ፈረንሳይ ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም የትዳር መብት እንዳልሆነ የሚደነግግ ሕግ ልታወጣ ነው

ፈረንሳይ ትዳር ውስጥ ግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም ግዴታ የሚያደርገውን "የትዳር መብት" የተሰኘ ሐሳብ የሚያስቀር ሕግ ልታወጣ ነው።

የአገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት ረቡዕ ዕለት ያጸደቀው ረቂቅ ሕግ፤ በፈረንሳይ የፍትሐ ብሔር ሕግ ውስጥ ይህንን በግልጽ የሚደነግግ አንቀጽ አካትቷል። የተሻሻለው ሕግ ላይ የሰፈረው አንቀጽ፤ በሰዎች መካከል የሚፈጸም "አብሮ የመኖር ኅብረት"፤ "የግብረ ሥጋ ግንኙነት የመፈጸም ግዴታን" የሚጥል እንዳልሆነ ደንግጓል።

የዚህ ረቂቅ ሕግ መውጣት፤ ፍቺ ለመፈጸም ፍርድ ቤት የሚቀርቡ ጥንዶች የትዳር አጋራቸው ወሲባዊ ግንኙነት ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆናቸው ጥፋት እንደሆነ በመጥቀስ እንዳይከራከሩ ያደርጋል። ይህም ቢሆን ግን ሕጉ በፍርድ ቤቶች የውሳኔ አሰጣጥ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ተብሎ አይጠበቅም።

ድንጋጌው መውጣቱን የሚደግፉ ሕግ አውጪዎች ግን በትዳር ውስጥ የሚፈጸምን የመድፈር ወንጀል ለመከላከል እና ስለዚህ አይነቱ ወሲባዊ ጥቃት ግንዛቤ ለመፍጠር ይረዳል የሚል ተስፋ ሰንቀዋል።

የሕጉ አቅራቢ የሆኑት የግሪን ፓርቲ ተወካዩ የፓርላማ አባል ማሪ ቻርሎት ጋሪን፤ "ይህ መብት ወይም ግዴታ እንዲቀጥል በመፍቀዳችን ትዳር ውስጥ ባል በሚስቱ ላይ የበላይነት እንዲኖረው እና ጥቃት እንዲያደርስ በጋራ ፈቃድ እየሰጠን ነው" ብለዋል።

"ትዳር፤ ለወሲብ የሚሰጥ ፈቃድ ፍጹም እና እድሜ ልክ የሚጸና እንደሆነ የሚቆጠርበት ዓለም ሊሆን አይችልም" ሲሉም ከዚህ ድንጋጌ ጀርባ ያለውን አመክንዮ አብራርተዋል።

የፈረንሳይ ሕግ ከዚህ ቀደምም ቢሆን የግብረ ስጋ ግንኙነት መፈጸም "የትዳር መብት" እንደሆነ የሚደነግግ ባይሆንም የአሁኑ ረቂቅ ሕግ መውጣት ጉዳዩ ግዴታ አለመሆኑን በግልጽ የሚያስቀምጥ ይሆናል።

በአሁኑ ሰዓት የፈረንሳይ የፍትሐ ብሔር የትዳር ግዴታዎች ብሎ ከሚዘረዝራቸው ጉዳዮች መካካል "መከባበር፣ ታማኝነት፣ ድጋፍ እና መረዳዳት" የሚሉት ይገኙበታል። ትዳር የሚመሰርቱ ጥንዶች "ለአብሮ መኖር" ቃል እንደሚገቡም ይገልጻል።

የግብረ ስጋ ግንኙነት "የትዳር መብት" ስለመሆኑ በየትኛውም የሕጉ ክፍል ላይ አልተደነገገም። ወሲብን ግዴታ የሚያደርገው አስተሳሰብ መነሻው በመካከለኛው ዘመን የተጻፈ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ነው።

ዘመናዊ የፍቺ ክሶችን የሚመለከቱ ዳኞችም ከጊዜ ወደ ጊዜ "አብሮ የመኖር ኅብረት" የሚለው ሐሳብ የግብረ ስጋ ግንኙነትንም እንደሚያካትት አድርገው በሰፊው ሲተረጉሙት ቆይተዋል።

በአውሮፓውያኑ 2019 ለበርካታ ዓመታት ከባለቤቷ ጋር ወሲብ ከመፈጸም የተቆጠበች አንዲት ሴት ጉዳይ ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ጉዳዩ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በወቅቱ ፍርድ ቤቱ ግለሰቧ ትዳሩ እንዲፈርስ ምክንያት የሆነውን ጥፋት እንደፈጸመች የሚያመለክት ፍርድ ሰጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ ግለሰቧ ጉዳዩን ወደ አውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ወስዳዋለች። ፍርድ ቤቱም፤ ፈረንሳይ የግብረ ስጋ ግንኙነት ለመፈጸም አለመፍቀድን እንደ ጥፋት መቁጠሯን አውግዟል።

ይህ ውሳኔ በሴቶች መብት ተከራካሪዎች (ፌሚኒስቶች) ዘንድ እንደ ትልቅ እርምጃ ተቆጥሯል።

የአውሮፓ የሰብአዊ መብቶች ፍርድ ቤት ያስተላለፈው ውሳኔ፤ የትዳር ፍቺን የሚመለከቱ የፈረንሳይ ዳኞች ተመሳሳይ ውሳኔ እንዳይሰጡ የሚያደርግ ነው።

ምንም እንኳ በፍርድ ቤቶች ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ እምብዛም ቢሆንም፤ አሁን የተዘጋጀው ረቂቅ ይህንን ሀሳብ በሕግ ለማስፈር ያለመ ነው።

የሴቶች መብት ተሟጋቾች፤ ሚስቶች ከባሎቻቸው ጋር ወሲብ ለመፈጸም የመስማማት "ግዴታ" አለባቸው የሚለው አሁንም ድረስ ማህበረሰቡ ውስጥ ጽንቶ የሚታይ እና ለክርክር መቅረብ ያለበት ጉዳይ እንደሆነ ይገልጻሉ።