በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈው የማያውቁ 10 ሀገራት

የ2025 የአፍሪካ ዋንጫ በደማቅ ሥነ ሥርዓት በሞሮኮ አስተናጋጅነት ተጀምሯል።

በምህጻረ ቃሉ አፍኮን ተብሎ የሚጠራው ይ 24 ሀገራት የሚሳተፉበት ይህ የእግር ኳስ ውድድር በአፍሪካ ትልቁ የእግር ኳስ ውድድር ነው።

አፍኮን በአውሮፓውያኑ 1957 አሀዱ ብሎ ሲጀምር ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን ብቻ ነበሩ የተሳተፉት። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ 44 ሀገራት ቢያንስ አንድ ጊዜ በውድድሩ ተሳትፈዋል።

የግብፅ፣ የናይጄሪያ፣ የካሜሩን እና የጋና በውድድሩ ትልቅ ስም ያላቸው ብሔራዊ ቡድኖች ናቸው።

ምንም እንኳ በቅርብ ዓመታት ውድድሩ እየሰፋ እንዲሁም የሚሳተፉ ሀገራት ቁጥር እየጨመረ ቢመጣም እስካሁን በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈው የማያውቁ ሀገራት አሉ።

ለመሆኑ እስካሁን በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፈው የማያውቁ ሀገራት እነማን ናቸው?

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ

አንዳንዶች ይህች ሀገር እስካሁን በአፍኮን አለመሳተፏ ያስደንቃቸዋል።

ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ ችሎታ ያላቸው ተጫዋቾች እጥረት ያለባት ሀገር አይደለችም። ነገር ግን ሀገሪቱ ሰላም የራቃት መሆኗ ለእግር ኳሷ ዕድገት መንቀራፈፍ አስተዋፅዖ አድርጓል።

በርካታ በአውሮፓ እና በአፍሪካ ሀገራት ክለቦች የሚጫወቱ ተጫዋቾች አሏት። ነገር ግን ብሔራዊ ቡድኑ በተለያዩ ምክንያቶች የሚገባውን ጥንካሬ ያገኘ አይመስልም።

ማዕከላዊ አፍሪካን ሪፐብሊክ በተደጋጋሚ ለአፍሪካ ዋንጫ ትደርሳለች ተብሎ ቢጠበቅም እስካሁን ሊሳካላት አልቻለም።

ጂቡቲ

ወታደራዊ እና ስትራቴጂካዊ ማዕከል ተደርጋ የምትቆጠረው የአፍሪካ ቀንድ አገሯ ጂቡቲ ለእግር ኳስ ትልቅ ቦታ የሰጠች አይመስልም።

የጂቡቲ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በአውሮፓውያኑ 1979 ነው የተመሠረተው። የአፍሪካ እግር ኳስ የበላይ አስተዳዳሪ ካፍን የተቀላቀለው በ1986 ሲሆን የፊፋ አባል የሆነው ደግሞ በ1994 ነው።

ብሔራዊ ቡድኑ የመጀመሪያውን ጨዋታ ያደረገው በ1947 ከኢትዮጵያ ጋር ነበር።

ምንም እንኳ የጂቡቲ እግር ኳስ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጥ ቢያሳይም ፉክክር የሚስተዋልበት ውድድር አለመኖሩ፣ መሠረተ-ልማት አለመሟላቱ እና የልምድ ማጣት እንቅፋት ተደርገው ይቆጠራሉ።

ኤስዋቲኒ

ለዓመታት ስዋዚላንድ በተሰኘ ስሟ ትታወቅ የነበረችው ሀገር በደቡብ አፍሪካ እግር ኳስ ጥላ ሥር ተደብቃ ቆይታለች።

የኤስዋቲኒ ትልቁ ስኬት በ2010 የአፍኮን ማጣሪያ ለሁለተኛ ዙር ማለፏ ሲሆን፣ በምድብ ማጣሪያ ተሸንፋ መውደቋ ይታወሳል።

በ2025 የአፍኮን ማጣሪያ ኤስዋቲኒ ከጊኒ ቢሳው አቻ ስትወጣ ዚምባብዌን መርታት ችላለች። ምንም እንኳ ይህ ውጤት ትልቅ የሚባል ቢሆንም ለአፍኮን ሊያሳልፋት ግን አልቻለም።

በአሁኑ ወቅት ኤስዋቲን በፊፋ የእግር ኳስ ሰንጠረዥ ከአፍሪካ 44ኛ ከዓለም ደግሞ 148ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ሌሶቶ

ደቡባዊ አፍሪካ ውስጥ የምትገኘው ትንሿ የባሕር በር አልባዋ ሀገር ሌሶቶ ለዓመታት በአፍሪካ እግር ኳስ ስሟን ለመትከል ስትሞክር ቆይታለች።

ከአውሮፓውያኑ 1992 ጀምሮ የፊፋ አባል የሆነችው ሌሶቶ በአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፋ አታውቅም።

የበጀት እጥረት፣ የአሠልጣኞች በፍጥነት መቀያየር እና ጥራት ያለው የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረግ ብሔራዊ ቡድኑ ትልቅ ደረጃ እንዳይደርስ ምክንያት ተደርገው ይወሰዳሉ።

አልፎም እግር ኳሱ እንዲያድግ የሚያስችል የረዥም ጊዜ ዕቅድ አለመኖሩ ስኬታማ እንዳትሆን አድርጓታል የሚሉ አሉ።

ቻድ

ቻድ በአፍሪካ ዋንጫም ሆነ በዓለም ዋንጫ ተሳትፋ አታውቅም።

የማጣሪያ ጨዋታዎችን ተሻግራም አታውቅም። ካፍ ባስተላለፈው ቅጣት ምክንያት በ2019 እና በ2021 የአፍሪካ ዋንጫዎች ላይ እንዳትሳተፍ ታግዳም ታግዳለች።

በፊፋ ሰንጠረዥ ግርጌ ላይ ከሚገኙ ሀገራት ተርታ የምትመደበው ቻድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እግር ኳሷን ለማነቃቃት እየሞከረች ትገኛለች።

ሶማሊያ

ስፖርት በሶማሊያ እንዳያድግ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል ፖለቲካዊ አለመረጋጋት ዋነኛው ጉዳይ ተደርጎ ይጠቀሳል።

የውቅያኖስ ከዋክብት በተሰኘ ስም የሚታወቀው ብሔራዊ ቡድኗ ከአውሮፓውያኑ 1986 ጀምሮ በሜዳው ተጫውቶ አያውቅም።

ሶማሊያ በእግር ኳስ ደረጃዋ በአሁኑ ወቅት ከዓለም 200ኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ስትሆን፣ በዓለም አቀፍ እግር ኳስ ለመሳተፍ መሠረት ለመጣል እየታገሉ ካሉ ሀገራት መካከል ናት።

ሳኦ ቶሜ እና ፕሪንሲፔ

አነስተኛ ደሴት የሆነችው ሳኦ ቶሚ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጧ እና ምጣኔ ሀብቷ እግር ኳሷ እንዳያድግ ምክንያት ሆነዋል።

የሕዝብ ቁጥሯ ከ200 ሺህ የሚያንሰው ይህች ትንሽ ሀገር ውስጥ የሚካሄዱ የእግር ኳስ ውድድሮች ደካማ የሚባሉ ናቸው።

ቢሆንም በካፍ እና በፊፋ የማጣሪያ ውድድሮች ላይ ከመሳተፍ ያገዳት የለም። ነገር ግን ለአፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ፈተና ሆኖባታል።

ደቡብ ሱዳን

በዓለም በዕድሜ ትንሿ ሀገር የሆነችው ደቡብ ሱዳን እግር ኳሷን ከዜሮ ለመገንባት እየሞከረች ትገኛለች።

የመሠረተ-ልማት፣ የገንዘብ እና የፖለቲካ ችግር ያለባት ደቡብ ሱዳን ብሔራዊ ቡድኗን ለሀገር ግንባታም እየተጠቀመችበት ነው።

በአፍሪካ 47ኛ ከዓለም ደግሞ 169ኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን በአፍኮን ተሳትፋ አታውቅም።

ሺሼልስ

የሲሼልስ ምጣኔ ሀብት ቱሪዝም ላይ ጥገኛ ነው። የምትታወቅበት የውድድር ስፖርት ዘርፍ የላትም።

በሲሼልስ እና በሌሎች የአፍሪካ ሀገራት መካከል ያለው የእግር ኳስ ልዩነት ሰፊ የሚባል ነው።

ሲሼል ለአፍሪካ ዋንጫ ደርሳ አታውቅም። በማጣሪያ ጨዋታዎችም መጨረሻ ሆና ነው የምታጠናቅቀው። አልፎም በሰፊ የጎል ልዩነት መሸነፍ ብርቋ አይደለም።

ኤርትራ

ከሌሎቹ ሀገራት በተለይ ኤርትራ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ ስትሳተፍ አትታይም።

ከውድድሮቹ ራሷን ማግለል አሊያም አድማ መምታት የተለመዱ ዜናዎች ናቸው። በሀገሪቱ ያለው የፖለቲካ ሁኔታ የእግር ኳሱን ዕድገት ወደኋላ ጎትቶታል።

በኦፊሴላዊ የእግር ኳስ ውድድሮች ላይ ባለመሳተፏ በፊፋ የእግር ኳስ ሰንጠረዥ ውስጥም አልተካተተችም።