ቀጥታ, በግሪንላንድ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር የተፋጠጡት የአውሮፓ መሪዎች ለአጸፋ ምላሽ እየተዘጋጁ ነው

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ግሪንላንድን ለመጠቅለል የያዙትን ዕቅድ እየተቃወሙ ባሉ የአውሮፓ አገራት ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ መዛታቸውን ተከትሎ፤ አገራቱ ለአጸፋ ምላሽ እየተጋጁ እንደሆነ ተገለጸ። አውሮፓውያን አገራቱ በመጪው ሐሙስ ስላሏቸውን አማራጮች ለመወያየት አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል። ከአማራጮቹ አንዱ በአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፍ መጣል ነው ተብሏል።

ጭምቅ ሃሳብ

  • በግሪንላንድ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር የተፋጠጡት የአውሮፓ መሪዎች ለአጸፋ ምላሽ እየተዘጋጁ ነው
  • "አውሮፓን ማስገደድ አይቻልም"- የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር

የቀጥታ ሽፋን

  1. “አውሮፓን ማስገደድ አይቻልም”- የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር

    የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜቴ ፍሬድሪክሰን “አውሮፓን ማስገደድ አይቻልም” ሲሉ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛቻ ምላሽ ሰጡ።

    ትራምፕ፤ አሜሪካ ግሪንላንድን ለመጠቅለል የምታደርገውን ሙከራ የሚያሰናክሉ ከሆነ ስምንት የአውሮፓ አገራት ታሪፍ እንደሚጣልባቸው ዝተዋል።

    ትራምፕ ከፊል ራስ ገዝ የሆነችው የዴንማርክ ግዛት ግሪንላንድን እንደሚጠቀልሉ መግለጻቸውን ተከትሎ፤ ዕቅዳቸውን የማይቀበሉ አገራት ላይ ታሪፍ እንደሚጥሉ ማስታወቃቸው በአውሮፓ ውዝግብ አስከትሏል።

    ታሪፍ ይጣልባቸዋል የተባሉት ስምንት አገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ የትራምፕ ዕቅድ “አደገኛ አካሄድ ነው” ሲሉ ኮንነዋል።

    “ታሪፍ ለመጣል መዛት ግንኙነትን ያሻክራል። ዴንማርክን እንዲሁም የግሪንላንድ ሕዝብን ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን” ብለዋል።

    የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) አባል አገራቱ “የአርክቲክን ደኅንነት ለመጠበቅ ቁርጠኛ ነን” ሲሉም አቋማቸውን ገልጸዋል።

    የአሜሪካ አጋር የሆኑት ዴንማርክ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን እና ዩናይትድ ኪንግደም በጋራ ካወጡት መግለጫ ባሻገር የዴንማርክ ጠቅላይ ሚኒስትር በተናጠል ባስተላለፉት መልዕክት የትራምፕን ዕቅድ አጥብቀው አውግዘዋል።

    በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም “ግጭት የፈለግነው እኛ አይደለንም። እኛ ትብብር ነው የምንሻው። የተቀረው አውሮፓ ስለደገፈን ደስተኛ ነኝ። አውሮፓን ማስገደድ አይቻልም” ብለዋል።

  2. በግሪንላንድ ጉዳይ ከአሜሪካ ጋር የተፋጠጡት የአውሮፓ መሪዎች ለአጸፋ ምላሽ እየተዘጋጁ መሆኑ ተገለጸ

    የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደሮች፤ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአውሮፓ አጋሮች ላይ ሊጥሉ ያሰቡትን የታሪፍ ዕቅድ እንዲተዉ ለማሳመን የሚያደርጉትን ጥረት ለማጠናከር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ።

    ታሪፉ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ኅብረቱ የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ እየተዘጋጀ መሆኑን እሑድ ዕለት እንደተናገሩ የዜና ወኪሉ ሮይተርስ ዘግቧል።

    ፕሬዝዳንት ትራምፕ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ አሜሪካ ግሪንላንድን እንድትገዛ እስካልተፈቀደላት ድረስ ከአውሮፓውያኑ የካቲት 1 ጀምሮ በአውሮፓ ኅብረት አባላት በሆኑ አገራት ላይ ተከታታይ የታሪፍ ጭማሪዎችን እንደሚያደርጉ ዝተዋል።

    የታሪፍ ጭማሪ ይደረግባቸዋል የተባሉት አገራት ዴንማርክ፣ ስዊድን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ኔዘርላንድስ እና ፊንላንድ ናቸው።

    የአውሮፓ ኅብረት አገራት በበኩላቸው እርምጃውን በማስፈራራት የማስገደድ ዘዴ እንደሆነ በመግለጽ ኮንነውታል።

    የኅብረቱ መሪዎች፤ አሜሪካ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ምን ዓይነት አማራጮች እንዳሏቸው ለመወያየት ለመጪው ሐሙስ አስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።

    ከቀረቡት አማራጮች አንዱ ወደ አውሮፓ በሚገባው እና 107.7 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ እንዳላቸው በሚገመቱት የአሜሪካ ምርቶች ላይ ታሪፎችን መጣል ነው።

    እስካሁን ድረስ ጥቅም ላይ ውሎ የማያውቀው አውሮፓ ኅብረት "የፀረ-ማስገደድ" እርምጃም (Anti-Coercion Instrument) በሌላ አማራጭነት ቀርቧል።

    ይህ እርምጃ፤ አሜሪካ በአውሮፓ ኅብረት ውስጥ ትርፍ በምታገኝባቸው የዲጂታል አገልግሎቶች፣ የኢንቨስትመንት፣ የባንክ ሥራዎች ወይም የንግድ አገልግሎቶች ላይ ገደብ የሚጥል ነው።

    እንደ ሮይተርስ ዘገባ፤ አሁን ባለው ሁኔታ ከዚህ ይልቅ ታሪፎችን መጣል ሰፊ ድጋፍ ያለው አማራጭ እንደሆነ የአወሮፓ ኅብረት ምንጮች ገልጸዋል።