አዛዥ እንደሆነ ይታመናል።












