ተመድ፡ "እስራኤል ወደ ጋዛ ምግብ እንዳይገባ ማገድን እንደ ጦር መሣሪያ እየተጠቀመች ነው"

አጠቃላዩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የጋዛ ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አጠቃላዩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የጋዛ ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል

እስራኤል ዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ወደ ጋዛ እንዲገቡ አትፈቅድም። ከ200 በላይ ጋዜጠኞችም በሥራ ላይ ሳሉ ተገድለዋል።

በጋዛ ያለውን ሁኔታ ለመዘገብ ሕይወታቸውን ለአደጋ ካጋለጡ ጋዜጠኞች በተጨማሪ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶችም መረጃዎችን እያወጡ ነው።

የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር ምክትል ዳይሬክተር ፓስካል ሁንዳት እንደሚሉት በጋዛ ያሉ ንጹኃን ሰዎች በተደጋጋሚ ከመፈናቀላቸው እና ዘወትር ለጥቃት ከመጋለጣቸውም ባሻገር ሰብአዊ እርዳታ በመስተጓጎሉ እየተፈተኑ ይገኛሉ።

"በፍጹም ከዚህ በላይ ሁኔታው እንዲባባስ መፍቀድ የለብንም" ይላሉ።

የተኩስ አቁም ስምምነቱ ተጥሶ እስራኤል በጋዛ የምታደርገውን ወረራ ቀጥላለች።

ወደ ጋዛ የሚወስዱ መንገዶች በእስራኤል ተዘግተዋል። ምግብ እና መድኃኒትን ጨምሮ የሰብአዊ እርዳታም ተቋርጧል።

ሁለተኛው ዙር የተኩስ አቁም ስምምነት የሚተገበርበት ዕድል በጦርነቱ ዳግመኛ መጀመር ምክንያት ጠባብ ሆኗል።

እስራኤል ከጋዛ ሙሉ በሙሉ ከወጣች ሐማስ የተቀሩትን ታጋቾች በአጠቃላይ እንደሚለቅ አስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የተቀሩት አክራሪ የእስራኤል ባለሥልጣናት ይሄንን መቀበል አልፈለጉም።

የጋዛ ፍልስጤማውያን በአይሁዳውያን ሰፋሪዎች እንዲተኩ ነው የሚፈልጉት።

አክራሪ ብሔርተኛ የእስራኤል ፖለቲከኞች ኔታንያሁ ወደ ጦርነት እንዲመለሱ ይፈልጉ ነበር። ይህንን ካላደረጉ የፖለቲካ ሕይወታቸው ጥያቄ ውስጥ ይገባል።

አዲስ "የተባባሰ" ጥቃት ጋዛ ላይ ለመሰንዘር ኔታንያሁ ዝተዋል። ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ በነዳጅ የበለጸጉ የአረብ አገራትን ከጎበኙ በኋላ ጥቃቱ እንደሚባባስ ስጋት አለ።

የዘፈቀደ የአየር ጥቃት በማድረስ ፍልስጤማውያንን መግደልና ማፈናቀል የዚህ ዕቅድ አካል ናቸው።

ድንገተኛ ጥቃቶች ሲፈጸሙ ፍልስጤማውያን የሚሸሹበት ጊዜ እንኳን አያገኙም።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጋዛ ከጦርነቱ በፊትም ሕዝብ ተጨናንቆ የሚኖርበት ነበር። እስራኤል የቻለችውን ያህል ፍልስጤማውያንን ከጋዛ ወጥተው ወደ ደቡባዊ ራፋህ አቅራቢያ እንዲሰደዱ ትፈልጋለች።

ራፋህ ሙሉ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ ወድሟል።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው 90 በመቶ ጋዛ ለፍልስጤማውያን መኖሪያ እንዳይሆን ወድሟል።

እስራኤል ሐማስ ወደ ጋዛ የሚገባውን ምግብ ይቆጣጠራል፣ ይሰርቃል ትላለች። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይሄንን ያስተባብላል።

እስራኤል የግል ድርጅቶች ምግብ እንዲያከፋፍሉ ባቀረበችው ሐሳብ ላይ የመንግሥታቱ ድርጅት እንደማይሳተፍ አስታውቋል።

የተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ "የጋዛ ነዋሪዎች እያዩት ያለውን ስቃይ እና እንግልት ለመግለጽ ቃላት ያጥረኛል። ከሁለት ወራት በላይ እርዳታ ተቋርጧል" ይላሉ።

"ረሃብ እየተስፋፋ ነው። ሰዎች ተዳክመዋል። በቀጣይ ሳምንታት እርዳታ ካልገባ ሰዎች በጥቃት ብቻ ሳይሆን በረሃብም መሞት ይጀምራሉ። ሰብአዊ እርዳታን የጦር መሣሪያ አድርጎ መጠቀም የሚባለው ይሄ ነው" ሲሉም ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ከሌሎች የተራድኦ ድርጅቶች እና መንግሥታት ጋር በጥምረት የሚያወጣው ሪፖርት ኢንተግሬትድ ፉድ ሰኪውሪቲ ፌዝ ክላሲፊኬሽን (አይፒሲ) የሚያሳየውም ያንዣበበውን አደጋ ነው።

አጠቃላዩ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው ሕዝብ ለረሃብ ተጋልጧል። ግማሽ ያህሉ ሕጻናት ሲሆኑ አሁን ባሉበት ሁኔታም ለአስከፊ የምግብ እጥረት ተጋልጠዋል።

በእስራኤል ከበባ ምክንያት ሕጻናት እየተራቡ ነው።

አይፒሲ እንደሚለው 22 በመቶ የሚሆኑት የጋዛ ነዋሪዎች (470,000 ሰዎች) ደረጃ አምስት በሚባለው አስከፊ የረሃብ ሁኔታ ውስጥ ናቸው።

"ከአምስት ቤቶች አንዱ ከፍተኛ የምግብ እጥረት ይገኝበታል። እስከ ሞት የሚያደርስ ረሃብ ተጋርጦባቸዋል" ይላል ሪፖርቱ።

ደረጃ አምስት የከፋ ረሃብ የመጨረሻው መለኪያ ነው።

71,000 ሕጻናት እና 17,000 እናቶች የምግብ እጥረት ሕክምና ያስፈልጋቸዋል።

የተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ
የምስሉ መግለጫ, የተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ

አሁን ላይ በሺዎች የሚቆጠር ምግብና መድኃኒት እንዲሁም ሌሎችም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶች ግብፅ ይገኛሉ።

የተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ፣ ባለፉት 19 ወራት (በተለይም ባለፉት 2 ወራት) ያዩትን "የጦር ወንጀል" ሲሉ ነው የሚገልጹት።

"ይሄን የሚፈርጀው ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት። ሆኖም ማየት ከምንችለው ተነስተን ምግብና ሰብአዊ እርዳታ መከልከልን እንደ መሣሪያ በመጠቀም እስራኤል በጋዛ ያላትን የፖለቲካ እና ወታደራዊ ግብ ለማሳካት እየሞከረች ነው" ብለዋል።

የእስራኤል ከበባ እና ተከታታይ ወረራ የዘር ጭፍጨፋ ሊባል የሚችል እንደሆነ ከቢቢሲ ተጠይቀው ቀጣዩን ምላሽ ሰጥተዋል።

"ውድመቱ ከፍተኛ ነው። የተገደሉት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው። ከተጠቀሰውም በላይ ነው። ስልታዊ በሆን መንገድ ትምህርት ቤቶች እና የጤና ተቋማት ሲወድሙ አይተናል። በጋዛ ሰዎች በተደጋጋሚ ተሰደዋል። ከፍተኛ ውድመት ነው። የዘር ጭፍጨፋ ደረጃ ላይ የሚደርስ ነው። ወደዚያ አቅጣጫ ነገሮች እየሄዱ መሆኑን ማየት ይቻላል።"

የእስራኤል መከላከያ ሚኒስቴር እስራኤል ከርትዝ እስራኤል ከበባ ማካሄድን "እንደ ዋነኛ ጫና ማሳደሪያ ስልት" እንደምትጠቀም አልደበቁም።

የብሔራዊ ደኅንነት ሚኒስቴር ኢታማር ቤን-ጋቭር "ሰብአዊ እርዳታ በማቋረጥ ሀማስ ላይ ጫና አሳድረን ታጋቾችን ማስለቀቅ ነው የምንፈልገው" ብለዋል።

የእስራኤል ባለሥልጣናት ንግግሮች ለጋዛ ነዋሪዎች አስፈሪ ናቸው።

1,200 የእስራኤል ተዋጊ አውሮፕላን አብራሪዎች በጻፉት ደብዳቤ ጦርነቱ መራዘሙ "ከደኅንነት ጉዳይ ይልቅ ከፖለቲካና ከግል ፍላጎት ጋር የተገናኘ ነው" ብለዋል።

የተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ እየዋሹ ነው ሲሉ የእስራኤል ባለሥልጣኖች በተደጋጋሚ ሲከሱ ነበር።

"የተጣረሰ መረጃ በማቅረብ የሕዝብን አስተያየት አዛብተዋል" ብላለች እስራኤል።

ሆኖም ግን ዋና ኮሚሽነሩ ክሶቹን ያጣጥላሉ።

የእስራኤልን ክስ ተከትሎ የተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ተቋም 19 ሠራተኞቹ ላይ ምርመራ አድርጓል።

እስራኤል የተቋሙን ሠራተኞች አግዳለች።

የጋዛ ነዋሪዎች ምዕራባቸውን ለእስራኤል ድጋፍ መቀጠላቸው ያሰጋቸዋል።

በሌላ በኩል ዶናልድ ትራምፕ ለጋዛ ነዋሪዎች ምግብ መቅረብ አለበት በሚል ራሳቸውን ለኔታንያሁ እያራቁ ነው።

የተመድ የፍልስጤማውያን ስደተኞች ተቋም ዋና ኮሚሽነር ፊሊፔ ላዛሪኒ "በቀጣይ ዓመታት ምን ያህል ተሳስተን እንደነበረ ይገባናል። ቀውሱን እያየን ነው። በታሪክ የተሳሳተ ወገን አጠገብ ነው የቆምነው" ይላሉ።

"ያልተመጣጠነ ጥቃት ነው። ሕዝቡን የሚያጠፋና ከመኖሪያው የሚያፈናቅል ነው። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የጋራ ተጠያቂነት አለበት። ችላ ባይነቱና ፖለቲካዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ እርምጃ አለመውሰዱ ተጠያቂ ያደርገዋል" ሲሉም አክለዋል።