ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከፍጻሜው ጨዋታ ባሻገር በሞሮኮው የአፍሪካ ዋንጫ የታዩ አነጋጋሪ ጉዳዮች
የ2025 የአፍሪካ እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር የተጠናቀቀበት መንገድ ሁልጊዜም ሲታወስ የሚኖር ነው።
ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሽርፍራፊ ሰከንዶች ሲቀሩት ዳኛው ለሞሮኮ ፍፁም ቅጣት ምት መስጠታቸውን ተከትሎ የሴኔጋል ተጫዋቾች ሜዳ ጥለው ለመውጣት ሞክረዋል።
የሞሮኮው ብራሒም ዲያዝ ፓኔንካ የተሰኘው የፍፁም ቅጣት ምት አመታት ተጠቅሞ ወደ መረብ የሰደዳት ኳስ በቀላሉ በሜንዲ ተይዛለች።
የአትላስ አናብስቱ አሠልጣኝ ዋሊድ ሬግራጉዊ ሁኔታውን "አሳፋሪ" ሲሉ የገለፁት ሲሆን፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፋ) ደግሞ ቅጣት ያስተላልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ነገር ግን ውድድሩን የሚገልጸው ይህ ብቻ አልነበረም።
ሞሮኮ ያዘጋጀችው የአፍሪካ ዋንጫ ከሞላ ጎደል የተሳካ እና ክብረ ወሰን የሰበሩ ግቦች የተቆጠሩበት ነው።
ለመሆኑ ለአንድ ወር ያህል ጊዜ በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ሲካሄድ ከቆየው የአፍሪካ ዋንጫ ምን ተማርን?
ደረጃቸውን የጠበቁ መሠረተ-ልማቶች
ሞሮኮ እጅግ ድንቅ የሚባል መሠረተ-ልማት ገንብታ፤ ስታድየሞቿን አስውባ ነው የጠበቀችው። በዋና ከተማዋ ራባት የሚገኘው የልዑል ሙሌይ አብደላህ ስታድየምን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
ሞሮኮ በአውሮፓውያኑ 2030 ከስፔን እና ፖርቹጋል ጋር በመሆን የዓለም ዋንጫን ለማዘጋጀት ደፋ ቀና እያለች ነው።
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ገንዘብ መድባ መሠረተ-ልማቷን ስታጠናክር ቆይታለች። ንጉሥ ሞሐመድ ስድስተኛ የሀገራቸውን መሠረተ-ልማት "ጥንካሬ እና ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ ዝግጁነት ያሳየ" ነው ብለውታል።
ካዛብላንካ የሚገኘው ስታዴ ሞሐመድ አምስተኛ እንዲሁም በፌስ፣ ማራኬሽ እና አጋዲር የሚገኙ ስታድየሞች ይታደሳሉ። ቤንስሊማኒ አቅራቢያ የሚገነባው 115 ሺህ መቀመጫዎች የሚኖሩት ስታድየም ግንባታም እየተጣደፈ ነው።
ለአፍሪካ ዋንጫ አዘጋጆች ብዙውን ጊዜ ፈተና የሚሆነው የመጫወቻ ሜዳ ሳር በዝናብ ወቅት እንኳ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን አሳይቷል።
"በቴክኖሎጂያችን እጅግ ደስተኞች ነን" ሲል የሮያል ሞሮኮ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አባል የሆነው ኦማር ኺያሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
"አፍሪካ ከሌሎች ሀገራት በላቀ ሁኔታ ልታደርገው እንደምትችል በማሳየቷ ደስተኞች ነን። ከዚያም በላይ ይህ ሁሉ ቴክኖሎጂ ምንጩ ከሞሮኮ መሆኑን ደስ የሚያሰኝ ነው።"
የቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ጥምር አዘጋጅ የሆኑት ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ በተመሳሳይ መልኩ የላቀ መሠረተ-ልማት ያሳያሉ ወይ የሚለው አጠራጣሪ ነው።
የኬንያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት ሁሴን ሞሐመድ፤ ሞሮኮ "ደረጃውን ከፍ አድርጋዋለች ብለው ነገር ግን የ2027 የአፍሪካ ዋንጫን የተሳካ ለማድረግ የተጀመሩ መሠረተ-ልማቶች እየተሻሻሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሦስቱ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት የሚያዘጋጁት ዋንጫ በየትኛው ወር ላይ እንደሚደረግ ካፍ ይፋ አላደረገም።
የተሻለ ገቢ
ካፍ እንደሚለው ከአፍሪካ ዋንጫ የሚገኘው ገቢ 90 በመቶ የጨመረ ሲሆን፣ በ2023 በአይቮሪ ኮስት ከቲኬት ሽያጭ የተገኘው 11 ሚሊዮን ዶላር በሞሮኮ ወደ 55 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ብሏል።
ውድድሩን ስፖንሰር የሚያደርጉ እና አጋር ሆነው የሚሠሩ ድርጅቶችም ቁጥር ወደ 23 ከፍ ብሏል። የአፍሪካ ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታ በማኅበራዊ ሚድያ ሰፊ መነጋገሪያም ሆኗል።
የአፍሪካ ዋንጫ ገቢ እና ተደራሽነት እንዲህ ከጨመረ ካፍ በየሁለት ዓመቱ ይደረግ የነበረውን የአህጉሪቱን ትልቁን የእግር ኳስ ውድድር ወደ አራት ዓመት ከፍ ማድረጉ አወዛጋቢ ነው። በሞሮኮ የተገኘው ገቢ በሌሎች ሀገራትስ ሊደገም ይችላል ወይ የሚለው አጠያያቂ ነው።
ሞሮኮ ለሦስተኛ ተከታታይ ጊዜ የሴቶች የአፍሪካ እግርኳስ ውድድር ዋንጫን ታዘጋጃለች።
የዳኝነት ጥያቄ
ከስኬቱ በተቃራኒ የእግር ኳስ ዳኞች ብቃት ጥያቄ ውስጥ የገባ ጉዳይ ሆኗል።
ሞሮኮ ከናይጄሪያ ጋር ከነበራት የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ በፊት አሠልጣኝ ሬግራጉዊ ዳኞች ለአዘጋጇ ሀገር ያዳላሉ የሚለውን ሐሳብ ሲያጣጥሉ ተሰምተዋል።
"እኔ በርካታ ጨዋታዎችን እመለከታለሁ። አጨቃጫቂው ጉዳይ ሁሉም ቦታ ያለ ነው። በአፍሪካም በሉት በአውሮፓ" ብለዋል።
በፍፃሜው ጨዋታ አርቢትሩ ዣን-ዣክ ንዳላ እስከ ሁለተኛ አጋማሽ ፍፃሜ ድረስ ሁኔታውን ተቆጣጥረው ሲመሩት ቆይተዋል።
90 ደቂቃው ተጠናቆ 8 ጭማሪ ደቂቃ ከታየ በኋላ በሁለትኛው ደቂቃ ሴኔጋል ጎል ብታስቆጥርም የሞሮኮው አምበል አሽራፍ ሐኪሚ ላይ ጥፋት ተሰርቷል በማለት ጎሉን መሻራቸው የሴኔጋል አሠልጣኝ እና ደጋፊዎችን ያስቆጣ ነበረ።
ከስድስት ደቂቃ በኋላ ደግሞ ሞሮኮ የፍፁም ቅጣት ምት ማግኘቷ ሴኔጋሎች ከሜዳ ለመውጣት የመሞከራቸው ምክንያት ሆነ።
በጠቅላላው በውድድሩ በርካታ ጊዜ የቪኤአር ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ቆይቷል። ረጅም ደቂቃ የወሰዱ የቪድዮ ምልከታዎች፣ አጠያያቂ በእጅ የተነኩ ኳሶች እና የፍፁም ቅጣት ምት ጥያቄዎች የሞሉትም ነበር።
ሞሮኮ ይህን ሁሉ ወጪ ያደረገችበት ውድድር 'ሴሚ-አውቶሜቴድ' የተሰኘው የዘመነ ከጨዋታ ውጭ የሆኑ ኳሶች (ኦፍሳይድ) መለያ ቴክኖሎጂ እንዴት የለውም የሚለውም ያነጋግራል።
ፀጥታ እና የደጋፊ ቁጥጥር
የሴኔጋል የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾቹ ከፍፃሜው በፊት በባቡር ወደ ራባት ሲመጡ በበርካታ ሰዎች መከበባቸውን ተከትሎ የተሰማውን ቅሬታ ገልጿል።
ለሞሮኮ ከተሰጠው አወዛጋቢ ፍፁም ቅጣት ምት በኋላ የቴራንጋ አናብስት ደጋፊዎች ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተጋጭተዋል።
ቢቢሲ ስፖርት አፍሪካ ከስታድየም ውጭ ደጋፊዎች ግፊያ እና መጨናነቅ ሲድርስባቸው መመልከት ችሏል።
እርግጥ የደጋፊ ቁጥጥር ማረጋጋት የአፍሪካ እግር ኳስ ብቻ ችግር አይደለም። በ2020 የአውሮፓው ዋንጫ እና በ2022 የአውሮፓ ቻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ የተከሰተውን ልብ ይሏል።
ከፍፃሜው በፊት የሴኔጋል እግር ኳስ ፌዴሬሽን 69 ሺህ 500 መቀመጫዎች ባሉት ስታድየም የተሰጠኝ ቲኬት 4 ሺህ ብቻ ነው የሚል ቅሬታ አሰምቷል።
የሞሮኮ ኳስ አቀባይ ታዳጊዎች የኤድዋርዶ ሜንዲን ፎጣ ከሁለተኛው በረኛ ለመንጠቅ ሲሞክሩም ታይተዋል።
ካፋ በእሑድ ጨዋታ የተስተዋሉ የስፖርት ዲሲፕሊን ጥሰቶችን በተመለከተ ምን ዓይነት ቅጣት ያስተላልፋል የሚለው ይጠበቃል።
በማኅበራዊ ሚድያ የተለቀቁ ቪድየዎች በሩብ ፍፃሜው የናይጄሪያው ግብ ጠባቂ ስታንሊ ንዋባሊ ፎጣ ሁለት ጊዜ ሲሰረቅ እና የሞሮኮ ደጋፊዎች ደስታቸውን ሲገልፁ ያሳያሉ።
የመመሪያ ለውጥ
ካፍ በጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች የቢጫ ካርድ ጉዳይን በተመለከተ የመመሪያ ለውጥ ማድረግ ያለበት ይመስላል።
በግማሽ ፍፃሜው 20 ተጫዋቾች ሁለተኛ ቢጫ ካርድ ከተመለከቱ ለፍፃሜው እንደማይጫወቱ ስለሚያውቁት በጥንቃቄ ሲንቀሳቀሱ ነበር።
የሴኔጋሉ አምበል ካሊዶ ኩሊባሊ እና አማካዩ ሐቢብ ዲያራ በዚህ ሕግ ምክንያት በፍፃሜው አልተሳተፉም። ናይጄሪያ እና ግብፅ ለፍፃሜው ቢያልፉ ካልቪን ባሲ እና ሆሳም አብድልማጊድን አናያቸውም ነበር።
ምንም እንኳ ዲሲፒሊን አስፈላጊ ቢሆንም አሠልጣኞች፣ ተጫዋቾች፣ ደጋፊዎች እና መገናኛ ብዙኃን በፍፃሜው ጨዋታ ጠንካራ የሆነ ብሔራዊ ቡድን ማየት ይፈልጋሉ።