ከሳዑዲ ጋር የ142 ቢሊዮን ዶላር የጦር መሳሪያ ስምምነት የደረሱት ትራምፕ የሶሪያን ማዕቀብ ሊያነሱ ነው

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት በሶሪያ ላይ ተጥሎ የቆየውን ማዕቀብ በሙሉ ለማንሳት ቃል ገቡ።

ፕሬዝዳንቱ በሪያድ ባደረጉት ንግግር አሁን ጊዜው ሶሪያ ወደፊት፣ "ወደ ታላቅነት የምትጓዝበት ዕድል" መሆኑን ተናግረዋል።

ትራምፕ በመጀመሪያው ቀን የሳዑዲ አረቢያ ቆይታቸው 142 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ስምምነት የተፈራረሙ ሲሆን፤ እንዲሁም የሳዑዲው ልዑል 1 ትሪሊየን ያወጣሉ ያሏቸው ሌሎች ኢንቨስትመንቶችም ላይ ከስምምነት ደርሰዋል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አገራቸው ከሳዑዲ አረቢያ የበለጠ "ሌላ ጠንካራ አጋር" እንደሌላት ኢንቨስተመንትን ለመሳብ ባለመው የመጀመሪያው የውጭ አገር ጉዟቸው ላይ ተናግረዋል።

ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸውም ሳዑዲ አረቢያ የመጀመሪያዋ የውጭ አገር ጉዟቸው መዳረሻ ነበረች።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ከዚህ በኋላ ኳታርን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን ይጎበኛሉ።

አሜሪካ ለሳዑዲ አረቢያ 142 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የጦር መሳሪያ ሽያጭ ለመፈጸም የተፈራረመች ሲሆን፣ ይህም እንደ ዋይት ሐውስ ገለጻ ዋሺንግተን እስከ ዛሬ ከፈጸመችው ሁሉ ትልቁ "የመከላከያ ትብብር ስምምነት" ነው።

በፕሬዝዳንቱ የሪያድ ጉብኝት ወቅት ለዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት በወደመችው ሶሪያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንደሚነሳ መገለፁ ሌላው ትልቅ ዜና ነበር።

በፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ የተመሩት የሶሪያ አማፂያን የባሻር አል አሳድን መንግሥት ከሥልጣን ያወረዱት በታኅሣሥ ወር ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሪያድ በተካሄደ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በሳዑዲ አረቢያው አልጋ ወራሽ ልዑል ሞሐመን ቢን ሳልማን ጥያቄ መሠረት ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ተናግረዋል።

"ለልዑሉ ምን ማድረግ እችላለሁ" ያሉት ትራምፕ በፎረሙ ላይ የተገኙ እንግዶች በሳቅ አጅበዋቸዋል።

ከአስርት ዓመታት በፊት የተጣለው ማዕቀብ የታለመለትን ዓላማ በሚገባ መምታቱን ተናግረው፣ ነገር ግን አሁን ጊዜው አገሪቱ ወደ ፊት የምትሄድበት ነው ብለዋል።

ይህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ውሳኔ አገሪቱ ወሳኝ የፖሊሲ ለውጥ ማድረጓን ያሳያል።

አሜሪካ በአውሮፓውያኑ 1979 የሶሪያን መንግሥት አሸባሪነትን የሚደግፍ ስትል የፈረጀች ሲሆን በ2004 ደግሞ ማዕቀብ ጥላለች።

በ2011 የእርስ በእርስ ጦርነት ሲቀሰቀስ ደግሞ ሶሪያ ተጨማሪ ማዕቀቦች ተጥለውባታል።

የሶሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሳድ አል ሺባኒ በኤክስ ገጻቸው ላይ ይህንን የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ ሶሪያን ዳግም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት "አዲስ ጅማሮ" እንደሚሆን ተናግረዋል።

የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ትራምፕ ረቡዕ ዕለት ከሶሪያው ፕሬዝዳንት አል ሻራ ጋር አጭር ቆይታ ለማድረግ መስማማታቸውን ገልጸዋል።

ትራምፕ እና የሳዑዲው ልዑል በኃይል፣ በመከላከያ፣ ማዕድን እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ስምምነት ተፈራርመዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ የሶሪያን አዲስ መንግሥት ለመደገፍ የተጣለውን ማዕቀብ ማንሳታቸውን ሲያስታውቁ ይህ እርምጃ የተወሰደው በሞሐመድ ቢን ሳልማን ጥያቄ መሠረት መሆኑ ተገልጿል።

አሜሪካ በሶሪያ ላይ ለአስርት ዓመታት ጥላ የቆየችው ማዕቀብ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ባሻር አል አሳድ ላይ ጫና ለመፍጠር እና ምጣኔ ኃብታዊ ጉዳት ለማድረስ በሚል ነበር።

ትራምፕ የሶሪያውን ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራን ረቡዕ ዕለት ያገኟቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ትራምፕ ከእስራኤል ጋር ያለውን ቀጣናዊ ግንኙነት ለማሻሻል እና ኢራን ላይ ጫና ለመፍጠር ከሳዑዲ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ይፈልጋሉ።

ሁለቱ አገራት የተፈራረሙት ስምምነት የአሜሪካ የአየር እና የሚሳዔል መከላከያ ኩባንያዎችን፣ የአየር ኃይል እና የህዋ፣ የባሕር ኃይል ደኅንነት እና የኮሚዩኒኬሽንን እንደሚያካትት ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

የሮይተርስ የዜና ወኪል ምንጮች በሁለቱ አገራት መካከል በተፈረመው ስምምነት ወቅት ሎክሄድ ኤፍ-35 የተሰኘው የውጊያ አውሮፕላን ተነስቶ የነበረ ቢሆንም በስምምነቱ ውስጥ ስለመካተቱ ግን የታወቀ ነገር የለም ብለዋል።

የሳዑዲው ልዑል በቀጣይ አንድ ወር ውስጥ ሁለቱ አገራት የሚፈራረሙትን ስምምነት ጨምሮ አጠቃላይ 1 ትሪሊዮን ዶላር የሚደርስ ስምምነት መደረጉን ተናግረዋል።

ሳዑዲ አረቢያ ከአሜሪካ የጦር መሳሪያ ገዢ ደንበኞች መካከል ቀዳሚዋ ናት።

ሁለቱ አገራት ላለፉት አስርታት ጠንካራ ወዳጅነት የፈጠሩ ሲሆን፤ ሳዑዲ ነዳጅ ስታቀርብ አሜሪካ ደግሞ ጦር መሳሪያ በመሸጥ ግንኙነታቸውን አጠናክረዋል።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት የሳዑዲ መንግሥት በ2018 ጀማል ኻሾግጂ የተባለውን ታዋቂ ጋዜጠኛ ቱርክ ኢኒስታንቡል ውስጥ ማስገደሉን ተከትሎ ተቀዛቅዞ ነበር።

በወቅቱ የአሜሪካ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ቢን ሳልማን ኻሾግጂ እንዲያዝ ካልሆነም እንዲገደል ትዕዛዝ ማስተላለፋቸውን ገልጾ ነበር።

የሳዑዲ መንግሥት ግን በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ የለኝም ሲል አስተባብሏል።

ትራምፕ በጉዟቸው በጉዳዩ ላይ ምንም ያላሉ ሲሆን፣ ቢን ሳልማንን "አስደናቂ ሰው" ሲሉ አንቆለጳጵሰዋል።

አክለውም "በጣም እንደምንዋደድ አምናለሁ" ብለዋል ትራምፕ።

ትራምፕ በመካከለኛው ምሥራቅ ስላለ ደኅንነት ሳይሆን ኢንቨስትመንት ላይ ባተኮረው በዚህ ጉዟቸው ከሪያድ ወደ ኳታር ረቡዕ ዕለት የሚሄዱ ሲሆን ሐሙስ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስን ይጎበኛሉ።

የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት በርካታ የአገሪቱ የንግድ ሰዎች ያጀቧቸው ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል በአስተዳደራቸው ውስጥ ሹመት የተሰጠው የቴስላ ኃላፊ ኤለን መስክ፣ የኦፕን ኤአይ ሳም አትማን፣ የብላክ ሮክ ላሪ ፊንክ እና የብላክስቶን ስቴፈን ስዋርዝማን ይገኙበታል።

ቢን ሳልማን ራዕይ 2030 ተብሎ በተሰየመው ትልቅ የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሃ ግብር የሳዑዲ ምጣኔ ኃብታዊ ምንጭን በማስፋት ላይ ያተኮሩ ሲሆን፣ ይህም ቤልጂየምን የሚያክለው እና የወደፊቷ ከተማ ተብሎ እየተገነባ ያለውን ግዙፍ ፕሮጀክትን ያካትታል።

ትራምፕ በንግግራቸው ወቅት ሳዑዲ አረቢያ በእስራኤል እና በአንዳንድ የባሕረ ሰላጤው አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ለመጀመሪያ ጊዜ መደበኛ እንዲሆን ያስቻለውን እንዲሁም በመጀመሪያው አስተዳደራቸው ወቅት የተደረሰውን ስምምነት ብትቀላቀል "ህልማቸው" መሆኑን ተናግረው ነበር።

ነገር ግን ሞሐመድ ቢን ሳልማን በጋዛ ያለው ጦርነት በቋሚነት እስኪቆም እና የፍልስጤም አገር የመሆን ዕድል ግልጽ እስካልሆነ ድረስ ይህ እንደማይሆን ተናግረዋል።

ትራምፕ በዚህ ጉዟቸው በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ስላለው ግጭት በአጭሩ ተናግረው ነበር።

በጋዛ የሚኖሩ "የተሻለ የወደፊት ጊዜ" እንደሚገባቸው ለተሰብሳቢዎቹ በመናገር፣ ሐማስ ግን "ለፖለቲካዊ ዓላማ ማገት፣ ማሰቃየት እና ዒላማ ማድረግን" መረጠ ሲሉ በመስከረም 2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ባጣቀሰ መልኩ ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ከሳዑዲ አረቢያ በማስከተል በሚቀጥሉት አስር ዓመታት 1.4 ትሪሊዮን ዶላር ኢንቨስት ለማድረግ ቃል ወደ ገቡት ኳታር እና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ያቀናሉ።