ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አመፅ በተጋጋለባት የአሜሪካዋ ከተማ በፖሊስ ስተለገደለው ግለሰብ የምናውቀው
ቅዳሜ ዕለት በአሜሪካዋ ሚኒያፖሊስ ከተማ የፌዴራል የስደተኞች እና ጉምሩክ ተቆጣጣሪ መኮንኖች አንድን ግሰለብ ተኩሰው መግደላቸውን ተከትሎ ቁጣው ተጋግሏል።
የ37 ዓመቱ ነርስ በከተማዋ በስተደኛ ተቆጣጣሪ ፖሊሶች (አይስ) የተገደለ ሁለተኛው ሰው ሲሆን፣ የአሜሪካ ዜጋ እና የከተማዋ ነዋሪ እንደነበር ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
በድንበር ጥበቃ ፖሊሶች እና በግለሰቡ መካከል የነበረውን አለመግባባት የሚያሳዩ ቪድየዎች በማኅበራዊ ሚድያ ተሠራጭተዋል።
የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መኮንኖቹ የተኮሱት ግለሰቡ ሽጉጥ ይዞ ስለነበር እና መሣሪያውን አላስረክብም በማለቱ ራሳቸውን ለመከላከል ነው ብለዋል።
የዐይን እማኞች፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት እና የግለሰቡ ቤተሰቦች ይህንን መግለጫ ተቃውመዋል። በእጁ የያዘው ተንቀሳቃሽ ስልክ እንጂ ሽጉጥ አይደለም ብለዋል።
የሟች ቤተሰቦች መንግሥት "በጣም የሚያሳምም ሐሰት" አሠራጭቷል ሲሉ የወቀሱ ሲሆን፣ "እባካችሁ ስለልጃችን እውነቱን አውጡ" ሲሉ ጠይቀዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት ሪኔ ጉድ የተባለች የአሜሪካ ዜጋ በስደተኛ ተቆጣጣሪ ፖሊስ መገደሏ የሚታወስ ነው።
ይህን ተከትሎም በተነሳው ተቃውሞ የአካባቢው ባለሥልጣናት እና ነዋሪዎች የፌዴራል መኮንኖች ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።
ቅዳሜ የተሰማው ግድያ የተከሰተው በአካባቢው ሰዓት አቆጣጠር ጥዋት 3፡05 ገደማ በደቡብ ሚኒያፖሊስ ነው።
የድንበር ጥበቃ ፖሊስ ኃላፊ ግሬግ ቦቪኖ እንዳሉት መኮንኖቹ "ዒላማቸውን" ለይተው ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ዘመቻ እያካሄዱ ሳለ ነው ፕሬቲ "9 ሚሊ ሜትር ከፊል አውቶማቲክ" ሽጉጥ ይዞ የተጠጋው።
ቦቪኖ ግለሰቡ ሽጉጥ በእጁ ይዞ ነበር ወይ የሚለውን ባይገለጹም መኮንኖቹ ሊነጥቁት እንደነበር አስታውቀው "ይህን ለመፈጸም ፈቃደኛ አልነበረም" ብለዋል።
ኃላፊው አክለው የድንበር ጥበቃ ፖሊሶቹ "ራሳቸውን ለመከላከል" ተኩሰዋል ብለዋል።
ሁኔታውን የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች ፕሬቲ መኮንኖቹን በስልኩ ሲቀርፅ እና በአካባቢው የነበሩ ሰዎች ሲጮሁ እና ሲያፏጩ ያሳያሉ።
በአንደኛው ቪድዮ አንድ ፖሊስ አንዲት ግለሰብን ሲገፍትራት ይታያል። ፕሬቲ ግለሰቧን በአንድ ክርኑ ደግፎ በሌላኛው እጁ ደግሞ ስልክ ይዞ ፖሊሶቹን ለመከላከል ሲሞክር እንደነበር ታይቷል።
በተለያዩ ቪድዮዎች ላይ ፕሬቲ ሽጉጥ ይዞ አይታይም። ቀጥሎ ቢያንስ 6 ፖሊሶች ግለሰቡን ይዘው ወደመሬት ሲገፍትሩት እና አንድ ፖሊስ በተደጋጋሚ ሽጉጥ ሲተኩስ ቪድየዎቹ አሳይተዋል።
ፖሊሶቹ መሬት ላይ ከተጋደመው ግለሰብ ራሳቸውን ሲያርቁም የተኩስ ድምፅ ይሰማ ነበር። በጠቅላላው አስር የተኩስ ድምፆች ተሰምተዋል።
የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር የግለሰቡ ነው ያለውን ሽጉጥ ፎቶ በማኅበራዊ ገፁ ላይ አጋርቷል።
ቦቪኖ በበኩላቸው "ሁኔታው ግለሰቡ ከፍተኛ ጉዳት ለማድረስ እና የሕግ አስከባሪ ኃይሎችን ለመጨፍጨፍ" የተዘጋጀ ይመስላል ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
የሚኒሶታ ግዛት ገዥ የሆኑት ዲሞክራቱ ቲም ዋልዝ "ተንቀሳቃሽ ምሥል በመኖሩ ለፈጣሪ ምስጋና ይግባው" ብለው የሀገር ውስጥ ደኅንነት መግለጫን "ሐሰት" ሲሉ ወቅሰዋል።
የአሌክስ ፕሬቲ ወላጆች የሆኑት ማይክል እና ሱዛን ስለልጃቸው "እውነታው" እንዲወጣ ጠይቀዋል።
ወላጆቹ ባወጡት መግለጫ "ልባችን ተሰብሯል፤ ደግሞም እጅግ ተበሳጭተናል" ማለታቸውን የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።