ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፑንትላንድ የአይኤስ ተዋጊ የሆኑ 23 "ኢትዮጵያውያንን" መያዟን አስታወቀች
የሶማሊያ ግዛት የሆነችው ከፊል ራስ ገዟ ፑንትላንድ በቁጥጥር ሥር ካዋለቻቸው 53 የእስላማዊው ታጣቂ 'ኢስላሚክ ስቴት' (አይኤስ) ተዋጊዎች መካከል ግማሽ ገደማው "ኢትዮጵያውያን" መሆናቸውን አስታወቀች።
የፑንትላንድ የጸረ ሽብር ዘመቻ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጹ "ኢትዮጵያውያን" እንደሆኑ የገለጻቸውን 26 የአይኤስ ተዋጊዎች ፎቶ እና ስም ዝርዝር ይፋ አድርጓል።
የአይኤስ ተዋጊዎች እንደሆኑ የተገለጹት ግለሰቦች የተያዙት 'አልሚስካት' በተባለው ተራራማ አካባቢ ከተደረገው ውጊያ በኋላ መሆኑን የፑንትላንድ የጸጥታ ኃይሎች ቅዳሜ ጥር 9/2018 ዓ.ም. ገልጸዋል። የፑንትላንድ ኃይሎች እና አይኤስ ለአንድ ዓመት ገደማ በአልሚስካት ውጊያ ሲያደርጉ የቆዩ ሲሆን አይኤስ በዚህ አካባቢ ግዙፍ ምሽጎች ነበሩት።
የፑንትላንድ ኃይሎች በግዛቷ በሚንቀሳቀሰው አይኤስ ላይ የከፈቱት ሰፊ ወታደራዊ እንቅስቃሴ አካል የሆነውን ይህንን ዘመቻ ያከናወኑት በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና አሜሪካ እገዛ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የጸረ ሽብር ዘመቻው፤ "ጀግኖች የፑንትላድ ኃይሎቻችን በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች እና አሜሪካ እገዛ አልሚስካት ውስጥ አይኤስን አሸንፈዋል። ዘመቻው የመጨረሻ ደረጃ ላይ ነው" ሲል በኤክስ ገጹ ጽፏል።
ከዚህ ልጥፍ ጋርም የአይኤስ ተዋጊዎች ናቸው የተባሉ 53 ሰዎች ፎቶ፣ ስማቸው እና ዜግነታቸው ተጠቅሶ ተለጥፏል። እነዚህ "የውጭ አገር ተዋጊዎች" የኢትዮጵያ፣ ሳውዲ አረቢያ፣ ቱርክ፣ ሞሮኮ፣ ሶሪያ እና ታንዛኒያ ዜግነት እንዳላቸው ተጠቅሷል።
የፑንትላንድ የጸረ ሽብር ዘመቻ መረጃ እንደሚያሳው፤ ግማሽ ገደማው ወይም 26 ያህሉ ሰዎች ዜግነታቸው "ኢትዮጵያዊ" ነው። በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡት የየመን እና የሞሮኮ ዜጎች ናቸው። የሁለቱም አገራት ዜግነት ያላቸው ዘጠኝ፣ ዘጠኝ ሰዎች እንደተያዙ ተገልጿል።
አምስት ታንዛኒያውያን፣ ሁለት ቱርካውያን እንዲሁም ሁለት የሳውዲ አረቢያ እና ሶርያ ዜግነት ያላቸው ሰዎች እንደተያዙ የፑንትላንድ መረጃ ያመለክታል።
የውጭ አገር ተዋጊዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን በተመለከተ ቢቢሲ ሶማሊ ያነጋገራቸው የፑንትላንድ የማስታወቂያ ሚኒስትር ማሕሙድ አይዲድ ዲሪር "ከየትም ይምጡ ከየት፣ ከሩቅም ይሁን ከቅርብ ሁሉም አንድ ዓይነት ርዕዮተ ዓለም የሚከተሉ ናቸው" ብለዋል።
"ይህ [እርምጃ] የፑንትላንድ ኃይሎች ቡድኑ ላይ ተቀናጁት ስኬት እና የአይኤስ ቡድን መሸነፍ ማሳያ ነው" ብለዋል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ እንደሚናገሩት የተያዙት ሰዎች ማንነት እና ዜግነት ይፋ የተደረገው በሦስት ምክንያቶች ነው።
በቀዳሚነት የጠቀሱት ምክንያት፤ "የፑንትላንድ እና የሶማሊያ ሕዝብ የተገኘውን የጦርነት ድል፣ የተገደሉትን እና በሕይወት የተያዙትን ጠላቶች እንዲያውቁት" ለማድረግ የሚል ነው።
ሁለተኛው ምክንያት የተያዙት ሰዎች ከመጡባቸው አገራት ጋር የሚገናኝ እንደሆነ ተናግረዋል። "[ግለሰቦቹ] የመጡባቸው አገራት ዜጎቻቸው እዚህ ችግር እየፈጠሩ እና ጥፋት ለመፈጸም እያቀዱ መሆኑን እንዲረዱ ማድረግ ጠቃሚ ነው" ብለዋል።
"በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተውን ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጥ ተከትሎ እዚህ አካባቢ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ የተቀረው ዓለም እንዲያውቀው ለማድረግ" የሚለው ደግሞ በሦስተኛነት ተነስቷል።
የተያዙት ግለሰቦች ከመጡባቸው አገራት መካከል ከሶማሊያ ጋር የየብስ ወይም የባሕር ድንበር የሚጋሩት ሦስቱ ብቻ ናቸው።
ማንነት እና ዜግነታቸው ተጠቅሶ ከተዘረዘሩት ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ ሲዋጉ እንደተያዙ ሌሎች ደግሞ እጃቸውን እንደሰጡ ተገልጿል።
የማስታወቂያ ሚኒስትሩ ማሕሙድ፤ በቁጥጥር ሥር ዋሉት የውጭ አገር ተዋጊዎች ''በማንኛውም ወንጀለኛ ላይ የሚወሰደው እርምጃ" እንደሚወሰድባቸው ገልጸዋል።
"ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንደ አሸባሪዎች እንደነበራቸው ሚና በተለያየ መንገድ ይይዛቸዋል። ተራ ወታደር የነበረው ማን ነው? ተሳስቶ ወደዚህ መንገድ የገባና አሁን የሚጸጸተው የትኛው ነው? እንዲሁም በዓላማው አምኖ መሪ የነበረው የትኛው ነው? የሚለው ይታያል። እንደየተሳተፉበት የውጊያ ሁኔታ እና ደረጃቸው ተገቢው እርምጃ ይወሰድባቸዋል" ብለዋል።
ግለሰቦቹ ከመጡባቸው አገራት ጋር የተደረገ ግንኙነት ይኖር እንደሆነ የተጠየቁት ሚኒስትሩ፤ "እኛ ያነጋገርናቸውም አሉ፣ እኛን ያነጋገሩንም አሉ" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
"ዲፕሎማሲ የራሱ የሆነ አሠራር አለው። ስለዚህ ግንኙነቶች እየተደረጉ ነው፣ ተደርገዋልም። ምክንያቱም እነዚህ ግለሰቦች በአገራቸው ወንጀል ፈጽመው የጠፉ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምናልባትም አንዳንድ አገራት ላያውቁ ይችላሉ" ብለዋል።
ወንጀለኛ ሰው የሚቀጣው ወንጀሉን በፈጸመበት ቦታ እንደሆነ ያነሱት የማስታወቂያ ሚኒስትሩ፤ ነገር ግን በደኅንነት ጉዳዮች ላይ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር የጋራ ትብብር እንዳለ ጠቁመዋል።
አሁን ይፋ ከተደረጉት በተጨማሪ በፑንትላንድ እስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ ሌሎች የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው የአይኤስ አይኤስ አባላት መኖራቸውንም አክለዋል።