ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶሪያ መንግሥት ራስ ገዝ የነበሩ አካባቢዎችን ለመቆጣጠር የሚያስችለውን ስምምነት ከኩርድ ኃይሎች ጋር ፈጸመ
የሶሪያ መንግሥት፤ በኩርድ ከሚመራው የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ጋር አፋጣኝ አገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጉን አስታወቀ። የሶሪያ መንግሥት በዚህ ስምምነት አማካኝነት አብዛኛው የአገሪቱን ክፍል በቁጥጥሩ ስር ማስገባቱን የሶሪያ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ለሁለት ሳምንት ገደማ የተካሄደውን ውጊያ የሚያስቆመው ይህ ስምምነት፤ ታጣቂዎቹ ኃይሎች በሶሪያ ወታደራዊ እና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ እንዲካተቱ እንደሚያደርግ ተገልጿል። ስምምነቱ በአጠቃላይ 14 ነጥቦችን ይዟል።
ፕሬዝዳንት አህመድ አል ሻራ በደማስቆ በሰጡት መግለጫ፤ ስምምነቱ የሶሪያ የመንግሥት ተቋማት የምስራቅ እና ሰሜናዊ ግዛቶች በሆኑት አል ሀሳካህ፣ ዴር ኤዞር እና ራቃ ላይ ቁጥጥራቸውን መልሰው እንዲያረጋግጡ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል።
ስምምነቱ የተደረሰው ፕሬዝዳንት አልሻራ በደማስቆ ከአሜሪካው የሶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ቶም ባራክ ጋር ከተወያዩ በኋላ ነው። ባራክ ስምምነቱ "ለተባበረች ሶሪያ" ትልቅ እርምጃ መሆኑን በመጥቀስ አድንቀውታል።
የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች አዛዥ ማዝሉም አብዲ በስብሰባው ላይ እንደሚገኙ ቢጠበቅም፤ በአየር ሁኔታ ምክንያት መጓዝ ባለመቻላቸው ጉብኝታቸው ወደ ሰኞ መራዘሙን አልሻራ ገልጸዋል።
አዛዥ አብዲ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልዕክት ስብሰባው መኖሩን አረጋግጠው፤ ከዋና ከተማዋ ሲመለሱ ስለ ስምምነቱ ዝርዝር መረጃዎችን ለሶሪያ ኩርዶች እንደሚገልጹ ተናግረዋል።
በኩርድ የሚመሩ ኃይሎች የራሳቸውን የራስ ገዝ አስተዳደር የመሰረቱት ከ10 ዓመት ገደማ በፊት ሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ በነበረችበት ወቅት ነው። በአካባቢው አይኤስን ለመዋጋት ለእነዚህ ኃይሎች አጋር አድርጋ የወሰደችው አሜሪካ፤ በትጥቅ እና ስልጠና ጠንካራ ድጋፍ ታደርግላቸው ነበር።
የኩርድ ኃይሎች በአሜሪካ ድጋፍ አይኤስን ከአብዛኛው የሰሜን ምስራቅ ሶሪያ ያስወጡ ሲሆን የኩርድ እና የአረብ ማህበረሰቦች በብዛት የሚኖሩባቸውን አካባቢዎችም ሲያስተዳድርሩ ቆይተዋል።
በፕሬዝዳንት አልሻራ እና በኩርድ ኃይሎች አዛዡ አብዲ በተፈረመው ስምምነት መሠረት፤ የሶሪያ ባለሥልጣናት የኩርድን የራስ-ገዝ አስተዳደር ስር የነበሩትን የሲቪል ተቋማት፣ የድንበር ኬላዎች እንዲሁም የነዳጅ እና ጋዝ ማውጫ ቦታዎችን ይረከባሉ።
የሶሪያ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ወታደራዊ እና የጸጥታ አባላት ከሚደረግላቸው ማጣራት በኋላ በአገሪቱ መከላከያ እና የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ስር ይጠቃለላሉ። በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ የሌላ አገር ዜጎች የሆኑ የአይኤስ ተዋጊዎች እና ቤተሰቦቻቸው የሚገኙባቸው እስር ቤቶችንም የሶሪያ መንግሥት ይረከባል።
የአገሪቱ መንግሥት በአንጻሩ ለኩርዶች ባህላዊ እና የቋንቋ መብቶች እውቅና ለመስጠት የገባውን ቃል በድጋሚ አረጋግጧል። የኩርድ ቋንቋን የይፋዊ ቋንቋ ማድረግ እና የኩርዶችን አዲስ ዓመት እንደ ብሔራዊ በዓል ማክበርን በዚህ ውስጥ ተካትተዋል።
ሶሪያ እ.ኤ.አ በ1946 ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ነፃነቷን ካገኘች በኋላ ለኩርዶች መብት ይፋዊ እውቅና ስትስጥ ይህ የመጀመሪያው ነበር።