አደገኛው ታጣቂ ቡድን አይ ኤስ በምዕራቡ ዓለም ዳግም እየተጠናከረ ይሆን?

ባለፈው ሳምንት አውስትራሊያ ቦንዲ የባሕር ዳርቻ ላይ የተፈፀመውን አስከፊ ጥቃት "በኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ርዕዮተ ዓለም" ምክንያት የተነሳሳ ይመስላል ብለው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ከተናገሩ በኋላ የኢስላሚክ ስቴት ቡድን ዓለም አቀፍ ትኩረት ስቧል።

የሱኒ ሙስሊም የሆነው የታጣቂ ቡድን 15 ሰዎችን ሕይወት ለቀጠፈው ጥቃት ኃላፊነቱን አልወሰደም። ይሁን እንጂ ፖሊስ ጥቃቱ በተፈጸመበት አካባቢ በተገኘ ተሽከርካሪ ውስጥ "በቤት ውስጥ የተሠሩ" የአይኤስ ባንዲራዎች ከተቀጣጣይ ፈንጂዎች ጋር ተገኝተዋል ብሏል።

ጥቃቱን በመፈፀም አባት እና ልጅ ተጠርጥረው መለየታቸው ተገልጿል። አባት በጥቃቱ ወቅት በፖሊስ በጥይት ሲገድል ልጅ ክፉኛ ቆለሎ በ15 የግድያ ወንጀሎች ክስ ተመሥርቶበታል።

በአውስትራሊያ የተፈፀመው ጥቃት አይኤስ በምዕራባውያን ዒላማዎች ላይ ጥቃቶችን ለማቀነባበር ወይም ለማነሳሳት ከመሞከር ወደኋላ አለማለቱን የሚያስታውስ ነው።

ይህ ጥቃት ተፈጽሞ የቡድኑ ስም ዳግም መነጋገሪያ የሆነው ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ በሶሪያ እና በኢራቅ የሚገኙትን "የካሊፌቶቹን" [ግዛቶቹን] ካጣበት ጊዜ ጀምሮ ተጽዕኖው በእጅጉ ከቀነሰ በኋላ ነው።

አይኤስ በቦንዲ የባሕር ዳርቻ 15 ንፁኃን ከመገደላቸው አንድ ቀን አስቀድሞ በሶሪያ ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች መገደላቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቹ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ደስታቸውን ከመግለጻቸው በስተቀር ዝም ብሏል።

አሜሪካ በሶሪያ ግድያውን የፈጸመው የአይኤስ ተልዕኮን የተቀበለ ግለሰብ እንደሆነ ተናግራለች።

በጂሃድ ላይ አተኩራ የምትሠራው የቢቢሲ ሞኒተሪንግ ባልደረባዋ ማይና አል ላሚ "ፈጽሞ ያልጠፋን ነገር ተመለሰ ብለን ማውራት አንችልም" ትላለች።

ጥቃቶችን ያለጊዜው የኢስላሚክ ስቴት ተግባራት አድርጎ መፈረጅ ለስህተት እንደሚያጋልጥም ታስጠንቅቃለች።

እንዲህ ማድረግ የቡድኑን ትክክለኛውን አቅም ከማሳየት ይልቅ ፕሮፓጋንዳውን ሊያቀጣጥል እንደሚችል አስጠንቅቃለች።

ኢስላሚክ ስቴት አሁንም አለ?

አይኤስ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ በነበረበት ወቅት ግብር በመሰብሰብ፣ በትምህርት፣ በሃይማኖታዊ ፖሊስ እና በጤና አጠባበቅ ሥርዓቶች ራሱን እንደ አንድ መንግሥት አድርጎ በማቅረብ የሶሪያ እና የኢራቅ ሰፊ ቦታዎችን ያስተዳድር ነበር።

ነገር ግን በ2019 ከ70 በላይ አገራትን ያቀፈው በአሜሪካ የሚመራው ጥምረት ካሸነፈው በኋላ፣ መሪው ራሱን አጥፍቷል።

አል ላሚ እንደምትለው የቡድኑ መሥራች እና መሪ አቡበከር አል ባግዳዲ በ2019 በአሜሪካ ጥቃት ወቅት ራሱን በማጥፋቱ ቡድኑ ያለው ቅቡልነት የበለጠ ተዳክሟል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አንዳቸውም መሪዎቹ ተቀባይነት ማግኘት ወይም ዝነኛ የመሆን ዕድል አልነበራቸውም።

የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት እንዳስታወቀው በአሁኑ ወቅት በሶሪያ እና በኢራቅ እስከ 3,000 የሚደርሱ የአይኤስ ተዋጊዎች አሉ።

በተቃራኒው ቡድኑ በአውሮፓውያኑ 2014 ካሊፌት መመሥረቱን ካወጀ በኋላ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ተዋጊዎች ቡድኑን ለመቀላቀል ሲጎርፉ ነበር።

አል ላሚ የአይኤስ ጥንካሬ እየቀነሰ መምጣቱን የሚያሳየው ሌላ ምልክት የጥቃቶቹ መጠን መሆኑን ትናገራለች።

ቡድኑ በ2010 አጋማሽ ላይ በሶሪያ፣ በኢራቅ እና በምዕራቡ ዓለም ለተፈጸሙ በርካታ ከፍተኛ ጥቃቶች ኃላፊነቱን ወስዷል።

"አሁን በአብዛኛው የሚተማመነው በትናንሽ፣ ጥቃት ፈጽሞ በመሸሽ ላይ ነው" ትላለች።

ስለዚህ በምዕራቡ ዓለም አልፎ አልፎ የሚፈጸሙት ጥቃቶች በአብዛኛው "ከማዕከል በሚደረግ ማስተባበር" ሳይሆን በአይኤስ "ዓላማ የተነሳሱ" የሚፈጽሟቸው ናቸው።

ባለፈው ዓመት የኮራሳን ፕሮቪንስ (አይኤስኬፒ) በመባል የሚታወቀው የአይኤስ የአፍጋኒስታን ቅርንጫፍ በጥር ወር በኢራን ወደ 100 የሚጠጉ እንዲሁም ከሁለት ወራት በኋላ በሩሲያ ወደ 150 የሚጠጉ ሰዎች ከተገደሉበት ጥቃት ጋር በተያያዘ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዜና መሆን ችሏል።

በተጨማሪም በአውሮፓ ውስጥ ጥቃቶችን በማሴር የተጠረጠረ ሲሆን፣ አብዛኛዎቹም ከሽፈዋል።

ይሁን እንጂ አይኤስኬፒ በዚህ ዓመት በከፍተኛ ሁኔታ በመዳከሙ በአፍጋኒስታን እንኳ ጥቃቶችን ለመፈጸም ተቸግሯል።

በአሁኑ ወቅት በአይኤስ ስም የተፈጸሙ አብዛኞቹ ጥቃቶች የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ ነው።

በኢኮኖሚክስ እና ሰላም ተቋም የታተመው የ2025 ዓለም አቀፍ የሽብርተኝነት መረጃ ጠቋሚ ሪፖርት መሠረት፣ አይኤስ እና ተባባሪዎቹ "በ2024 በ22 አገራት ለ1,805 ሰዎች ሞት ምክንያት በመሆን እጅግ አደገኛ የሆነ ሽብርተኛ ድርጅት ሆኗል" ብለዋል።

አል ላሚ አይኤስ አብዛኛውን የፕሮፓጋንዳ አቅሙን አጥቷል ትላለች። "እነዚያ በሚገባ የተደራጁ እና የተራቀቁ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮዎች ነበሯቸው እና አሁን ቪዲዮዎችን ለማውጣት በጣም ይቸገራሉ።"

ነገር ግን አይኤስ አሁንም በኦንላይን ሚዲያዎቹ አማካኝነት ጥቃቶችን እንዲፈጸሙ እየቀሰቀሰ ነው።

አል ላሚ "ወጣት፣ የማኅበራዊ ሚዲያ እውቀት ያላቸው እና ቡድኑ በፕሮፓጋንዳው ላይ ያስቀመጠውን ክፍተት በትክክል የሸፈኑ የኦንላየን ደጋፊዎች ሠራዊት" ያለው መሆኑ ግን የተለየ ያደርገዋል ትላለች።

ወጣቶችን ለማግኘት እንደ ፌስቡክ እና ኢንስታግራም ባሉ መድረኮች ላይ ንቁ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

የቢቢሲ ሞኒተሪንግ ተንታኞች ብዙውን ጊዜ ስለጦር መሳሪያ መጠቀም፣ እንዴት መተኮስ እንደሚቻል እና አንድን ሰው እንዴት መግደል እንደሚቻል የሚያስረዱ "ዝርዝር መመሪያዎች" የያዙ መልዕክቶችን ያገኛሉ።

አል ላሚ ከእነዚህ ልጥፎች ውስጥ አንዳንዶቹ ልምድ ባላቸው "የሚዲያ ጂሃዲስቶች" የተጻፉ እንደሆኑ ብትገምትም፣ አንዳንዶቹ "በአይኤስ ፕሮፓጋንዳ ተጽዕኖ ስር የወደቁ እና ቡድኑ መልዕክቱን እንዲያሠራጭ የሚረዱ ተራ ወጣቶች የተዘጋጁ ናቸው" ብላ ትገምታለች።

አይኤስ በአፍሪካ እና በእስያ እያደገ ነው?

አይኤስ በመካከለኛው ምሥራቅ መቀመጫው በነበሩ አካባቢዎች ያገኝ የነበረውን ድጋፍ በማጣቱ ሌላ አማራጭ ፍለጋ እንዲያማትር አስገድዶታል።

በደቡብ እስያ፣ አይኤስ-ኮራሳን ፕሮቪንስ ወይም አይኤስኬፒ በጣም አደገኛ ከሆኑ የቡድኑ ቅርንጫፎች አንዱ እንደሆነ ይታሰባል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአፍጋኒስታን እና በሰሜን ፓኪስታን መቀመጫውን ያደረገው ይህ ቡድን 2,000 ተዋጊዎች እንዳሉት እና እንደ ታጂኪስታን እና ኡዝቤኪስታን ካሉ ሌሎች የመካከለኛው እስያ አገራት አዳዲስ አባላትን እንደሚመለምል አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የምሥራቅ እስያ ፕሮቪንስ (አይኤስኢኤፒ) ተብሎ የሚጠራው የደቡብ ምሥራቅ እስያን የሚሸፍነው እና በአብዛኛው በደቡባዊ ፊሊፒንስ ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው ቡድን ቀደም ሲል በፊሊፒንስ እና በኢንዶኔዢያ ለተከሰቱ በርካታ አስከፊ ጥቃቶች ተጠያቂ ነበር።

ይሁን እንጂ ይህ ቡድን በዚህ ዓመት ምንም ዓይነት ጥቃት አልፈፀመም።

ባለሙያዎች እንደሚሉት የአይኤስ ዋና ትኩረት አፍሪካ ነው።

በኔዘርላንድስ የሚገኘው ዓለም አቀፍ የፀረ-ሽብርተኝነት ማዕከል የደኅንነት ባለሙያ የሆኑት አድሪያን ሽቱኒ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ "አይኤስ በአህጉሪቱ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

"ይህንን ያደረጉት እንደ ሳህል (የሰሜን አፍሪካ ቀጠና) እና ምዕራብ አፍሪካ ያለውን ደካማ አስተዳደር በመጠቀም፣ በግዳጅም ሆነ በፈቃደኝነት የምዕራባውያን ወታደሮች ለቅቀው በመውጣታቸው፣ በቀጠናው ያለው አለመረጋጋት እና ለፀረ ሽብር ጥረቶች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ በመቀነሱ የተነሳ የተፈጠሩ የፀጥታ ክፍተቶችን በመጠቀም ነው።"

እንደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዘገባ፣ የኢስላሚክ ስቴት ዌስት አፍሪካ ፕሮቪንስ (አይኤስደብሎውኤፒ) ከ8,000 እስከ 12,000 ተዋጊዎች ሊኖሩት ይችላል።

አል ላሚ ቡድኑ በዚህ ዓመት ካደረጋቸው አስር ጥቃቶች ዘጠኙ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የተፈጸሙ መሆናቸውን ትናገራለች።

አይኤስ በሳህል እና ሶማሊያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም በእነዚህ አካባቢዎች ጠንካራ የአልቃይዳ ክንፍ የሆኑ የጂሃዲስቶች ፉክክር እንዳለባት ጨምራ ታብራራለች።

ሆኖም ግን በናይጄሪያ፣ በዴሞክራቲክ ኮንጎ እና በሞዛምቢክ ጠንካራ እንደሆነ ጨምራ ገልጻለች።

በእነዚህ አገራት ታጣቂዎች ብዙውን ጊዜ ክርስቲያኖችን እንዲሁም ወታደሮችን ዒላማ ያደርጋሉ።

በዲሞክራቲክ ኮንጎ የአይኤስ ተባባሪዎች በተደጋጋሚ ወረራ በሚፈጽሙባቸው አካባቢዎች ሙስሊም ያልሆኑ ሰዎች ግብር እንዲከፍሉ ለማድረግ ሞክረዋል ትላለች።

"አይኤስ በኮንጎ የሚገኙ ክርስቲያኖች ሦስት አማራጮች እንዳሏቸው ይናገራል፤ ሙስሊም መሆን፣ ጂዝያ በመባል የሚታወቀውን ግብር ለአይኤስ መክፈል ወይም መሞት ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ እነሱ [ታጣቂዎቹ] አማራጭ አይሰጧቸውም። ወደ መንደሮቻቸው ዘልቀው ከገቡ በኋላ ይገድሏቸዋል" ስትል አክላለች።

አል ላሚ እንደምትለው አይኤስ በአፍሪካ ውስጥ የሚያደርገው እንቅስቃሴ የዓለም አቀፍ የሚዲያ ትኩረት ባለመኖሩ በአብዛኛው የማይዘገብ ሲሆን ቡድኑ ራሱም በዚህ ጉዳይ ቅሬታ አቅርቦ ያውቃል።

"ባለፈው ዓመት አይኤስ ተስፋ ቆርጦ ነበር። በይፋዊ መልዕክት 'እነዚህን ሁሉ ክርስቲያኖች በአፍሪካ እየገደልን ነበር፣ የምዕራቡ ዓለም ሚዲያዎች ዘረኛ ናቸው። ግድ የላቸውም'" ማለቱን ትናገራለች።

አይኤስ በአፍሪካ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረገ ቢሆንም፣ አል ላሚ እንደምትለው በአንድ ወቅት በሶሪያ እና በኢራቅ ከነበረው ጥንካሬ ጋር "ምንም" አይወዳደርም።

"አይኤስ በመካከለኛው ምሥራቅ እንደነበረው ሁሉ በአፍሪካ ውስጥ የትኛውንም ቦታ አይቆጣጠርም። ይልቁንም በድብቅ ጥቃት በመፈጸም እና በመሸሽ ላይ ተወስኖ ነው ያለው።"

ቀጣዩ ምን ይሆናል?

የቻተም ሐውስ ከፍተኛ ፌሎ የሆኑት ዶ/ር ሬናድ ማንሱር፣ አይኤስ ከቀደመው ጊዜ በበለጠ በጣም ደካማ እንደሆነ ያምናሉ።

"በአይሲስ ሥር የኖሩት ብዙ ሰዎች ተጎድተዋል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። በመንግሥታት ተስፋ መቁረጥ ቢኖርም እንኳ "አይሲስ ከዚህ በፊት ያደርግ የነበረው ዓይነት ግፊት የለም" ብለዋል።

"እነዚያ መሠረቶች አሁን የሉም፤ ስለዚህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ ካሊፌቱ ተነስቶ ላናይ እንችላለን" ሲሉ አክለዋል። ነገር ግን በርካታ የታጠቁ ቡድኖች ለሥልጣን በሚፎካከሩባቸው አካባቢዎች አይኤስ የመስፋፋት አቅም እንዳለውም አስጠንቅቀዋል።

የደኅንነት ባለሙያው አድሪያን ሽቱኒ እንደሚሉት ትልቁ አደጋ ያለው የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ከአይኤስ ለሚመጣው ስጋት እንዴት ምላሽ መስጠት አለበት የሚለው ነው።

ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ጥቃቶችን ተከትሎ "ምላሽ የመስጠት አቀራረብ" እንደማይሠራ እና ከተለያዩ አገራት የሚመጣ ቀጣይነት ያለው ጫና አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።

"እንደ አይኤስ ያሉ ተለዋዋጭ የሆኑ ጥቃቶችን ለሚፈጽሙ ድርጅቶች አልፎ አልፎ የሚሰጥ ምላሽ በቂ አይደለም" ካሉ በኋላ "አይኤስ በቸልተኝነት ውስጥ ይደረጃል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።