ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ጀርመን ጥቃት ሊፈፅም ነበር ያለችውን የሐማስ አባል ያዘች
የጀርመን ፖሊስ አንድ የሊባኖስ ዜጋን የሐማስ አባል በመሆን እና አውሮፓ ውስጥ ጥቃት ለመፈጸም እያቀደ ነበር በማለት መያዙን አስታወቀ።
ማንነቱ "ሞሐመድ ኤስ." በሚል የተገለጸው ግለሰብ በቁጥጥር ሥር የዋለው ከቤይሩት ተነስቶ በርሊን ብራንደንበርግ አየር ማረፊያ ከደረሰ በኋላ ነው።
የጀርመን ፌደራል መንግሥት ዐቃቢያነ ሕጎች ግለሰቡ በአይሁዳውን እና በአስራኤል ተቋማት ላይ ጥቃት ሊፈጸም በታቀደ ሴራ ውስጥ በመሳተፍ እና ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጥይቶችን በመግዛት ውስጥ ተሳትፏል ብለዋል።
ተጠርጣሪው የክስ ሂደቱ ከመጀመሩ በፊት በእስር ላይ እንዲቆይ ለማድረግ ዳኛ ፊት እንደሚቀርብ ተገልጿል።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በእስራኤል በተፈጸመበት ጥቃት ክፉኛ የተዳከመው እና ጋዛን የሚቆጣጠረው ሐማስ በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በእስራኤል እና በሌሎች በርካታ አገራት በሽብር ቡድንነት የተፈረጀ ነው።
ፍልስጤማዊው ታጣቂ ቡድን ከሁለት ዓመት በፊት በእስራኤል ላይ በፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት 1,200 ያህል ሰዎችን በመግደል ከ250 በላይ የሚሆኑትን አግቶ ወስዶ ነበር።
ይህንንም ተከትሎ እስራኤል በጋዛ ላይ ባካሄደችው መጠነ ሰፊ ወደታራዊ ዘመቻ ከ70 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አሁን በቁጥጥር ሥር የዋለው "ሞሐመድ ኤስ." ባለፈው ጥቅምት ጀርመን ውስጥ በሚገኙ በአይሁዳውያን እና በእስራኤል ተቋማት ላይ ጥቃት ለመፈጸም ከነበረ ዕቅድ ጋር በተያያዘ ከተያዘው "አበድ አል ጂ" ከተባለው ግለሰብ ጋር ግንኙነት እንዳለው የጀርመን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።
በወቅቱ ሦስት ሰዎች የጦር መሳሪያ ለመቀባበል በርሊን ውስጥ በተገናኙበት ጊዜ በፖሊሶች ተይዘዋል። ከተያዙት መካከል ሁለቱ የጀርመን ዜጎች ሲሆኑ፣ አንዱ ደግሞ የሊባኖስ ዜጋ ነው።
ፖሊስ እርምጃውን በወሰደበት ጊዜ ላይፕዚግ እና ኦበርሃውሰን በተባሉ ሁለት የጀርመን ከተሞች ውስጥ ፍተሻ ተደርጎ እንደነበረ ዴር ስፒግል የተባለው የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግቧል።
ከዚህ ጋር ባልተያያዘ ሁኔታ ደግሞ ባለፈው ኅዳር የጀርመን ባለሥልጣናት ሌላ የሊባኖስ ዜጋ የሆነ ተጠርጣሪ የሐማስ አባልን አገሪቱ ከቼክ ሪፐብሊክ ከምትዋሰንበት ድንበር አቅራቢያ ይዘዋል።