ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ግብፅ "በቂ ውሃ እንዳታገኝ" ያደረገውን የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ "መፍታት አለብኝ" አሉ
ከቀናት በፊት በአባይ (ናይል) ጉዳይ ኢትዮጵያ እና ግብፅን ለማደራደር ጥያቄ ያቀረቡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ ኢትዮጵያ የናይል ወንዝ "ፍሰትን የሚያስቆም ግድብ" ሠርታለች አሉ። በዚህም ምክንያት ግብፅ ከናይል ወንዝ "በቂ ውሃ እንደማታገኝ" የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ይህንን ጉዳይ "መፍታት ይኖርብኛል" ሲሉ ተደምጠዋል።
ትራምፕ ይህንን የተናገሩት የበድጋሚ ወደ ሥልጣን የመጡበትን አንደኛ ዓመት በማስመልከት ትናንት ማክሰኞ ጥር 12/2018 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ላይ ነው።
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ አስተዳደራቸው 'አሳክቷል' ያሏቸውን ጉዳዮች ዘለግ ያለ ጊዜ ወስደው ያብራሩት ፕሬዝዳንቱ፤ በተደጋጋሚ የሚናገሩትን "ስምንት ጦርነቶችን አስቁሜያለሁ" የሚል መከራከሪያ በዚህ መግለጫ ላይም አንስተዋል።
ትራምፕ እንዳስቆሙ ከገለጿቸው ጦርነቶች ውስጥ በእስራኤል እና ኢራን፣ የኮሶቮ እና ሰርቢያ፣ የኮንጎ እና ሩዋንዳ፣ የፓኪስታን እና ሕንድ እንዲሁም አርሜኒያ እና አዘርባጃን መካከል የተካሄዱ ግጭቶች ይገኙባቸዋል። በኢትዮጵያ እና ግብፅ መካከል ሊነሳ ነበር ያሉትን ጦርነትም በዚህም ዝርዝር ውስጥ ተካትቷል።
እነዚህ ጦርነቶች "ለመቋጨት የማይቻሉ" በማለት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ "ለእያንዳንዱ ጦርነት የኖቤል ሽልማት ማግኘት ነበረብኝ" ሲሉም ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንቱ ከሚዘረዝሯቸው ከእነዚህ ግጭቶች ውስጥ አብዛኞቹ ለቀናት ብቻ የቆዩ ግጭቶች ሲሆኑ፣ በኢትዮጵያ እና ግብፅ መካከል ደግሞ አንድም ወታደራዊ እንቅስቃሴ አልተደረገም።
ትራምፕ ግን በማክሰኞው ንግግራቸው "ግብፅ እና ኢትዮጵያ በግድቡ ምክንያት ሊዋጉ ነበር፤ እኔ ግን አስቆምኳቸው" ብለዋል።
"ኢትዮጵያ ውስጥ ናይል ከሚባለው ትንሽ ወንዝ የሚመጣውን ፍሰት የሚያስቆም ግድብ ሠርተዋል" ያሉት ፕሬዝዳንቱ፤ አሁንም ቢሆን ይህንን ጉዳይ መፍታት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
"ሁልጊዜም ናይል ግብፅ ውስጥ እንዳለ ነበር የማስበው፤ ውቡ ናይል ከፒራዲሚዶች ጋር። እነርሱ ግን ግድብ ገነቡ" ብለዋል።
ትራምፕ የናይል (አባይ) ወንዝን "ትንሽ" ቢሉትም መረጃዎች ግን 6,650 ኪሎ ሜትር ርዝመት በመያዝ በዓለም ረጅሙ ወንዝ ሆኖ አማዞንን ይፎካከራል።
የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው ወንዙ 11 የተፋሰሱ አገራትን በማካለል በቀጣናው መረጋጋት እና በውሃ ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ወንዝ ነው።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ አሜሪካ "ለግድቡ ግንባታ የዋለውን ገንዘብ ሰጥታለች" የሚለውን ንግግራቸውን በድጋሚ በዚህ በመግለጫቸው ላይም አንስተዋል።
"ለግድቡ ክፍያ የፈጸመው ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ [ነች]።በዓለም ላይ ትልቁ ግድብ ይመስለኛል" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከአሜሪካ 'ተሰጥቷል' ያሉትን ገንዘብ በተመለከተም "እኔ 'እንዴት ይህ እንዲሆን ፈቀዳችሁ? ለምን እንዲህ አደረግን?' አልኩ። እኛ ነን የገንዘብ ድጋፍ ያደረግነው" ሲሉም አክለዋል።
የግድቡን መገንባት "ምንኛ አስከፊ ነገር ነው" በማለት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ በዚህም ምክንያት ግብፅ በቂ ውሃ እያገኘች እንዳልሆነ ሲናገሩ ተደምጠዋል። "ግብፅ አባይ ውስጥ በቂ ውሃ የላትም። ውሃውንም ለብዙ ነገሮች ይጠቀሙበታል፤ ለመዝናኛ፣ ለጉዞ፣ ለቱሪዝም እና ለሌሎችም ነገሮች" ብለዋል።
"ትልቅ ግድብ አላቸው። አሁን እሱንም ለመፍታት መስራት ይኖርብኛል" ሲሉ ዕቅዳቸውን ገልጸዋል።
ትራምፕ ይህንን በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል የቁርሾ ምንጭ ስለሆነው የናይል ወንዝ እና የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በዚህ አዓነት መልኩ ሲናገሩ የመጀመሪያቸው አይደለም።
ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በተለያዩ ጊዜያት አሜሪካ ለግድቡ ግንባታ የዋለውን ገንዘብ እንደሰጠች እና በሁለቱ አገራት መካከል የተካሄደን ጦርነት እንዳስቆሙ በተደጋጋሚ ተናግረዋል።
በትራምፕ ስለሚነሳው የአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ ከቢቢሲ ጥያቄ የቀረበላቸው የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ፤ "ይህ የሕዳሴ ግድብ በኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ገንዘብ ነው የተገነባው" የሚል ምላሸ ሰጥተው ነበር።
ትራምፕ ይህንን ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ የምታነሳቸውን የቅሬታ ነጥቦች የሚደግፍ ንግግራቸውን በድጋሚ ትናንት ያሰሙት የናይል ወንዝ ጉዳይ በተመለከተ አዲስ አበባ እና ካይሮን ለማደራደር ጥያቄ ካቀረቡ ከቀናት በኋላ ነው።
ፕሬዝዳንት ባለፈው ሳምንር ጥር 8 ቀን ለግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አልሲሲ በጻፉት ደብዳቤ፤ "በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለውን ውጥረት መፍታት ከአጀንዳዬ በቀዳሚነት የሚቀመጥ ነው" ብለዋል።
"የናይል ወንዝ ክፍፍል" ጉዳይም "ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት" እንደሚፈልጉ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ፤ አሜሪካ "ለግብፅ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ቁርጠኛ" እንደሆነችም አረጋግጠዋል።