ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አርሴናል ከማንቸስተር ዩናይትድ እና የሌሎች የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታ ግምቶች
የ23ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚር ሊግ ጨዋታዎች ቅዳሜ፣ እሑድ እና ሰኞ እንዲከናወኑ መርሃ ግብር ተይዞላቸዋል።
ቅዳሜ አምስት፤ እሑድ አራት ቀሪው አንድ ጨዋታ ደግሞ ሰኞ የሚከናወን ይሆናል።
ለንደን ላይ የሊጉ መሪ አርሴናል ባለፈው ሳምንት በማንቸስተር ደርቢ አሸነፊ የሆነውን ማንቸስተር ዩናይትድን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል።
እነዚህን የሊጉን ጨዋታዎች የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን እንደሚከተለው ገምቷል።
ቅዳሜ
ዌስት ሃም ከ ሰንደርላንድ
በውድድር ዓመቱ መክፍቻ ሳምንት ሰንደርላንድ ዌስት ሃምን 3 ለምንም ያሸነፈበት ጨዋታው የቡድኖቹን ዕጣ ፈንታ የሚጠቁም ይመስላል።
ዌስት ሃም ባለፈው ሳምንት ቶተንሃምን ማሸነፍ ችሏል።
ሰንደርላንድ ደግሞ ከሜዳው ውጭ ጥሩ የሚባል ጊዜ እያሳለፈ አይገኝም።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት የትኛውም ቡድን ማንንም ማሸነፍ እንደሚችል ተደጋግሞ በመታየቱ ጨዋታዎችን ለመገመት ከባድ አድርጎታል።
ግምት፡ 1 - 1
በርንሌይ ከ ቶተንሃም
ቶተንሃም ማክሰኞ ምሽት በሻምፒዮንስ ሊግ ቦሪስያ ዶርትሙንድን ቢያሸንፍም አሰልጣኝ ቶማስ ፍራንክ አሁንም ጫና ውስጥ ናቸው።
በርንሌይ ላለመውረድ እየተፍጨረጨረ እንደሚገኝ ከሊቨርፑል ጋር አቻ በመለያየት አሳይቷል።
ቡድኑ በሊጉ ለመቆየት በሜዳው የሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ወሳኝ ናቸው።
ጨዋታው በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።
ግምት፡ 0 - 0
ፉልሃም ከ ብራይተን
ሁለቱ ቡድኖች በደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ተከታትለው ከመቀመጣቸውም በላይ በመጀመሪያው ዙር አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።
ፉልሃም ባለፈው ሳምንት በሊድስ ቢሸነፍም በርካታ ተጫዋቾችን ከአፍሪካ ዋንጫ መልስ አግኝቷል።
ብራይተን ጎል ማስቀጠር ቢችልም ጨዋታው በፉልሃም የበላይነት የሚጠናቀቅ ይመስለኛል።
ግምት፡ 2 - 1
ማንቸስተር ሲቲ ከ ዎልቭስ
ኧርሊንግ ሃላንድ ባለፉት ሳምንታት ብራይተን ላይ ብቻ በፍጹም ቅጣት ምት ጎል አስቆጥሯል።
የሲቲ ችግር ሰፊ መሆኑን ለመረዳት በሻምፒዮንስ ሊግ በቦዶ/ግሊምት መሸነፋቸውን መመልከት በቂ ነው።
አዲስ ፈራሚው ማርክ ጉሂ በዚህ ጨዋታ መሰለፉ የቡድኑን የተከላካይ መስመር ያረጋጋዋል።
ዎልቭስ ባለፉት አራት ጨዋታዎች ባለመሸነፍ ለመነቃቃት ቢሞክርም የሲቲ የቁጣ ምት የሚያርፍበት ይመስለኛል።
ግምት፡ 3 - 1
በርንመዝ ከ ሊቨርፑል
ሊቨርፑል ረቡዕ ዕለት ከማርሴይ ጋር ጥሩ ቢጫወትም ይህ ጨዋታ እንደሚከብደው እገምታለሁ።
በርንመዝ በበኩሉ ዘንድሮ ለመገመት አስቸጋሪ የሆነ ቡድን ሆኗል።
ውጤቱ ምንም ይሆን ምን ይህ ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ይታይበታል።
በርንመዞች ጎል ማስቆጠር ቢችሉም ሦስት ነጥቡ የሊቨርፑል እንደሚሆን እገምታለሁ።
ግምት፡ 1 - 2
እሑድ
ብሬንትፎርድ ከ ኖቲንግሃም ፎረስት
ብሬንትፎርድ በሜዳው ጠንካራ ቢሆንም የፎረስት አጨዋወት ጨዋታውን ከባድ ያደርግባቸዋል።
ብሬንትፎርድ በመከላከል እና በመልሶ ማጥቃት ለመጫወት የሚመርጡ ሲሆን ፎረስትም ተመሳሳይ አካሄድን ይመርጣል።
የሾን ዳይሽ ቡድን ከኋላ ክፍተት ባለመፍጠር በመልሶ ማጥቃት ጎል ያስቆጥራል።
ግምት፡ 2 - 1
ክሪስታል ፓላስ ከ ቼልሲ
ፓላስ እየተፈረካከሰ ይመስላል። አምበሉ ማርክ ጉሂ ወደ ሲቲ አቅንቷል። አሰልጣኑ ዘንድሮ እንደሚለቁ ተናግረዋል። አጥቂው ሦን-ፊሊፔ ማቴታም ልቀቁኝ ብሏል።
ቼልሲ ቤትም ነገሮች ጥሩ አይመስሉም። አዲሱ አሰልጣኝ ሊያም ሮዝኒየር በአንዳንድ ውሳኔዎቻቸው እየተተቹ ነው።
ይህንን ጨዋታ ቼልሲ እንደሚያሽንፍ እገምታለሁ።
የፓላስ መጨረሻ ምን ሊሆን እንደሚችል መገመት ግን ከባድ ነው።
ግምት፡ 0 - 1
ኒውካስል ዩናይትድ ከ አስቶን ቪላ
ቪላ ባለፈው ሳምንት በሜዳው በኤቨርተን መሸነፉ የሊጉን ጨዋታዎች ለመገመት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ያሳያል።
ቪላ በሜዳው ያደረጋቸውን 11 ጫዋታዎች ከማሸነፉም በላይ ባለፉት ዓመታት በኤቨርተን ላይ የበላይነት ነበረው።
ቪላ በዩሮፓ ሊግ ወደ ቱርክ ከመጓዙም በላይ ተጫዎችን በጉዳት አጥቷል።
በዚህ ምክንያትም ይህንን ጨዋታ ኒውካስል እንደሚያሽንፍ እገምታለሁ። የቡድኑ አማካይ ጠንካራ ከመሆኑም በላይ በሜዳው ውጤታማ ነው።
ግምት፡ 2 - 1
አርሴናል ከ ማንቸስተር ዩናይትድ
ዩናይትድ በአዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ማይክል ካሪክ ስር በማንቸስተር ደርቢ ጥሩ ተንቀሳቅሷል።
ቡድኑ ወጥ አቋም ማሳየት እንዳለበት አሰልጣኙ ቢናገርም፤ ምንም ያህል ጥሩ ቢንቀሳቀሱ ከኤምሬትስ አንድ ነገር ለማግኘት ከባድ ይሆንባቸዋል።
አርሰናል ባለፈው ሳምንት ከፎረስት ጋር ነጥብ ተጋርቷል።
የሚኬል አርቴታ ቡድን በድጋሚ ነጥብ የሚጥል አይመስለኝም።
ካሪክ የሲቲን አጨዋወት እንዳስቆመው የመድፈኞቹንም የሚያስቆም ዝግጅት ቢያደርግም የአርሴናለን የቆመ ኳስ ምን ሊያደርገው ይችላል?
ግምት፡ 2 - 0
ሰኞ
ኤቨርተን ከ ሊድስ
ኤቨርተንም ዘንድሮ ለመገመት አስቸጋሪ ከሆኑት ቡድኖች መካከል ነው።
ጃክ ግሪሊሽ በጉዳት ምክንያት ከዚህ ጨዋታ ውጭ መሆኑ ተረጋግጧል።
በመጀመሪያው ዙር ጨዋታ ሊድስ አንድ ለምንም ማሸነፍ ችሏል።
ጨዋታው በኤቨርተን አንድ ለምንም የበላይነት እንደሚጠናቀቅ ባስብም ዶምኒክ ካልቨርት ሌዊን በቀድሞ ክለቡ ላይ ጎል እንደሚያስቆጥር አስባለሁ።
ግምት፡ 1 - 1