ትራምፕ የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች 'ደህንነት በራቃቸው ከተሞች እንደማይካሄዱ' አስታወቁ

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የ2026 ዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ጨዋታዎችን ደህንነት የራቃቸው ናቸው ብለው ከሚያስቧቸው ከተሞች እንደሚቀይሩ ተናገሩ።

በሚቀጥለው ዓመት ክረምት ላይ 48 ቡድኖች የሚጋጠሙበትን የዓለም ዋንጫ 11 የአሜሪካ ከተሞች ለማስተናገድ ተዘጋጅተዋል።

የ2026 የዓለም ዋንጫን ካናዳ እና ሜክሲኮ አሜሪካ በጋራ ያሰናዳሉ።

ውድድሩን የማዘጋጀት እና አስተናጋጅ ከተሞችን የመምረጥ ኃላፊነት ያለበት ፊፋ በዚህ ውሳኔ ምክንያት የሎጂስቲክስ ችግሮች ሊገጥሙት እንደሚችል ይጠበቃል።

ትራምፕ ይህንን ለውጥ ለማድረግ ሥልጣን ይኑራቸው አይኑራቸው ግልጽ ባይሆንም ከፕሬዚዳነት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ ጋር ግን የቅርብ ወዳጅ ናቸው።

ትራምፕ በኦቫል ኦፊስ ለተገኙ ጋዜጠኞች "ይህ ለዓለም ዋንጫ መልካም ነው" ብለዋል።

"እኔ ደህንነቱ የተጠበቀ አይደለም ብዬ ካሰብኩ ወደ ሌላ ከተማ እናዞረዋለን።"

የዓለም ዋንጫን የሚያስተናግዱት 11 ከተሞች አትላንታ፣ ቦስተን፣ ዳላስ፣ ሂውስተን፣ ካንሳስ ሲቲ፣ ሎስ አንጀለስ፣ ማያሚ፣ ኒው ዮርክ/ኒው ጀርሲ፣ ፊላደልፊያ፣ ሳንፍራንሲስኮ እና ሲያትል ናቸው።

ትራምፕ ጥያቄ የቀረበላቸው በዲሞክራቶች በሚመሩት ሲያትል እና ሳን ፍራንሲስኮ ስለሚካሄዱ ጨዋታዎች ነበር።

ሁለቱም ከተሞች ስድስት ጨዋታዎችን እንደሚያዘጋጁ የወጣው ድልድል ያሳያል።

በሚቀጥለው ዓመት ስምንት ጨዋታዎችን እንዲሁም የ2028 ኦሊምፒክ የምታስተናግደው እና የዲሞክራቶች ጠንካራ ግዛት የሆነችው ሎስ አንጀለስንም ጠቅሰዋል።

"ማንኛውም ከተማ ለዓለም ዋንጫ፣ ወይንም ለኦሊምፒክ ትንሽም ቢሆን አደገኛ እንደሆነ ካሰብን፣ ጨዋታዎች በተለያዩ ከተሞች ስለሚደረጉ በተለይ ለዓለም ዋንጫ፣ እዚያ እንዲካሄድ አንፈቅድም። ወደ ሌላ አካባቢ እንቀይረዋለን" ብለዋል።

ትራምፕ በተደጋጋሚ በአሜሪካ የተለያዩ ግዛቶች የሚታዩ ወንጀሎችን መቅረፍ የአጀንዳቸው ማዕከል መሆኑን ይናገራሉ።

ምንም እንኳ እአአ ከ2023 ጀምሮ ወንጀል እየቀነሰ መምጣቱን መረጃዎች ቢያሳዩም ባለፈው ወር የብሔራዊ ዘብ አባላትን እና የፌደራል ኃይሎችን በዋሺንግተን ዲሲ አሰማርተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ወደ ሜንፊስ እና ቺካጎ ወታደሮችን ለመላክ እቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር 2000 የብሔራዊ ዘብ አባላትን በሎስ አንጀለስ የሚገኙ ሰነድ አልባ ስደተኞችን እና የተቃውሞ ሠልፎችን ለመቆጣጠር አሰማርተዋል።

የዓለም ዋንጫ የምድብ ድልድል እአአ ዴሴምበር 5 በዋሺንግተን ዲሲ ይወጣል።

ጨዋታው እአአ በ2026 ከሰኔ 11 እስከ ሐምሌ 19 ድረስ ይካሄዳል።

ትራምፕ ስለዓለም ዋንጫ ሲናገሩ ይህ የመጀመርያቸው አይደለም።

በግንቦት ወር ሩሲያ በዓለም ዋንጫ መሳተፏ ከዩክሬን ጋር የምታደርገውን ጦርነት ለማቆም "እንደ ማበረታቻ" ያገለግላል ብለው ነበር።

ይህ ንግግራቸው የተሰማው ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ፊፋ እና የአውሮፓ እግር ኳስ ማኅበር የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኗን ከየትኛውም የዓለም አቀፍ ውድድሮች ካገዱ በኋላ ነው።

በመጋቢት ወር ደግሞ ዋንጫውን በጥምረት በሚያዘጋጁት አሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ መካከል ያለው ፖለቲካዊ ውጥረት ለውድድሩ ጥሩ ነው ሲሉ ተናግረዋል።