ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ ብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት 82 የአይኤስ አባላት በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ
በኢትዮጵያ የሽብር ተግባራትን ለመፈጸም ተመልምለዋል የተባሉ 82 የእስላማዊ መንግሥት (አይኤስ) አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት አስታወቀ።
በቁጥጥር ስር የዋሉት የሶማሊያ ራስ ገዝ ግዛት በሆነችው ፑንትላንድ የሚንቀሳቀሰው አይኤስ ክንፍ አካል መሆናቸውን መግለጫውን ዋቢ አድርገው የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ቡድኑ በፑንትላንድ አሠልጥኖ ወደተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ያሰማራቸው 82 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ከፌደራል ፖሊስ እና ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመተባበር እንደሆነ መግለጫው ጠቁሟል።
በቁጥጥር ስር ከዋሉትም መካከል ከአይኤስ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸው እና ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ እንደሚገኙበትም ዘገባዎች ጠቁመዋል።
በተጨማሪም በዓለም አቀፍ ደረጃ የአይኤስ የመረጃ ክንፍ ያደራጃቸው እና በፋይናንስ እና በሎጂስቲክስ እገዛ ሲያደርጉ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ከዋሉት መካከል እንደሚገኙበትም ተጠቅሷል።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት በመዲናዋ አዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ በሶማሌ እና በሐረሪ ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች መሆኑም ተገልጿል።
ተቋሙ አይኤስ በኢትዮጵያ ያለውን የጥፋት ተልዕኮ ለማስፋፋት እና ምልመላ ለማከናወን የሃይማኖት ተቋማትን እንዲሁም ሃይማኖትን እንደ ሽፋን ይጠቀማል ብሏል።
ከዚህም በተጨማሪ የሕዝብን አንድነት እና ተከባብሮ የመኖር እሴት የሚሸረሽሩ ብሎም ለአመጽ እና ሁከት የሚያነሳሳሱ አስተምህሮቶችን ለመስፋፋት ሙከራ ይደረግ እንደነበር በማስረጃዎች ማረጋገጡን አስታውቋል።
የአይኤስ የሶማሊያ ክንፍ በኢትዮጵያ ለመስፋፋት እና የሽብር መረብ ለመዘርጋት ሙከራ እያደረገ ስለመሆኑ ጥብቅ ክትትል ሲያደርግ መቆየቱን ተቋሙ ጠቅሷል።
ክንፉ በኢትዮጵያ "ሴሎች" ለመመሥረት የሚያደርገውን ጥረት አደረግኩት ባለው የስጋት ግምገማ "ተጋላጭነትን የሚያስከትሉ እና ወደ ብሔራዊ ደኅንነት ስጋት የሚያድጉ ተጨባጭ ግጭቶች ተለይተዋል" ብሏል።
አይኤስ ሶማሊያ- በሰሜን ምሥራቅ ሶማሊያ ተራሮች ውስጥ የመሸገው እና በአፍሪካ ውስጥ የእስላማዊ መንግስት (አይኤስ) ቡድን ማዕከልነቱ ይነገራል።
ትራምፕ ሥልጣናቸውን ከተረከቡ ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ በሶማሊያ ራስ ገዝ አስተዳደር በሆነችው ፑንትላንድ ውስጥ ከፍተኛ የአይኤስ ጥቃቶችን አቀነባባሪ እና ሌሎች ታጣቂዎች ላይ "አነጣጥሯል" ያሉትን በመፈጸም በርካታ ዋሻዎችን በማውደም ታጣቂዎች መግደላቸውን ተናግረዋል።
አይኤስ በሶማሊያ ለአስር ዓመታት ያህል ሲንቀሳቀስ የቆየ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአገር ውስጥ፣ በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ጉልህ እየሆነ ስለመምጣቱ ይገለጻል።
የፑንትላንድ ባለሥልጣናት እና ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ ባለሥልጣናት የአይኤስ-ሶማሊያ መሪ፣ ባለ ብርቱካናማ ጢሙ፣ እና መነጽር ለባሹ አብዱልቃድር ሙሚን፣ አሁን የአይኤስ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊ ነው ይላሉ።
አንዳንድ ሪፖርቶች ባለፈው ግንቦት አሜሪካ ባደረገችው የአየር ጥቃት መገደሉን ቢጠቁሙም፤ ነገር ግን እስካሁን ማረጋገጫ አልተገኘም።
የአይኤስ ቅርንጫፎች በአህጉሪቱ ከሞዛምቢክ እስከ ማሊ፣ ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እስከ ናይጄሪያ እየሠሩ ባሉበት አይኤስ-ሶማሊያ እንደ ወሳኝ ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
የአሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት እና የሶማሊያ ባለሙያዎች የአይኤስ የፋይናንስ መሠረት ቁልፍ አካል የሆነው የአል-ካራር ጽህፈት ቤት በፑንትላንድ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ በአፍሪካ እና ከዚያም ባሻገር ላሉ የቡድኑ ቅርንጫፎች የገንዘብ እና እውቀትን ይሰጣል።
የአሜሪካ የግምጃ ቤት የውጭ ሀብት ቁጥጥር ቢሮ (OFAC) እንዳስታወቀው አይኤስ ሶማሊያ በአውሮፓውያኑ 2022 የመጀመሪያ አጋማሽ በአገር ውስጥ የንግድ ድርጅቶች፣ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች፣ አርብቶ እና አርሶ አደሮች ላይ ግብር በመጣል 2 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ መሰብሰቡን አስታውቋል።
አይኤስ-ሶማሊያ ከአፍሪካም አልፎ እንደሚመለከት የሚነገር ሲሆን አይኤስ በየመን ቀይ ባሕርን አቋርጠው በኢራን ከሚደገፉ የሁቲ አማፅያን ጋር ሊመሳጠር እንደሚችልም ተንታኞች ይጠቅሳሉ።
ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የውጭ አገር ተዋጊዎች ቡድኑን በመቀላቀል አይኤስ በቁጥር እና ያለው ጥንካሬ እንዲያጎለብት አድርገውታል።
የአይኤስ-ሶማሊያ ምልምል ዋና ምንጭ በፑንትላንድ የወደብ ከተማ ቦሳሶ ባሕር አቋርጠው ወደ ውጭ አገር ለመሻገር ተስፋ የሰነቁ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ናቸው ተብሎ ይታሰባል።
አይኤስ በባሕረ ሰላጤው ሀገራት ከሚያገኙት የተሻለ ክፍያ የሚያቀርብላቸው ሲሆን፣ የቡድኑ ከፍተኛ አዛዦች ኢትዮጵያውያን እንደሆኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የፑንትላንድ የፀጥታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሙባረክ ከዚህ ቀደም ለቢቢሲ እንደተናገሩት "አይኤስ-ሶማሊያ ውስጥ 80 በመቶ ወይም ከዚያ በላይ የሚሆኑት የውጭ ተዋጊዎች መሆናቸውን ገምግመናል፣ በአብዛኛው ከሰሜን አፍሪካ፣ ከኢትዮጵያ፣ ከታንዛኒያ እና ከመካከለኛው ምሥራቅ የመጡ ተዋጊዎች ናቸው" ብለዋል
ባለፈው ጥቅምት ወር የአሜሪካ አፍሪካ ዕዝ ኃላፊ ማይክል ላንግሌይ አይኤስ በሰሜናዊ ሶማሊያ በአንድ ዓመት ውስጥ "በሁለት እጥፍ" ያደገ መስሏቸው እንደነበር ተናግረዋል።
ቡድኑ በታኅሣሥ ወር ፑንትላንድ ባሪ ግዛት ውስጥ የሚገኘውን የጦር ሰፈር በመምታት ካካሄዳቸው እጅግ የተራቀቁ ጥቃቶች መካከል አንዱን ፈጽሟል።
ቡድኑ አንድም ሶማሌያዊ በጥቃቱ አልተሳተፈም ሲል መግለጫ አውጥቷል።
12ቱ አጥቂዎች ከሰባት ሀገራት ማለትም ከታንዛኒያ፣ ከአልጄሪያ፣ ከሞሮኮ፣ ከሊቢያ፣ ከቱኒዚያ፣ ከየመን እና ከኢትዮጵያ የመጡ ናቸው።
እንቅስቃሴው ገንዘብ በማሰባሰብ ረገድም የበለጠ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል።