የጤና ባለሙያዎች የጠሩት ከፊል የሥራ ማቆም አድማ መጀመሩን ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, Ethiopian Health professionals
የደሞዝ እና ጥቅማ ጥቅም ጥያቄ በማንሳት ለመንግሥት የሰላሳ ቀናት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ ጊዜ ሰጥተው የነበሩት የጤና ባለሙያዎች ምላሽ ባለማግኘታቸው ከፊል የሥራ ማቆም አድማ መምታታቸውን ለቢቢሲ ተናገሩ።
ባለሙያዎች ከጥቂት "የተመረጡ የሕክምና ክፍሎች" ውጪ ያሉ ክፍሎች ከዛሬ ግንቦት 5/2017 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ ማቆማቸውን ገልፀዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አምስት በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ባለሙያዎች ከድንገተኛ፣ ከማዋለጃ፣ ከፅኑ ሕሙማን እንዲሁም ከድንገተኛ ቀዶ ሕክምና ክፍሎች ውጪ ያሉ የሕክምና ተቋማት ክፍሎች አገልግሎቶች ማቋረጣቸውን ተናግረዋል።
በተለይም ስፔሻላይዝድ እና ኮምፕርሄንሲቭ የሆኑ የአገሪቱ ትላልቅ የሚባሉ ሆስፒታሎች ሥራ ማቆማቸውን የንቅናቄው አስተባባሪዎች የገለፁ ሲሆን፤ "ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ሥራ አቁመዋል" ብለዋል።
ለአብነትም ያህል ጥቁር አንበሳ፣ ቅዱስ ጳውሎስ፣ አለርት፣ ፈለገ ሕይወት፣ ጥበበ ጊዮን፣ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ሆስፒታል፣ አዲስ ዘመን፣ ሐዋሳ ሆስፒታሎች የከፊል አድማው ከተመታባቸው የጤና ተቋማት መሀል የሚጠቀሱ ናቸው።
የአገሪቱ ቀደምት እና ግዙፍ የሆነው ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል "ግማሽ የሚሆኑ ክፍሎቹ" መዘጋታቸውን የገለፁ ስማቸውን እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የጤና ባለሙያ፤ እርሳቸውን ጨምሮ ሐኪሞች ታካሚዎችን "ራውንድ" አይተው ከሥራ መውጣታቸውን ገልፀዋል።
"ስጋት የሌለባቸውን ቦታዎች [ክፍሎች] ዘግተን ወጥተናል" ያሉት ሐኪሙ፤ እስከ 40 በመቶው የሚሆነው የሆስፒታሉ ባለሙያ ሥራ አልገባም ብለዋል።
በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ኮምፕርሄሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሚያገለግሉ ሐኪምም እርሳቸውን ጨምሮ አብዛኞቹ ባለሙያዎች አድማ መምታታቸውን ገልፀው፤ ከድንገተኛ ክፍሎች ውጪ ያለ አገልግሎት "ሙሉ ለሙሉ ዝግ ነው" ብለዋል።
"ተመላላሽ ሕክምና፣ ተኝቶ ህክምና፣ ድንገተኛ ያልሆነ ቀዶ ሕክምና ሙሉ ለሙሉ ዝግ ነው" ያሉት ሐኪሙ "ከተመደቡ ባለሙያዎች ውጪ" ያሉ ሠራተኞች ወደ ሥራ አለመግባታቸውን ተናግረዋል።
ይህን ያረጋገጡ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ አንድ የሆስፒታሉ የሥራ ኃላፊ "ኢንተርን እና ሬዚደንት ሐኪሞች መቶ በመቶ በሚባል ደረጃ አልገቡም" ብለዋል።
ባሕር ዳር የሚገኘው የአማራ ክልል ትልቁ ሆስፒታል የጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ባለሙያዎችም አድማ መምታታቸውን ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ ባለሙያ፤ "95 በመቶ የሚሆኑ የጤና ባለሙያዎች አድማ ላይ ናቸው" ብለዋል።
"የመጨረሻው አቅማችንን አሟጠን እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ ሠርተናል። ከዚህ በላይ ምንም ማድረግ የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ እንጂ የቅንጦት ነገር [ፈልገን] አይደለም" ሲሉ ባለሞያው ለአድማው ተገቢነት ምክንያት አቅርበዋል።
"ዛሬ ብዙ ሆስፒታሎች ሥራ ላይ አይደሉም" ሲሉ ስለ አድማው ማብራሪያ የሰጡት አንድ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ አስተባባሪ፤ የከፊል ሥራ ማቆም አድማው "ባቀድነው ልክ እየሄደ ነው" ብለዋል።
የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ማስተማሪያ ሆስፒታል ኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ለደቡባዊ የኢትዮጵያ ክልሎች ሪፈራል ሆስፒታል ሲሆን፤ በከፊል አድማው "[ታካሚዎች] ይጉላላሉ፤ ሳይታዩ ሊያድሩ የሚችሉ ታካሚዎች ይኖራሉ" በማለት አንድ የሥራ ኃላፊ ተፅዕኖውን ከወዲሁ ገልፀዋል።
ባለሙያዎች በበኩላቸው ይህ እንዳይሆን ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን በመግለፅ፤ ለአጠቃላይ የጤና ሥርዓቱ መስተካከል ሲባል የሚደረግ እርምጃ ስለመሆኑ አስምረዋል።
"እየተራባችሁ፤ ከሰው በታች ሆናችሁ፤ እየተቸገራችሁ፤ ልጅ ማሳደግ ሳትችሉ አገልግሉ የሚል ቃል አልገባንም። እንደዚህ ብዬ እጄን አንስቼ ቃል አልገባሁም" የሚሉት የጥቁር አንበሳ ስፔሻሊት ሐኪም፤ ታካሚዎች ላይ ለሚፈጠር የሕክም እጦት ባለሙያው "ከደሙ ንፁህ ነው" ሲሉ ተጠያቂው መንግሥት ነው ብለዋል።
ሌላ ባለሙያም በበኩላቸው "ወደን የገባንበት ሳይሆን ብቸኛው መንገዳችን ይኸው ነው ብለን ስላሰብን፤ ጠይቀን የሚሰማን ስላጣን ነው" ሲሉ መከፈል ያለበት መስዋዕትነት ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አሁንም መንግሥት "ዝምታን መርጧል" ያሉት የጤና ባለሙያዎች፤ የጤና ተቋማት አመራሮች ባለሙያዎች ላይ ጫና እየፈጠሩ እንደሆነም ተናግረዋል።
"የ11 ተመራቂ ዶክተሮች ደሞዛቸው ታግዷል። ወደ ስድስት የሚሆኑ ስኒየር ዶክተሮች ደግሞ የቃል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል" ሲሉ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጫናዎች እየደረሱ መሆኑን የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሐኪም አስረድተዋል።
የንቅናቄው አስተባባሪ መጋቢት 10 ለታቀደው ሙሉ የሥራ ማቆም አድማ ድረስ መንግሥት ዝም ብሎ ይጠብቃል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ እስካሁን በይፋ መንግሥት የጤና ባለሙያዎችን ለማነጋገር ጥሪ እንዳላቀረበላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የሆስፒታል የሥራ ኃላፊ ግን በሚቀጥሉት ቀናት የፌደራል የሥራ ኃላፊዎች ከባለሙያዎችን ጋር ሊመክሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ውስጥ የሚገኙ የጤና ተቋማት ውስጥ በሚካሄደው ከፊል የሥራ ማቆም አድማ ምክንያት ተቋማቱ ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ ሠራተኞች ወደ ሥራ ገበታቸው እንዲመለሱ የሚያስጠነቅቁ ማስታወቂያዎችን እያወጡ ነው።
ይህ ከፊል የሥራ ማቆም አድማ ከመጀመሩ በፊት መንግሥት ጥያቄያቸውን በመስማት ምላሽ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም ተጨባጭ ነገር እንደሌለ ባለሙያዎቹ ተናግረዋል።
ካለፈው ሳምንት ማብቂያ ጀምሮም በተለያዩ ደረጃዎች ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እና የማኅበር አመራሮች በፀጥታ ኃይሎች መያዛቸው የተነገረ ሲሆን፣ የተወሰኑትም በዋስ መለቀቃቸው ተዘግቧል።
ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ የሆነው አምነስቲ በእስር ላይ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እንዲለቀቁ ጥሪ አቅርቧል።
ሰኞ ምሽት በብሔራዊው ቴሌቪዥን ላይ የቀረቡት የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ መንግሥት የጤና ባለሙያዎቹን ጥያቄ ለመመለስ እየሠራ መሆኑን አመለክተዋል።












