በናዚ አገዛዝ ወቅት ጠፍቶ የነበረን ሀብት ይዞ የተገኘው አሮጌ ሻንጣ

የሁሉም መጀመሪያ የሆነው አልጋ ስር ተደብቆ የተገኘው ሻንጣ ነው። የአንቶኒ ኤስቶን አባት ፒተር በአውሮፓውያኑ 2009 በድንገት ሕይወታቸው አለፈ።

አንቶኒ አስፈላጊውን የሕግ ሂደት ለመወጣት ተፍ ተፍ ሲል ሐምፕሻየር በሚገኘው ቤታቸው ውስጥ ቡናማ ሻንጣ አገኘ።

በውስጡ አዳዲስ የጀርመን ገንዘብ፣ የፎቶ አልበሞች፣ የሕይወታቸውን የተለያየ ምዕራፍ የሚያትቱ ማስታወሻዎች፣ የልደት ምስክር ወረቀት ይዟል።

ፒተር ሮድሪክ ኤስቶን ራሳቸውን ኩሩ "እንግሊዛዊ" አድርገው ነው የሚቆጥሩት።

በእርግጥ ተወልደው ያደጉት በበርሊን ከሀብታም ቤተሰብ እንደተገኘው ፒተር ሃንስ ሩዶልፍ አይዝነር፣ ከጀርመን ጦርነት በፊት ነው።

አባቱ ከየት እንደ መጡ ጥቂት ዕውቀት የነበረው አንቶኒ፣ ሻንጣው ምንም የማያውቀውን የቀደመ የቤተሰቡ ሕይወት ላይ ብርሃን አብርቶለታል።

ሻንጣው በናዚ አገዛዝ የተዘረፈውን የኪነ ጥበብ ሥራ እና ንብረት፣ በአይሁዶች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ፈጅት (ሆሎኮስት) የተጎዳው ቤተሰብን፣ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ፓውንድ የሚገመት የጠፋ ሀብት እና ቅርስ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ ነበር።

በሻንጣው ውስጥ የተገኙት ጥቁር እና ነጭ ፎቶግራፎች የፒተርን የልጅነት ሕይወት ይናገራሉ።

ፎቶዎቹ አንቶኒ ካደገበት በተለየ መርሴዲስ፣ በአገልጋዮች የተሞሉ ቤቶችን፣ በመላዕክት ምሥል ያጌጡ ደረጃዎችን የሚታይባቸው ነበሩ።

በጣም የሚያስገርመው አንዱ ፎቶ ላይ የ12 ዓመቱ ፒተር አይዝነር ከጓደኞቹ ጋር ፈገግ ብሎ፣ የናዚ ሰንደቅ ዓላማን ከሩቅ ሲውለበለብ ይታያል።

አንቶኒ "ካለፈው ዘመን አሁንን ለመጨበጥ የተዘረጋ እጅ እንደሆነ ተሰማኝ" ብሏል።

አባቱ ዝምተኛ እና ቁም ነገረኛ ሰው ነበሩ ሲል ይገልጻቸዋል። ስለ ልጅነታቸው ከመናገር የተቆጠቡ እና ንግግራቸው ላይ ስለሚሰማው ትንሽ የጀርመንኛ ዘዬ ሲጠየቁ ማድፈንፈን የሚመርጡ ነበሩ።

አንቶኒ "[እሱ] በእውነቱ እንደሌሎች ሰዎች እንዳልሆነ የሚጠቁሙ ፍንጮች ነበሩ…ዓለም በእርሱ ዙሪያ ጨለማ ነበረች" ብሏል።

እጅግ በጣም ብዙ ሀብት

ስለ አንቶኒ የቤተሰብ ታሪክ ቀጣዩ ትልቅ ፍንጭ የመጣው ከሥነ ጥበብ ሥራ ነው።

ጀርመንኛ አቀላጥፋ የምትናገር ጓደኛውን በሻንጣው ውስጥ ከሚገኙት ሰነዶች መካከል ምልክት የተደረገባቸውን ሃህንስ ዌርኬ ስለ ተባለ ኩባንያ እንድትፈልግለት ጠየቃት።

ድረገጾች ላይ ፈልጋ ካገኘች በኋላ ለአንቶኒ በአንድ የንግድ ድርጅት ባለቤትነት የተያዙ የሚመስሉ የሥዕል ፎቶግራፍ ላከችለት።

በምሥሉ ላይ የሚቀልጥ ብረት ይታያል። በዙሪያው የተሰበሰቡ ሠራተኞች ፊት ላይ የሚቀልጠው ብረት ብርሃኑን ረጭቶባቸዋል።

ጀርመን ለዓመታት ወደ ዘለቀው አስቀያሚ ወራት ከመዝለቋ በፊት ያለውን የሚያሳይ የጥንካሬ እና የኃይል አመልካች ምሥል ነው።

እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1910 ሀንስ ባሉሼርክ በሚባል ሠዓሊ ባለቤትነት ተይዞ የነበረ እና ምናልባትም የሃንሼ ዌርኬ የብረታ ብረት ንግድን በመካከለኛው አውሮፓ ከሚገኙ በጣም ግዙፍ የሆነውን የቴክኖሎጂ ኩባንያ እንዲገነባ በረዳው ሃይንሪች አይዝነር እንዲሳል የተደረገ ሊሆን ይችላል።

በሻንጣው ውስጥ ያሉት ሰነዶች ይህ የአንቶኒ ቅድመ አያት መሆናቸውን ያሳያሉ።

የተደረጉ ተጨማሪ ጥናቶች እንዳረጋገጡት በ20ኛው ክፍለ ዘመን መባቻ ላይ ሄንሪች በጀርመን ውስጥ ካሉት ሀብታም ነጋዴዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

በዚህ ዘመን ካለ ባለ ብዙ ቢሊየነር ጋር የሚስተካከል ሀብት ነበራቸው።

ኩባንያው በጀርመን፣ በፖላንድ እና በሩሲያ የቱቦ ብረቶችን ያመርት ነበር።

ሃይንሪሽ እና ባለቤቱ ኦልጋ በበርሊን እና በዙሪያዋ በከተማው መሃል ላይ የሚገኘውን አስደናቂ ባለ ስድስት ፎቅ በእምነበረድ የተንቆጠቆጠ ሕንጻን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች አፍርተዋል።

በአውረሮፓውያኑ 1900ዎቹ መጀመሪያ ላይ የተነሳ ፎቶግራፍ አንድ ትንሽ ቦርጭ እና ጢም ያለውን ሰው ያሳያል። ሄንሪሽ ጥቁር ሱፍ ለብሶ፣ ኦልጋ ከአጠገቡ አነስተኛ ዘውድ ደፍታ ተቀምጣለች።

በ1918 ሲሞት፣ ሄንሪሽ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በቅርቡ ለተመለሰው ለልጁ ሩዶልፍ የኩባንያውን እና የግል ሀብቱን አክሲዮኖችን አስተላለፈ።

ጦርነቱ ከፍተኛ የሰው ውድመት ቢያስከትልም ሀንሼ ዌርኬ በዚያ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ሀብት አከማችቶ ነበር።

ይህም የጀርመን ጦር የብረት ፍላጎትን ማሟላት አስችሏል።

ሩዶልፍ እና ቤተሰቡ ከጦርነቱ በኋላ አገራቸውን ያጎሳቆለውን ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ትርምስ በተሳካ ሁኔታ ተቋቁመዋል።

ሆኖም ግን በጥቂት ዓመታት ውስጥ ሁሉም ነገር እንደ ጉም በንኖ ጠፋ።

ሁሉም ነገር ተለወጠ

አንቶኒ በሻንጣው ውስጥ ባገኛቸው ማስታወሻዎች ላይ ፒተር በወላጆቹ መካከል ስለ ናዚ ማስፈራሪያ የሰማቸውን የሹክሹክታ ንግግሮች አስፍሯል።

ጀርመን እና አጋሮቿ በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ለመሸነፋቸው እና ይህንን ተከትሎ ለመጣው የኢኮኖሚ ድቀት አይሁዶች በአዶልፍ ሂትለር ተከስሰዋል።

ሩዶልፍ አይዝነር ኩባንያውን ለናዚ አገዛዝ ከጠቀመ ምንም እንደማይነካው ያምን ነበር።

ለተወሰነ ጊዜ ይህ ተግባራዊ የሚሆን ቢመስልም ፀረ አይሁድ ሕጎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ጠንካራ የከረሩ እየሆኑ ሲመጡ እና በዙሪያው የሚያያቸው በደሎች እየባሱ ሲሄዱ እንደገና ለማጤን ተገደደ።

በመጋቢት ወር 1938 መንግሥት ሀንስ ዌርኬን ፈልጎ መጣ።

በባለሥልጣናት ከፍተኛ ጫና የአይሁዶች ንብረት የሆነው ኩባንያ በወረደ ዋጋ የናዚ ደጋፊ ለነበረው የማንነስማን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ዊልሄልም ዛንገን ኩባንያ እንዲሸጥ ተደረገ።

የአይሁዶች የንግድ ድርጅቶች ዘረፋን በሚመለከት መጽሐፍ የጻፈው ዴቪድ ዴ ጆንግ "የተዘረፉት ሀብት እና ንብረቶቹ ዛሬ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው መገመት ፈጽሞ የማይቻል ነገር ነው" ብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2000 ማንነስማን ከ100 ቢሊየን ፓውንድ በላይ በሆነ ስምምነት ለቮዳፎን ተሽጧል።

ይህም በወቅቱ የተመዘገበ ትልቁ የንግድ ሽያጭ ነበር።

በዚያ ሽያጭ ውስጥ ከተካተቱት የኢንዱስትሪ ንብረቶች ውስጥ ቢያንስ የተወሰነው ክፍል በአንድ ወቅት የኢዝነር የንግድ ኢምፓየር አካል ነበር።

የሀንሼ ዌርኬ መፍረስ እና የኩባንያው አባላት መታሰራቸው አይዝነሮች መሸሸ እንደሚያስፈልጋቸው እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።

በ1937 ግን ማንኛውም አይሁዳዊ ጀርመንን ለቅቆ ለመውጣት የሚፈልግ ከሆነ ያለውን ንብረት 92 በመቶ ለመንግሥት አሳልፎ እንዲሰጥ የሚያስገድድ የግብር ሕግ ወጣ።

በዚህ ግብር የተነሳ አይዝነሮች ከሀብታቸው የተረፈውን ለማጣት ተገደዱ።

ስምምነቱ

በዚህ ቀውስ ውስጥ በበርሊን መዛግብት ውስጥ እንደተመዘገበው የኢኮኖሚክስ ባለሙያ እና የታክስ አማካሪ ማርቲን ሃርቲግ የተባለ ሰው በአይዝነር ሕይወት ውስጥ ትልቅ ቦታ ማግኘት ጀመረ።

በ1930ዎቹ በአይዝነር ቤት እንግዳ መቀበያ መዝገብ ውስጥ ስሙ በተደጋጋሚ የተገኘ ሲሆን፣ ስለ መልካም መስተንግዷቸው አመስግኗቸዋል።

አይሁዳዊ ያልሆኑት ሄር ሃርቲግ ንብረቶቻቸው በናዚ የተወረሰባቸውን ቤተሰቦች መፍትሔ የሰጣቸው ይመስላል።

በተለይም የያዙዋቸውን በርካታ ንብረቶች አይሁዶችን ላይ ትኩረት ከሚያደርጉ ሕጎች ለመጠበቅ ዋና ዋና የግል ሀብታቸውን ለእሱ ፈርመዋል።

አንቶኒ አያቶቹ ሃርቲግ አንድ ቀን ንብረቶቹን እንደሚመልስላቸው አምነው ነበር ይላል።

ተሳስተዋል። ይልቁንስ የአይዝነር ንብረቶችን በቋሚነት በራሱ ስም አዘዋውሯል።

ቢቢሲ የመጀመሪያዎቹን የሽያጭ ሰነዶች ቅጂዎች በጀርመን የፌዴራል መዛግብት አግኝቶ ለሦስት ገለልተኛ ባለሙያዎች አሳይቷል።

ሦስቱም ይህ ስምምነት "የግዳጅ ሽያጭ" ማስረጃ ነው ብለው ደምድመዋል።

የግዳጅ ሽያጭ የሚለው አገላለጽ በናዚዎች ዘመን የአይሁድ ንብረት መውረስን ለመግለጽ በሰፊው ጥቅም ላይ የዋለ ነው።

ለዘመናት የገነቡትን ሀብት ቢያጡም የአንቶኒ አያቶች እና አባት በ1938 ከጀርመን ለማምለጥ ቻሉ።

አንቶኒ በሻንጣ ውስጥ ያገኛቸው የባቡር ትኬቶች፣ የሻንጣዎች መለያዎች እና የሆቴል በራሪ ወረቀቶች ጉዟቸው ከየት ወደ የት እንደነበር መመልከት እንዲችል አድርጎታል።

በሐምሌ 1939 ወደ እንግሊዝ ከተጓዙት የመጨረሻ መርከቦች አንዱን ከመያዛቸው በፊት፣ ቤተሰቡ ከናዚዎች አንድ እርምጃ በመቅደም ወደ ቼኮዝሎቫኪያ ከዚያም ወደ ፖላንድ ሄደዋል።

በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ቢያጡም ዕድለኛ ከሆኑት የኢዝነር ቤተሰብ አባላት መካከል ነበሩ።

አብዛኞቹ ዘመዶቻቸው በማጎሪያ ካምፖች እንዲቆዩ ተደርገው ተገድለዋል።

ሩዶልፍ ራሱ አብዛኛውን ጦርነቱን ካሳለፈ በኋላ በ1945 ሕይወቱ አልፏል።

ከሀርቲጎች ጋር መገናኘት

የሚቀጥለው የአንቶኒ እርምጃ የአይዝነር ቤተሰብ እና ማርቲን ሃርትጊን ሀብት ምን እንደደረሰ ማወቅ ነበር።

በትክክል ምን እንደተሰረቀ፣ እንዴት እንደተለወጠ እና ዛሬ የት እንዳለ ለማወቅ ልምድ ያላትን መርማሪ፣ ያና ስላቮቫን ቀጠረ።

በሳምንታት ጊዜ ውስጥ ስለ ዘመዶቹ፣ ንብረቶቻቸው እና የንብረቶቻቸውን ዝርዝሮች ጨምሮ ብዙ ሰነዶችን አገኘች።

አንቶኒ በጉዞው መጀመሪያ ላይ ያየውን ሥዕል ማግኘት ችላለች። አይዘንዋልዝወርክ በበርሊን በሚገኘው የብሮን ሙዚየም ስብስብ ውስጥ ነበር።

የጥበብ ሥራውን ለማስመለስ ቀደም ሲል የተደረገው ሙከራ ችግር አጋጥሞት ነበር።

አንቶኒ ሽያጩ ከናዚ ጭቆና ጋር የተያያዘ መሆኑን ማረጋገጥ ይችል ይሆን? ወደ ሙዚየሙ ከመግባቱ በፊት በሕጋዊ መንገድ በበርካታ ሰዎች እጅ ስላለመግባቱ እንዴት ማወቅ ይችላል?

ያና በሙዚየሙ እና በኪነጥበብ ሥራዎች ሻጭ መካከል የተደረገ የደብዳቤ ልውውጥ ማግኘቷ ትልቅ ስኬት አምጥቷል።

የጥበብ ሥራዎችን የሚሸጠው ግለሰብ ሥዕሉን የሸጠው በአውሮፓውያኑ 1938 በማርቲን ሃርቲግ ቁጥጥር ስር የነበረው ንብረት ከሆነው የኢዝነርስ የቀድሞ ቤተሰብ ቤት ነው።

ሃርቲግ ቀሪ ሕይወቱን በዚያ አሳልፏል።

በ1965 ከመሞቱ በፊት በበርሊን መፈራረስ ወቅት ሕንፃውን በጥሩ ሁኔታ አሳድሶታል።

ሃርቲግ ከሞተ በኋላ ንብረቱ አሁን በ80ዎቹ ውስጥ ላሉት ሴት ልጁ ተላለፈ።

እኚህ ሴት ደግሞ በአውሮፓውያኑ 2014 ቤቱን ለልጆቻቸው በስጦታ አስተላልፈው ወደ ገጠር መኖሪያቸው ሄደዋል።

በዚያም አንቶኒ እና ያናን ለማግኘት ፈቃደኛ ሆኑ።

የማርቲን ሃርቲግ ሴት ልጅ አንቶኒ እና ያና ከጠበቁት በጣም የተለየ ታሪክ ነበራቸው።

አባቷ ሁልጊዜ ናዚዎችን ይቃወሙ እንደነበር እና ታላቅ ጓደኞቼ ሲሉ የገለጿቸውን አይዝነሮችን ከሆሎኮስት ለማዳን እንደረዱ ነገሯቸው።

ቤተሰቡን "እዚህ መቆየት አትችሉም፣ ወደ ብሪታንያ፣ ወደ ለንደን ሂዱ" በማለት እንዲሸሹ እንዳሳመኗቸው ጨምረው አስረዱ።

አባታቸው ሥዕሎችን ከፍሬሞቹ ውስጥ በማውጣት በልብስ ውስጥ በመደበቅ ከጀርመን በድብቅ እንዲያስወጡ እንደረዷቸው እንደነገሯት አጫወቷቸው።

ከአይዝነር በ1938 ስለወሰዱት ንብረት ሲጠይቁም በሕጋዊ መንገድ የተገዙ ናቸው ሲሉ መለሱ።

"አባቴ በሕጋዊ መንገድ ሁለት ቤቶችን ገዛ" ካሉ በኋላ "ሁልጊዜ በጣም ትክክል ለመሆን ይጥሩ ነበር" ሲሉ አክለዋል።

ሌሎች የቤተሰቡ አባላት ግን ቅድመ አያታቸው አይዝነርስን ሀብት ሊወስድ እንደሚችል በመናገር የበለጠ ግልጽ ነበሩ።

የማርቲን ሃርቲግ የልጅ ልጅ ቪንሰንት በ20ዎቹ ዕድሜው ላይ ያለ እና አናጺ ለመሆን እየተማረ ነው።

የአንቶኒ አያቶች በአንድ ወቅት ይኖሩበት የነበረው ቤታቸው ያለፈ ጊዜ የማይመች ታሪክ እንደነበረው እንደተሰማው ተናግሯል።

"በእርግጥ የሆነ ጊዜ ላይ ጉጉት ነበረኝ፤ እኛ እንደ ቤተሰብ በዚህ ጥሩ ቦታ የምንኖረው ከየት አምጥተን ነው" ሲል ተናግሯል።

"ሁኔታዎች እንዴት ነበሩ? የሚለውን ጥያቄ ራሴን ጠይቄያለሁ።"

ቪንሰንት የአንቶኒ አይሁድ ቤተሰብ የደረሰባቸውን ካወቀ በኋላ አይዝነሮች ንብረታቸውን ለቅድመ አያቱ ሲያስረክቡ ብዙም ምርጫ እንዳልነበራቸው ተሰምቶታል።

'ስለ ገንዘቡ አይደለም'

አንቶኒ የአያቶቹ ንብረት ለማስመለስ ክስ የመመሥረት ፍላጎት የለውም።

አያቱ ሂልዴጋርድ፣ የሩዶልፍ ባለቤት በ1950ዎቹ ውስጥ ለማስመለስ ሞክረዋል። ግን በሃርቲግ የሕግ ሰዎች ውድቅ ሆኗል።

በቀድሞ ምዕራብ ጀርመን በናዚ ጥቃት ሰለባ የሆኑ አይሁዳውያን ንብረታቸውን እንዲጠይቁ የሚፈቅደው ሕግም አሁን ጊዜ አልፎበታል።

ከአይዝነር ቤተሰብ ለተወሰዱት የጥበብ ሥራዎች ግን አሁንም የማስመለስ ተስፋ አለ።

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በበርሊን የሚገኘው የብሮሃን ሙዚየም የአይዘንዋልዝወርክ ሥዕል ለሄንሪክ አይዝነር ቤተሰቦች ለመመለስ ማሰቡን ለአንቶኒ አሳውቋል።

ሙዚየሙ ጉዳዩ በሂደት ላይ ያለ በመሆኑ ከቢቢሲ ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ አልፈለገም።

በኢየሩሳሌም ከሚገኘው የእስራኤል ሙዚየም ሌላ ሥዕል ለአንቶኒ የተመለሰ ሲሆን፣ በኦስትሪያ የሚገኝ ሌላ የሥዕል ሥራ ጥያቄም እንዲሁ በእንጥልጥል ላይ ነው።

የአንቶኒ ምርመራ ካገኛቸው ማስረጃዎች መካከል ከናዚ የደኅንነት ፖሊስ (ጌስታፖ) ዝርዝር ውስጥ ከዘመዶቹ የተወሰዱ ልዩ ቅርሶችን እና ሥዕሎችን ይዟል።

ቤተሰቡ ወደፊት ተጨማሪ ንብረቶችን አግኝቶ የማስመለስ ዕድሉ ሰፊ ነው።

"ሁልጊዜ ስለ ማስመለስ ስናገር ስለ ቅርሶቹ፣ ገንዘብ እና ንብረት ሳይሆን ስለ ሰው ነው" ይላል አንቶኒ።

የቤተሰቡን ያለፈ ታሪክ ሲመረምር በአንድ ወቅት አባቱ እና አያቶቹ እነማን እንደሆኑ ዝርዝር ዕውቀት አግኝቷል።

"ይህ ሁሉ ውጣ ውረድ እውነተኛ ሕይወት ያላቸው ወደ እውነተኛ ሰውነት ቀይሯቸዋል።"

ይህ ዕውቀት አሁን ለአዲሱ ትውልድ ተላልፏል።

ፒተር በ1939 ወደ ብሪታንያ በመርከብ ሲጓዝ የአይዝነር ስም ጠፍቶ ሊሆን ይችላል፤ አሁን ግን እንደገና ሕያው ነው።

በነሐሴ 2024 የተወለደው የአንቶኒ ታላቅ ወንድም ልጅ ካስፒያን የአይዝነር ስም ተሰጥቶታል።

አንቶኒ ወንድሙ ለረጅም ጊዜ የናፈቁትን ቤተሰቦቻቸውን ለማክበር መወሰኑ ትልቅ ስሜት ፈጥሮበታል።

"ታውቃለህ፣ ካስፒያን እስካለ ድረስ ይህ ስም አሁንም ከእሱ ጋር ይኖራል" ይላል።

"ሰዎች እንዲህ ብለው ይጠይቃሉ፤ ይህ ገራሚ ስም ነው፤ ታሪኩ ምንድን ነው?"