የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ግምት፡ ሲቲ ነጥብ ይጥል ይሆን? አርሰናልስ?

እርግጥ ነው ቶተንሀም በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ድንቅ የሚባል አቋም እያሳየ ነው። ነገር ግን በፕሪሚዬር ሊጉ ያለበት ሁኔታ ለአሠልጣኝ ቶማስ ፍራንክ አስጊ ነው።

ባለፈው ሳምንት ከበርንሊ አቻ ሲወጣ ሜዳ ገብቶ የተመለከተው የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን ደጋፊዎቹ ተበሳጭተው ነበር ይላል።

ቶተንሀም እሑድ ማንቸስተር ሲቲን ያስተናግዳል። መሪው አርሰናል ደግሞ ወደ ሊድስ ያቀናል።

የ24ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎችን ግምት ሱተን እንዲህ አስቀምጧል።

ቅዳሜ

ብራይተን ከኤቨርተን

ጃክ ግሪሊሽ በዚህ ጨዋታ አለመኖሩ ለኤቨርተን ትልቅ ጉዳት ነው። በተቃራኒው ኢሊማን ንዲያዬ መመለሱ እና አጥቂው ባሪ ግብ ማስቆጠር መጀመሩ መልካም ዜና ነው።

ኤቨርተን በያዝነው የውድድር ዘመን ከሜዳ ውጭ ያላቸው አቋም ጥሩ የሚባለው ነው። ካለፈው ጥቅምት ጀምሮ ከሜዳቸው ውጭ አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፉት።

ወደ አሜክስ ስታድየም ሲመጡ የተሻለ ክብረ ወሰን ስላላቸው ከዚህ ጨዋታ አንድ ነገር ያገኛሉ ባይ ነኝ።

ብራይተን ምንም እንኳ ወጥ አቋም ማሳየት ባይችሉም በሜዳቸው አንድ ጊዜ ብቻ ነው የተሸነፉት። ከዚህ ጨዋታ አንድ ነጥብ ያገኛሉ ብዬ እገምታለሁ።

ግምት፡ 1-1

ሊድስ ከአርሰናል

ይህ ጨዋታ ጥሩ እንደሚሆን እጠብቃለሁ። አርሰናል ያለበትን አቋም የሚያሳየንም ይሆናል።

ሊድስ በሜዳቸው ጥሩ ሆነዋል። አሠልጣኝ ዳንኤል ፋርከ እየሠሩ ያሉት ነገር የሚደነቅ ነው። ባለፈው ሰኞ ከኤቨርተን ጋር በነበራቸው ፍልሚያ ሦስት ነጥብ አለማግኘታቸው የሚያስቆጭ ነው።

አርሰናል ባለፈው ነሐሴ ሊድስን አስተናግደው 5 ለምንም ረትተዋል። ነገር ግን አሁን በጨዋታ ጎል የማስቆጠር አቅማቸው ጥያቄ ላይ ወድቋል።

የሚኬል አርቴታ ቡድን እንደሚሸነፍ ብገምትም ጨዋታው ለመድፈኞቹ ቀላል እንደማይሆን አምናለሁ። እንደተለመደው ከቆመ ኳስ አንድ ግብ አስቆጥረው ያሸንፋሉ።

ግምት፡ 0 - 1

ዎልቭስ ከቦርንመዝ

ዎልቭስ አሁን የሚጫወቱት ለክብር ነው። እርግጥ ነው ባለፉት ጥቂት ጨዋታዎች የተሻለ መነቃቃት አሳይተዋል። ነገር ግን ከፕሪሚዬር ሊጉ መውረዳቸው ሳይታለም የተፈታ ነው።

ቦርንመዝ በ23ኛው ሳምንት ፍልሚያ በመጨረሻው ደቂቃ ባስቆጠሩት ጎል ሊቨርፑልን መርታት ችለዋል። ቢሆንም ከሜዳ ውጭ ያላቸው አቋም አስጊ ነው። ካለፈው ነሐሴ ጀምሮ አንድ ጊዜ ብቻ ነው ማሸነፍ የቻሉት።

ወደ ሞሊኒው ስታድየም ከመጡ 11 ቡድኖች መካከል ስምንቱ ድል ሲቀናቸው ዌስት ሀም ብቻ ነው የተሸነፈው።

ቦርንመዝ ግብ እንደሚያስቆጥሩ ባውቅም ግብ እንደሚገባባቸው መገመት ችላለሁ።

ግምት፡ 1 - 1

ቼልሲ ከዌስት ሀም

ቼልሲ በአውሮፓው ቻምፒዮንስ ሊግ ናፖሊን አሸንፎ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል። አሠልጣኝ ሊያም ሮዝንዮር በዚህ ድል ተቺዎቻቸውን ዝም ያሰኙ ይመስላል።

የዌስት ሀም ነገር የሚተማመኑበት አይደለም። ከጥቂት ሳምንት በፊት ተስፋ የቆረጡ ይመስሉ ነበር። ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ መነቃቃት ታይቶባቸዋል።

ቼልሲ ምናልባት በሳምንቱ አጋማሽ ወደ ጣሊያን ደርሶ መምጣቱ ያዳክመው ይሆናል የሚል ጥርጣሬ ቢኖረኝም ድል እንደሚቀናው እገምታለሁ።

ግምት፡ 2 - 1

ሊቨርፑል ከኒውካስል

ኒውካስል በአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ የሚያደርገውን ጨዋታ ለመዘገብ ወደ ፓሪስ አቅንቼ ነበር። አጀማመራቸው ደካማ የሚባል የነበረ ቢሆንም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ግን ጨዋታውን ማሸነፍ የሚችሉበትን ዕድል አባክነዋል።

ኒውካስል አማካዩ ብሩኖ ጉማሬሽ ካልተሰለፈ የማሸነፍ ዕድሉ ዝቅ ያለ መሆኑን የቁጥር መረጃዎች ያሳያሉ።

አሠልጣኝ ኤዲ ሀው አማካያቸውን ለሊቨርፑል ፍልሚያ ለማሳረፍ ይመስላል ከፒኤስጂ ጋር በነበረው ጨዋታ ያላሰለፉት። ያም ቢሆን በአንፊልድ ሊቨርፑል እንደሚያሸንፍ እገምታለሁ።

ሊቨርፑል በቻምፒዮንስ ሊጉ ቃራባቅ ላይ ግማሽ ደርዘን አስቆጥሯል። ነገር ግን ዘንድሮ አቋሙ ወጥ አለመሆኑ ግልፅ ነው።

የአርን ስሎት ቡድን ባያስተማምነኝም ኒውካስል ከሜዳቸው ውጭ ያለው አቋም ደካማ መሆኑ ግምቴ ለቀያዮቹ እንዲሆን ያደርገኛል።

ግምት፡ 2 - 1

እሑድ

አስተን ቪላ ከብሬንትፈርድ

ቲየለማንስ፣ ማጊን እና ካማራ በጉዳት ምክንያት ለቪላ አይሰለፉም። ባለፈው ሳምንት ማጊን እና ካማራ ባይኖሩም ወደ ሴይንት ጀምስ ፓርክ ተጉዘው ባለድል መሆን ችለዋል። በዚህኛውም ጨዋታ ተመሳሳይ ነገር እጠብቃለሁ።

ታሚ አብርሀም ተመልሶ አስተን ቪላን ተቀላቅሏል። ከኦሊ ዋትኪንስ ጋር በመጣመር የቪላን አጥቂ መስመር ያጠናከሩታል ብዬ አምናለሁ።

ብሬንትፈርድ ላለፉት ሳምንታት ያሳዩን ድንቅ ግስጋሴ በሾን ዳይሽ ቡድን ኖቲንግሀም ሊቆም ግድ ሆኗል።

ግምት፡ 2 - 0

ማንቸስተር ዩናይትድ ከፉልሀም

ባለፉት ወራት የምናውቀው ማንቸስተር ዩናይትድ ቢሆን ኖሮ ፉልሀም ድል ይቀናዋል ብዬ እገምት ነበር። አሁን ግን አላደርገውም።

ማይክ ካሪክ የቀያይ ሰይጣኖቹ አሠልጣኝ ሆኖ ከመጣ በኋላ የዩናይትድ ተጫዋቾች ሁኔታው ቀለል ያለላቸው ይመስላል። አብዛኞቹ ተጫዋቾች መሰለፍ የፈቀዱበት ቦታ ላይ ሆነው እየተጫወቱ ነው።

ብሩኖ ኳስ ይዞ መንቀሳቀስ ብቻ ሳይሆን መጫወት በሚፈልግበት ቦታ ነው የሚጫወተው።

ፉልሀም ሁሌም ግብ ማስቆጠር እንደሚችሉ አውቃለሁ። ነገር ግን አሁን የተነቃቃው ዩናይትድን ያሸንፋሉ ብዬ አልገምትም።

ግምት፡ 2 - 1

ኖቲንግሀም ፎረስት ከክሪስታል ፓላስ

ፎረስት ይህን ጨዋታ ካሸነፈ ከፓላስ ጋር በነጥብ እኩል ይሆናል። ፓላስ አደጋ ላይ ያለ ይመስላል። ወደ ወራጅ ቀጣናው እየተጎተተ እንደሆነ ይሰማኛል።

ይህንን ማለት ባልፈልግም አሠልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ታሪክ ቢሠሩም መልቀቅ እንዳለባቸው ይሰማኛል። ፓላስ ይህን ጨዋታ ያሸንፋል የሚል ግምት የለኝም።

ግምት፡ 1 - 0

ቶተንሀም ከማንቸስተር ሲቲ

ኧርሊንግ ሀላንድ ጎል ወደ ማስቆጠሩ ተመልሷል። በቻምፒዮንስ ሊጉ ጋላታሳራይ ላይ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል።

ማርክ ጌሂ እና አንትዋን ሴሜንዮ ለዚህ ጨዋታ ብቁ መሆናቸው ለሲቲ ትልቅ ዜና ነው።

አርሰናል ላይ ጫና እንዲበረታ ከፈለጉ ሲቲዎች የራሳቸውን ሥር መሥራት አለባቸው። ይህ ጨዋታ ለሲቲ ቀላል ባይሆንም የጌሂ መምጣት የተከላካይ መስመራቸውን ያጠናክራላቸዋል።

የቶተንሀም ደጋፊዎች ቡድናቸው እያሳየ ባለው ወቅታዊ አቋም በፍፁም ደስተኛ አይደሉም። በዚህኛውም ጨዋታ ደስታ የሚያጎናጽፋቸው ነገር ይኖራል ብዬ አላስብም።

ግምት፡ 0 - 2

ሰኞ

ሰንደርላንድ ከበርንሊ

ዎልቭስ ከሊጉ ይወርዳል ብዬ ከገምትኩ ጥቂት ሳምንታት ተቆጥረዋል። አሁን ደግሞ ተራው የበርንሊ ይመስላል።

በርንሊ አቻ የሚወጣቸውን ጨዋታዎችን ማሸነፍ መቻል አለበት። ባለፈው ሳምንት ከቶተንሀም ጋር በነበራቸው ጨዋታ ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባቸው ግብ ነው አቻ የወጡት።

ጥቋቁር ድመቶቹ ሰንደርላንዶች አምበላቸው ግናኒት ዣካን በጉዳት ቢያጡም በሜዳቸው ቀላል የሚባሉ አይደሉም።

ግምት፡ 1-0