ትራምፕ የኖቤል ሽልማት ባለማግኘታቸው "ከአሁን በኋላ ስለ ሰላም ብቻ የማሰብ ግዴታ እንደሌለባቸው" ተናገሩ

ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት የጠበቁትን የኖቤል የሰላም ሽልማት ያላገኙት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ "ከአሁን በኋላ ስለ ሰላም ብቻ የማሰብ ግዴታ አለብኝ የሚል ስሜት እንደሌላቸው" ተናገሩ።

ትራምፕ ለኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዮናስ ጋህር ስቶሬ በላኩት መልዕክት ሽልማቱን ላለማግኘታቸው አገሪቱን ተጠያቂ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ስቶሬ በበኩላቸው ለትራምፕ በሰጡት ምላሽ የኖቤል ሽልማቱን የሚሰጠው ራሱን የቻለ ኮሚቴ እንጂ የኖርዌይ መንግሥት እንዳልሆነ አስረድተዋል።

ባለፈው ጥቅምት ላይ የተካሄደውን የ2025 ኖቤል ሽልማት በሰላም ዘርፍ ያሸነፉት የቬንዙዌላዋ የተቃዋሚ መሪ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ናቸው።

በተጨማሪም ትራምፕ በዚህ መልዕክታቸው፤ አሜሪካ የዴንማርክ ግዛት በሆነችውን ከፊል ራስ ገዟ ግሪንላንድ ላይ "ሙሉ እና አጠቃላይ ቁጥጥር" እንደሚያስፈልጋት ተናግረዋል።

ግዛቲቱን ለመቆጣጠር ኃይል የመጠቀም እቅድ ያላቸው እንደሆነ ሲጠየቁ ግን "አስተያየት የለኝም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

የኔቶ አባል የሆነቸው ዴንማርክ፤ የአሜሪካ የመካላከያ ተጣማሪ እና ከፍተኛ ተጽእኖ ያላት አጋር ነች። የኔቶ አባላት አንዳቸው ላይ ውጫዊ ጥቃት በሚደርስ ጊዜ መተባበር ላይ የተመሰረተ መርህን ይከተላሉ።

ጥምረቱ በአውሮፓውያኑ 1949 ከተመሰረተ ጀምሮ አንዱ አባል በሌላው ላይ ጥቃት ሰንዝሮ አያውቅም።

ዴንማርክ አሜሪካ በግሪንላንድ ላይ ወታደራዊ እርምጃ የምትወስድ ከሆነ የኔቶ መጨረሻ እንደሚሆን አስጠንቅቃለች።

አንዳንድ የአውሮፓ አገራትም ለዴንማርክ ድጋፋቸውን ለመግለጽ ባለፈው ሳምንት ጥቂት ወታደሮችን ወደ ግሪንላንድ ልከዋል።

ይህ የአውሮፓውያን አገራት ትዕምርታዊ እርምጃ ያልጣማቸው ትራምፕ፤ የግሪንላንድን ወደ አሜሪካ መጠቅለል በሚቃወሙ ስምንት የኔቶ አጋሮች ላይ የ10 በመቶ ታሪፍ እንደሚጥሉ ዝተዋል። ከመጪው የካቲት ጀምሮ ተግባራዊ የሚያደርጉትን ታሪፍ ሰኔ ላይ ወደ 25 በመቶ እንደሚያሳድጉትም አስጠንቅቀዋል።

የኖርዌይ ጠቅላይ ሚኒስትር በራሳቸውን እና በፊንላንድ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስተብ ስም ወደ ትራምፕ መልዕክት የላኩት ይህ ውጥረት በተካረረበት ወቅት ነው።

ሁለቱ የአውሮፓ መሪዎች "ሁላችንም ይህንን ለማብረድ እና ለማርገብ መስራት አለብን። አብረን መቋም ባለብን [በዚህ ጊዜ] በዙሪያችን ብዙ ነገር እየተፈጠረ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ ለዚህ በሰጡት ምላሽ፤ "ከ8 በላይ ጦርነቶችን አስቁሜም አገራችሁ የኖቤል የሰላም ሽልማት ላለመስጠት በመወሰኗ ከአሁን በኋላ ስለ ሰላም ብቻ የማሰብ ግዴታ የለብኝም። ምንም እንኳ [ሰላም] ሁሌም ትልቅ ቦታ የሚይዝ ቢሆንም አሁን ለአሜሪካ የሚበጀውን እና ተገቢውን ነገር አስባለሁ" ሲሉ ጽፈዋል።

ዴንማርክ ግሪንላንድን ከሩሲያ ወይም ከቻይና መከላከል እንደማትችል የተናገሩት ፕሬዝዳንቱ፤ ዴንማርክ "ለምን [የግሪንላንድ] 'የባለቤትነት መብት' ሊኖራት ቻለ? ምንም አይነት የጽሁፍ ሰነድ የለም። ከመቶ አመታት በፊት ጀልባ እዚያ ስላረፈ ብቻ ነው፤ የእኛም እዚያው ጀልባዎች ነበሩን" ሲሉ ጠይቀዋል።

"ኔቶ ከምስረታው ጀምሮ ማንም ሰው ካደረገለት በላይ አድርጌያለሁ፤ አሁን ኔቶ ለአሜሪካ አንድ ነገር ማድረግ አለበት" ብለዋል።

"በግሪንላንድ በእኛ ሙሉ ቁጥጥር ስር እስካልሆነች ድረስ የዓለም ደህንነት አይጠበቅም" በማለትም አቋማቸውን ገልጸዋል።

አነስተኛ የሕዝብ ቁጥር እና ከፍተኛ ሀብት ያላት የአርክቲክ ደሴቷ ግሪንላንድ፤ የሚሳኤል ጥቃትን አስቀድሞ ለማስጠንቀቅ እና በቀጣናው የሚያልፉ መርከቦችን ለመከታተል አመቺ ስፍራ ናት።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኬር ስታርመር፤ የግሪንላንድ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የተመለከተ ማንኛውም ውሳኔ የሚተላለፈው "በግሪንላንድ ሕዝብ እና በዴንማርክ ኪንግደም ብቻ" እንደሆነ ሰኞ ዕለት ተናግረዋል። አሜሪካ ልትጥል የዛተችውን ታሪፍም "ስህተት" ሲሉ ገልጸውታል።