የናዚ መሪዎችን የአእምሮ ጤና እንዲፈትሹ የተሾሙት ዶክተር አሳዛኝ ታሪክ

የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ያስከተለውን ውድመት መረዳት ለበርካቶች ቀላል አልነበረም። ከ80 ዓመታት በፊት ውድመቱን ለመገንዘብ ጥረቶች ሲደረጉ ነበር።

ናዚዎች አይሁዳውያንን፣ የሮማኒ ሕዝቦችን፣ የፖለቲካ ተቀናቃኞቻቸውን እንዲሁም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪዎችን የያዙባቸው የግድጅ ማቆያዎች ይፋ ወጥተዋል።

በጀርመን ኑረንበር ከተማ ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ፍርድ ቤት ሲቋቋም፤ እንዴት ያ ሁሉ ጭካኔ ተፈጸመ? ለሚለው ጥያቄ መልስ እንደሚሰጥ ሲጠበቅ ነበር።

ፍርድ ቤቱ ከአውሮፓውያኑ ጥቅምት 20/1945 አንስቶ የናዚ መሪዎችን ክስ መመልከት ጀመረ።

ብዙ የሕግ እና ቴክኒክ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ነበረባቸው። ከእነዚህ መካከል ተከሳሾቹ ላይ ምን ዓይነት ክሶች ይቅረቡ? የሚለው ይጠቀሳል።

ማን ይዳኛቸው? ምን ዓይነት ሕጋዊ አካሄድ ይተግበር? የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል።

ዋነኛው ጥያቄ የነበረው ግን እነዚህ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ለመቆም በሥነ ልቦና ዝግጁ ናቸው ወይ? የሚለው ነበር።

የአእምሮ ጤናቸውን ሁኔታ እንዲበይኑ የተመረጡት አሜሪካዊው የሥነ ልበና ባለሙያ ዶ/ር ዳግላስ ኤም ኬሊ ናቸው።

ያልጎለበተው የአእምሮ ጤና ምርምር

የዓለም አቀፉ የብይን ሰጪዎች ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ካርሎስ አያላ ኮራዎ "አንድ ሰው የአእምሮ ሕመም ወይም መቃወስ ገጥሞት ያለ ፈቃዱ ድርጊት ከፈጸመ ተጠያቂ እንዳይሆን ወይም ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ እንዳይሆን ሕጉ ይደነግጋል" ይላሉ።

ዶ/ር ዳግላስ በካሊፎርንያ ዩኒቨርስቲ የሥነ ልቦና ተመራማሪ ነበሩ። የናዚ አመራሮችን የአእምሮ ጤና ሲበይኑ የፍርድ ሒደቱ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድር ይታወቃል።

በአሜሪካ መከላከያ ውስጥ እስከ ሉተነንት ኮሎኔልነት ድረስ አገልግለዋል። በአውሮፓ በጦርነት የተደናገጡ ወይም የተዳከሙ የኅብረቱ ኃይሎች ወታደሮችን አክመዋል።

ያኔ ያደገሩት ሕክምና በዘመናዊ የሥነ ልቦና ምርምር ከአስደንጋጭ ክስተት በኋላ የሚፈጠር የአእምሮ ቀውስ (post-traumatic stress disorder ወይም በምጽሐረ ቃል PTSD) ተብሎ ይታወቃል።

ዶ/ር ዳግላስ ስምንት ወራት ከናዚ መሪዎች ጋር አሳልፈዋል። የናዚ መሪዎች ተይዘው የነበረው በሉግዘምበርግ ሆቴል ውስጥ ነበር።

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ጃክ ኢል-ሀይ እንደሚሉት ዶ/ር ዳግላስ "የተለያዩ የሥነ ልቦና ስልቶችን" ተጠቅመዋል።

ጋዜጠኛው 'The Nazi and the Psychiatrist' የሚል መጽሐፍ ያሳተሙ ሲሆን፤ ታሪኩ ወደ ፊልምነት ተለውጧል።

ጋዜጠኛው 15 ካርቶን ሙሉ ሰነዶች እና በዶ/ር ዳግላስ የተጻፈ ሪፖርት ተመልክተዋል። ዶክተሩ ናዚዎች ላይ ያደረጉትን ጥናት ሲከታተሉ ለ10 ዓመታት ከዶክተሩ ቤተሰቦች ጋር አሳልፈዋል።

ዶ/ር ዳግላስ ለተከሳሾቹ ቃለ ምልልስ አድርገዋል። የሥነ ልቦና ፈተና በመስጠትም የጤናቸውን ሁኔታ ፈትሸዋል።

ከተሰጣቸው ፈተና አንዱ ረቂቅ ሥዕል በመጠቀም ያዩትን እንዲገልጹ የተደረገበት (Rorschach inkblot test) ነው።

ሌላኛው ፈተና ፎቶዎች እና ምሥሎችን በመጠቀም ተከሳሾቹ ታሪክ እንዲናገሩ ማድረግ (Thematic Perception Test) ነው።

የሰዎች የማሰላሰል ብቃት የሚመዘንበት (IQ test) የሰጧቸው ሲሆን፤ ተከሳሾቹ አማካይ ወይም ከአማካይ በላይ የማሰላሰል አቅም እንዳላቸው የፈተናው ውጤት ጠቁሟል።

ከእሳት ጋር ጨዋታ

ዶ/ር ዳግላስ ከተከሳሾቹ መካከል የበለጠ ትኩረት የሰጡት ኸርማን ጎሪንግ ለተባለው ሰው ነው።

ኸርመን የአዶልፍ ሒትለርን ቦታ ይተካል ተብሎ የታሰበ የጀርመን አየር ኃይል 'ዘ ሉፍትዌፍ' ኮማንደር ነበር።

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ጃክ ኢል-ሀይ እንደሚሉት ኸርማን ከተጠርጣሪዎቹ በአጠቃላይ ከፍተኛ አመራር ላይ የነበረው ነው።

"ሁለቱም የላቀ የማሰላሰል አቅም ያላቸው፣ ተወዳጅ እና በራሳቸው ዛቢያ ብቻ የሚሽከረከሩ ሰዎች ስለሆነ ተቀራርበዋል" ይላሉ።

ዶ/ር ዳግላስ ኸርበርት ምን ያህል ጨካኝ ሰው እንደሆነ አልጠፋቸውም። በጦርነቱ ወቅት ያስተላለፈውን የክፋት ውሳኔንም ያውቃሉ።

ሆኖም ግን ሁለቱ ግለሰቦች እርስ በርስ በመከባበር ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት መሥርተዋል።

ዶክተሩ "ደስ የሚል ሰው ለመሆን ሲፈልግ ደስ የሚል ሰው ይሆናል። በጣም ጥልቅ የማሰላሰል ችሎታ አለው። ቀልድ አዋቂም ነው" ሲሉ ስለ ኸርበርት ጽፈዋል።

ይህ ጽሑፍ በአሜሪካ የሆሎኮስት ሙዚየም ውስጥ ይገኛል።

ዶክተሩ "በየቀኑ የታሰረበት ክፍል ስገባ ፈገግ ብሎ ቆሞ ሰላም ይለኛል። ከጨበጠኝ በኋላ ወንበሩ ይዞልኝ ይመለሳል። 'ዶክተር እንደምን አደርክ፤ ልትጎበኘኝ ስለመጣህ ደስ ብሎኛል፤ እባክህ ተቀመጥ' ይለኛል። ከዚያም ከጎኔ ተቀምጦ ጥያቄዎቼን ይመልሳል" ሲሉም ጽፈዋል።

ዶ/ር ዳግላስ የኸርማንን አእምሯዊ እና አካላዊ ጤና ፈትሸዋል።

ኸርማን ከልክ ያለፈ ውፍረቱን እንዲቀንስ እና ከኮዴይን ሱስ እንዲላቀቅ ለማድረግ ዶክተሩ ሞክረዋል።

ለኸርማን የአመጋገብ ሥርዓት ነድፈው ከሱስ ለማላቀቅ ሞክረዋል። በጦርነቱ ወቅት ከደረሰበት የአካል ጉዳት ለማገገም ከሚወስደው ኮዴይን ሱስ ለማስወጣት የነደፉት ሕክምና ነበር።

በሁለቱ መካከል የተፈጠረው ጓደኝነት "ሙያዊ ቀይ መስመርን" ያለፈ ነው የሚሉ ባለሙያዎች አሉ። ዶክተሩ ያላቸውን ተዓማኒነት እንደሸረሸረም ይገልጻሉ።

አሜሪካዊው ጋዜጠኛ ጃክ ኢል-ሀይ "ዶክተሩ በኸርማን እና በባለቤቱ ኤሚ መካከል ደብዳቤ ያመላልሱ ነበር። ይሄንን ፍርድ ቤቱ አልፈቃደላቸውም" ይላሉ ።

ኸርማን እሱ እና ባለቤቱ ከሞቱ ዶክተሩ ልጁን አሜሪካ ወስደው እንዲያሳድጉለትም ጠይቋል። የዶክተሩ ባለቤት ግን ለዚህ ፈቃደኛ አልሆነችም ነበር።

አስፈሪው የምርምር ውጤት

ዶ/ር ዳግላስ በምርመራቸው መጀመሪያ ላይ የናዚ መሪዎች በአእምሮ ሕመም ምክንያት እልቂት መፈጸማቸውን ያምኑ ነበር።

ሆኖም ግን የናዚ አመራሮች የአእምሮ ሕመም እንደሌለባቸው በማረጋገጥ "ከድርጊታቸው ጀርባ ያለው የአእምሮ ጤና እክል እንዳልሆነ" መወሰናቸውን ጋዜጠኛው ይናገራሉ።

"የምርመራቸው ውጤት እንደ ናዚዎች ያሉ ሰዎች በመካከላችን፣ በሁሉም አገር እንደሚኖሩ ምልከታ የሰጠ ነበር" ይላሉ።

"ሰዎቹ መደበኛ ሰዎች ነበሩ። ግን በጭካኔ እና ቢሮክራሲ ታውረዋል። በየትኛውም አገር ከትልቅ ጠረጴዛ ጀርባ የምናገኛቸው ዓይነት ሰዎች ናቸው" ሲሉም አክለዋል።

አሜሪካዊው የሥነ ልቦና ተመራማሪ ጆኤል ዲማስዴል 'Anatomy of Malice: The Enigma of the War Criminals' በተባለው የጦር ወንጀለኞችን በተመለከተ መጽሐፋቻቸው እንዳሰፈሩት የናዚ መሪዎች የአእምሮ ጤና እክል እንደሌላቸው ዶ/ር ዳግላስ አረጋግጠዋል።

በአውሮፓውያኑ 1946 ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ስለ ፋሺዝም አስጊነት ትምህርት ሲሰጡ ቆይተዋል።

በወቅቱ የዘር መድልዎን የሚደግፍ ፖሊሲ የሚያራምዱ ፖለቲከኞች በሥልጣን ላይ ነበሩ።

ዶ/ር ዳግላስ ከናዚ መሪዎች ጋር ያደረጉት ቆይታ ሕይወታቸውን ለውጦታል። ስለ አእምሮ ጤና ሕክምና ያለው ዕሳቤ እንዲለወጥም አድርጓል።

ጋዜጠኛው እንደሚሉት፤ ወንጀለኞችን በሥነ ልቦና ሕክምና ማዳን እንደማይቻል ለማወቅ ያስቻለ ክስተት ነው።

"እነዚህ ሰዎች ጤነኛ ከነበሩ ድርጊታቸውን ለምን ፈጸሙ? የሚለው ጥያቄ እንዴት ምላሽ ያገኛል። ዶክተሩ የመጨረሻ የሕይወታቸውን ክፍል ያሳለፉት ስለ ወንጀለኞች ሥነ ልቦና በመመራመር ነው" ይላሉ ጋዜጠኛው።

ዶ/ር ዳግላስ ከኸርማን ጋር ባሳለፉት ጊዜ ምክንያት የአልኮል መጠጥ ሱሰኛ እንደሆኑ የሚያምኑ አሉ።

ከናዚ አመራሮች ጋር የነበራቸውን ቆይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ለድባቴ ተጋልጠዋል።

በአውሮፓውያኑ ጥር 1/1958 ከባለቤታቸው ጋር ኃይለኛ ንትርክ ውስጥ ገቡ። በድንገት ሳይናይድ መርዝ ወስደውም ወዲያው ሕይወታቸው አለፈ።

ዶክተሩ ከመሞታቸው ከ12 ዓመታት በፊት ኸርማንም በተመሳሳይ መንገድ ራሱን አጥፍቷል። ኸርማን ራሱን ያጠፋው ሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች ፍርድ ሊሰጥበት ሰዓታት ሲቀሩት ነበር።