ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአምስት እጥፍ የጨመረው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ የስታድየም መግቢያ ቲኬት
ጉዊዶ ፔራልታ የሒሳብ ሠራተኛ ነው። ዕድሜውን ሙሉ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድንን ሲደግፍ ኖሯል። ለ2026 የዓለም ዋንጫ ገንዘብ ማጠራቀም የጀመረው የኳታር ዓለም ዋንጫ እንደተጠናቀቀ ነው።
ነገር ግን ያጠራቀመው ገንዘብ ለጉዞው በቂ መሆኑን እርግጠኛ አይደለም።
"በኳታር የአየር ቲኬት ዋጋ 1470 ዶላር ነበር። ለአሁኑ የዓለም ዋንጫ ግን እስካሁን 6960 ዶላር ከፍያለሁ" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል። እስከ ፍፃሜው ድረስ የሚያደርሰውን ቲኬት ገዝቶ አስቀምጧል።
ያለፈው የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ አርጀንቲና ለዋንጫ ካልደረሰች የተወሰነ ቲኬት የገዛበት ገንዘብ ይመለስለታል። ነገር ግን አርጀንቲና ለዋንጫ ከደረሰች በኳታር ዓለም ዋንጫ በጠቅላላ ያወጣውን ያክል ገንዘብ ቲኬት ላይ ብቻ ያውላል ማለት ነው።
"እግር ኳስ ቢዝነስ እንደሆነ ይገባኛል። ይህኛው ግን ከቁጥጥር ውጭ ሆነ። ይህ የቢዝነስ የዓለም ዋንጫ ነው" ይላል።
ጉዊዶ ዕድለኛ ከሚባሉ ሰዎች መካከል ነው። እንደእሱ ላሉ ቀንደኛ ደጋፊዎች ብሔራዊው የእግር ኳስ ማኅበር ርካሽ ቲኬት ቀድሞ እንዲደርሳቸው ያደርጋል።
ሌሎች ደጋፊዎች ለቲኬት ከዚህም በላይ ይከፍላሉ። በተጨማሪም ለጉዞ እና ለሚያርፉበት ቦታ የሚከፍሉት ወጪ አለባቸው።
የዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከሌሎቹ በተለይ እጅግ ውድ ነው የሚል ቅሬታ የሚሰማው ለዚህ ነው።
እጅግ ውዱ የዓለም ዋንጫ
ዩይትድ ስቴትስ፣ ሜክሲኮ እና ካናዳ የ2026 የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ አዘጋጅ ሀገራት ናቸው። ጨዋታዎቹ በ16 ስታድየሞች የሚከናወኑ ሲሆን፣ አብዛኞቹ በአሜሪካ ይደረጋሉ።
በዓለም ዙሪያ ያሉ የእግር ኳስ ደጋፊዎች በጉጉት ሲጠብቁት የነበረው የቲኬት ዋጋ ባለፈው ታኅሣሥ ይፋ ተደርጓል።
እንደ ቀደመው ጊዜ የቲኬት ዋጋዎች የሰዎችን አቅም በማገናዘብ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ በሚለው ተደልድለዋል።
ነገር ግን በርካታ የእግር ኳስ ደጋፊዎችን ያስደነገጠው አነስተኛ የሚባለው ዋጋ እንኳ ከዚህ ቀደም ከነበሩት ውድድሮች ዋጋ ከፍ ያለ መሆኑ ነው።
እጅግ ውድ ከሚባለው የመጀመሪያው ክፍል እስከ አራተኛው ክፍል ድረስ የሁሉም ቲኬቶች ዋጋ በፊፋ የተዘጋጀ ነው።
አብዛኞቹ ቲኬቶቹ እጅግ ውድ በሚባሉት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ክፍል የተመደቡ ናቸው።
ቲኬቶቹን አሁን በፊፋ ኦፊሴላዊ የቲኬት መሸጫ ገፅ ማግኘት አይቻልም። አብዛኞቹ ቲኬቶች ተሽጠው እንዳለቁ ይታመናል።
ክፍል ሦስት ያሉ ቲኬቶች ግን አሁንም ገበያ ላይ ናቸው። በዚህ ክፍል ውስጥ ያሉ ቲኬቶች ለምድብ ጨዋታ የሚሆኑ ሲሆኑ፣ ዋጋቸው ከ140 እስከ 1120 ዶላር ይደርሳል። ለፍፃሜው ጨዋታ ደግሞ ዋጋ 4185 ዶላር ሊሆን ይችላል።
ቲኬቶቹን በጊዜ ገዝተው መልሰው የሚሸጡ አሉ። የፍፃሜውን ጨዋታ ቲኬት መልሰው ከሚሸጡ ሰዎች መግዛት ይቻላል። የፊፋ ድረ-ገፅ እንደሚያሳየው የዓለም ዋንጫ ፍፃሜ ጨዋታን ለማየት ከ8749 ዶላር እስከ 46 ሺህ ዶላር ማውጣት ግድ ይላል።
የአውሮፓ እግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበር "እጅግ ውድ የቲኬት ዋጋ" ሲል ቅሬታውን አሰምቷል። ማኅበሩ የቲኬት ዋጋው ከኳታር የዓለም ዋንጫ ጋር ሲነፃፀር በአምስት እጥፍ ከፍ ያለ ነው ይላል።
የፊፋው ፕሬዝደንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ባለፈው ታኅሣሥ ለዓለም የስፖርት ስብሰባ ዱባይ በተገኙበት ወቅት የቲኬት ዋጋውን ሲከላከሉ ተሰምተዋል።
"ያለፊፋ በዓለማችን 150 ሀገራት እግር ኳስ አይኖርም። እግር ኳስ እውን የሆነው ከዓለም ዋንጫ በምናገኘው ገቢ ነው። ገቢውን መልሰን በመላው ዓለም ፈሰስ እናደርጋለን" ብለዋል።
"ይህ ውድድር በዓለም ዙሪያ ላሉ ደጋፊዎች ምን ማለት እንደሆነ እያወቅን ሁሉንም ደጋፊ በስታድየም አለማስተናገዳችን ይቆጨናል።"
ፊፋ ለትችቱ የሰጠው የ60 ዶላር ምላሽ
ፊፋ ለቀረበበት ትችት ምላሽ ይሆን ዘንድ ለብሔራዊ ቡድን ደጋፊ ማኅበራት የሚሰጥ የ60 ዶላር ቲኬት ይፋ አድርጓል።
ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ እንደሚለው ይህ ዋጋ ቀንደኛ የሚባሉ ደጋፊዎች ከ4185 ይልቅ 60 ዶላር ከፍለው ፍፃሜውን ሳይቀር እንዲመለከቱ ያስችላል።
ፊፋ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ከስታድየም አቅም 8 በመቶው በውድድሩ ከሚሳተፉ ሀገራት ለሚመጡ ማኅበራት እንደሚሆን አስታውቋል። ከዚህ 10 በመቶው ደግሞ 60 ዶላር ከፍለው ለሚገቡ ደጋፈዎች የሚሆን ነው።
የአውሮፓ እግር ኳስ ደጋፈዎች ማኅበር ይህ እርምጃ ፊፋ "ለቀረበበት አሉታዊ ትችት ምላሽ እንዲሆን የተዘጋጀ ማታለያ" ሲል ቅሬታውን አሰምቷል።
ቢቢሲ በዳላስ ኤቲኤንድቲ ስታድየም የመግቢያ ዋጋ ቲኬት ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል ተመልክቷል።
አርጀንቲና በዚህ ስታድየም ከዮርዳኖስ እና ከኦስትሪያ ጋር የምድብ ጨዋታዎቿን ታደርጋለች። ጉዊዶ እኒህን ጨዋታዎች ለመመልከት አቅዷል።
የፊፋ ድረ-ገፅ እንደሚለው የዳላስ ስታድየም 70 ሺህ 122 ተመልካቾች የማስተናገድ አቅም አለው።
ድረ-ገፁ በክፍል አራት (ዝቅተኛው የቲኬት ዋጋ) ስንት ወንበሮች እንደተደለደሉ ይፋ አላደረገም። ዳላስ ስታድየም ደግሞ ቢቢሲ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ አልሰጠም።
ነገር ግን ከዳላስ ሰታድየም ጋር ከሚሠራው ሲትጊክ ድረ-ገፅን በመጠቀም ቢቢሲ ያጣራው መረጃ በክፍል አራት በዚህ ስታድየም የተደለደሉ ወንበሮች 0.39 በመቶ ብቻ መሆኑን ያሳያል። ይህም 279 ብቻ ነው ማለት ነው።
ከመግቢያ ቲኬት ውጭ ያለው ወጪ
የደጋፊዎች ወጪ የመግቢያ ቲኬት ላይ አያቆምም። ጉዊዶ እንደሚለው ለኳታር ዓለም ዋንጫ የመደበው ገንዘብ 5 ሺህ ዶላር ነበር። ይህ ገንዘብ ቲኬት፣ የአውሮፕላን ጉዞ፣ ሆቴል እና ዕለታዊ ወጪዎችን ሸፍኖለታል።
"ኧረ እንደውም የተረፈኝ ገንዘብ ነበር" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
ለ2026 የዓለም ዋንጫ ስድስት ወራት ቢቀሩትም እስካሁን የሚያርፍበትን ቦታ ማግኘት አልቻለም።
ቡኪንግ ዶት ኮም እንደሚያሳየው ለሚመጣው ሰኔ በዳላስ ዝቅተኛው የሆቴል ዋጋ ለአንድ ምሽት 190 ዶላር ነው። ስካይስካነር ደግሞ ከአርጀንቲና ዋና ከተማ ቦነስአይረስ ወደ ዳላስ ዝቅተኛው የአውሮፕላን ቲኬት 1260 ዶላር ነው ይላል።
የዓለም ዋንጫ ሲቃረብ የስታድየም መግቢያ ቲኬት ዋጋ እንዲሁም የሆቴል እና የጉዞ ወጪዎች ከፍ እያሉ ይመጣሉ።
አሜሪካ የሚኖሩ የእግር ኳስ ደጋፊዎችም የዋጋው ነገር ያሳሰባቸው ይመስላል።
የዓለም ዋንጫ ከሚዘጋጅባቸው ስታድየሞች መካከል አንዱ ሜትላይፍ ስታድየም ነው። የአሜሪካን ፉትቦል ቡድኖቹ ኒው ዮርክ ጃያንትስ እና ኒው ዮርክ ጄትስ ስታድየም ነው።
የ23 ዓመቷ የኒው ዮርክ ነዋሪ ሻርለት ባዎል የቲኬት ዋጋ ከአቅሟ በላይ እንደሆነ ትናገራለች።
"የዓለም ዋንጫን እወደዋለሁ። ነገር ግን ዋጋው እጅግ ውድ ነው። በጣም የሚገርም ነገር ነው" ስትል ለቢቢሲ ሐሳቧን ታጋራለች።
"እንደተረሳን ነው የምንቆጥረው። እዚሁ ከተማችን አንድ ትልቅ ውድድር እየተካሄደ ነገር ግን ውድ በመሆኑ ምክንያት መታደም አንችልም" ትላለች።
ሌሎች ክፍለ ዓለማት የሚገኙ የእግር ኳስ ደጋፊዎችም ቅሬታቸውን እየገለፁ ነው።
"ጋና በቶሮንቶ፣ ቦስተን እና ፊላደልፊያ ነው የምትጫወተው። እኒህን ጨዋታዎች ለማየት 15 ሺህ ዶላር ያስፈልጋል" የሚለው ጋናዊው የስፖርት ጋዜጠኛ ሙፍታዉ አብዳላይ ነው።
"የምናርፍበት ቦታ፣ ምግብ እና ከቦታ ቦታ ለመዘዋወር በጠቅላላለው ከ10 እስከ 15 ሺህ ዶላር ያስፍለጋል" ሲል ለቢቢሲ ይናገራል።
"የዋጋ መጨመሩ ተቀባይነት የለውም። በጋና እና አፍሪካ ያለው ምጣኔ ሀብት ከሌሎች ክፍለ ዓለማት ጋር የሚነፃፀር አይደለም። እግር ኳስ እንወዳለን። ነገር ግን ከዚያ በላይ ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ አለ።"