የቀድሞው የ'አርሚ 15' አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ ገብረ ለምን በቁጥጥር ሥር ዋሉ?

የትግራይ የፀጥታ ኃይሎች የቀድሞው የ'አርሚ 15' አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ ገብረን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን የቢቢሲ ምንጮች ገለጹ።

"ማንም ሰው ከሕግ በላይ አይደለም። ስለዚህ ታስሯል" ሲሉ መረጃውን ለቢቢሲ የሰጡት አንድ ከፍተኛ የሠራዊቱ አዛዥ ተናግረዋል።

ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ፤ ህወሓት ያካሄደውን ጠቅላላ ጉባኤ የሚደግፉትን እና በአቶ ጌታቸው ረዳ ይመራ የነበረው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ለውጥ እንዲደረግበት የጠየቁትን የክልሉ ታጣቂ ኃይሎች አዛዦችን በመቃወም ይታወቃሉ።

"ከኮር በላይ" በሚል የሚታወቁትን አዛዦች የተቃሙት ብርጋዴር ጄነራሉ፤ ካለፈው ዓመት ጥር ጀምሮ ከሠራዊቱ ታግደው ቆይተዋል።

የክልሉ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ቅዳሜ ማታ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ፤ "የሥነ ምግባር እና ሕግ ጥሰት ፈፅመዋል" ባላቸው አባላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱን አስታውቋል።

ስማቸውን ይፋ ሳያደርግ "አንዳንድ ወታደራዊ አመራሮች" ያላቸው አካላት "የወታደሩን ሕግ እና አሠራር በመጣስ ባልተገባ ድርጊት ውስጥ እየተሳተፉ መሆናቸው ታውቋል" ሲልም ከስሷል።

አቶ ጌታቸው ረዳ በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ የኮማንደሩን እስራት ተቃውመዋል።

"ስለ ጉዕሽ ገብረ መታፈን ብዙ ማለት አልፈልግም። ስለማንነቱ እና ጀግንነቱ ሁሉም ያውቃል ብዬ አስባለሁ" በማለት በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ኃይሎች ተስፋ ቆርጠው እንዳይበተኑ በማድረግ "ተዓምር" መሥራታቸውን አስታውሰዋል።

"ምንድን ነው የተከሰተው? ከአንድ ዓመት በፊት ከኃላፊነቱ ያለአግባብ የተነሳ ሰው ምን አጠፋ? ከጠላት ጋር ግንኙነት መፍጠር ማለትስ ምንድነው?" ያሉት አቶ ጌታቸው "ጉዕሽ እና አጋሮቹ መርኅን ስለተከተሉ ብቻ" ለዚህ መዳረጋቸው ጽፈዋል።

"መታሰር የሚገባቸው ሌቦች በሕግ ስም ጀግኖችን የሚያፍኑባት ትግራይ ከኅልውናዋ ፀር የቆመች ናት። ለትግራይ የሚቆረቆር ሁሉ ቀጣፊዎቹን መቃወም አለበት" በማለትም አክለዋል።

የክልሉ የሰላም እና ፀጥታ ቢሮ መግለጫ "በተደጋጋሚ ተፈጽመዋል" ያላቸው "ስህተቶች" ውስጣዊ ሰላምን ለማወክ መሥራት፣ በወታደሮች እና በአመራሩ መካከል ያለውን እምነት ለመሸርሸር መሞከር እና ወታደራዊ ኃይሉ ሥልጠና እንዳያደርግ እንዲሁም ለተልዕኮ እንዳይዘጋጅ ማወክ እንደሆኑ ገልጿል።

ብርጋዴር ጄነራል ጉዕሽ በትግራይ የፀጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር የዋሉትም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ተጠቅሷል።

"ጉዳዩ በሠራዊቱ ሕገ ደንብ መሠረት በወታደራዊ ፍርድ ቤት የሚታይ ይሆናል" ሲሉ የቢቢሲ ምንጭ ተናግረዋል።

ቢቢሲ የትግራይ ሠራዊት ሕገ ደንብ የተባለውን ሰነድ ማግኘት አልቻለም።

የክልሉ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ "በተመሳሳይ ወንጀል ውስጥ በሚሳተፉ ተጠርጣሪዎች" ተጨማሪ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቋል።

በትግራይ ጦርነት ከተዋጉ የሠራዊቱ አባላት መካከል 175 የሚደርሱ አዛዦች፣ ምክትሎቻቸው፣ የሎጂስቲክስ ኦፊሰሮች የሚገኙባቸው ሲሆን አብዛኞቹ የህወሓት የቀድሞ ታጋዮች ናቸው።

የትግራይ መከላከያ ኃይል ብሎ ራሱን የሚጠራው ሠራዊት መቀለን ሰኔ 2013 ዓ. ም. ዳግመኛ መቆጣጠሩን ተከትሎ አምስት ከፍተኛ የሠራዊቱ አዛዦች "እኛ የህወሓት ሠራዊት ነን" ብለው ማወጃቸው ይታወሳል።

ባለፈው ዓመት ጥር ወር ላይ ደግሞ የትግራይ ሠራዊት ከፍተኛ ኮማንደሮች በፕሪቶሪያ ስምምነት የተመሠረተው የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተጣለበትን ግዴታ እየተወጣ ስላልሆነ ለውጥ እንዲደረግበት እንዲሁም "ደካማ አመራሮቹ" እንዲተኩ መወሰናቸውን ባሳወቁበት ወቅት ወደ 10 የሚሆኑ ከፍተኛ አዛዦች ስብሰባ ረግጠው ወጥተዋል።

ጊዜያዊ አስተዳደሩ ኃላፊነቱን ካለመወጣቱ ባሻገር "ዓላማውን እንዳላሳካ፣ የሕዝብን ፍላጎት እንደከዳ እና የውጭ ኃይሎች መጠቀሚያ እንደሆነ" በመግለጽ ከስሰዋል።

ይሄንን ተከትሎም ከትግራይ ወታደራዊ አመራሮች በተቃራኒው በመቆም የተወሰኑ ወታደሮች የራሳቸው ኃይል ሲያቋቁሙ የተወሰኑት ደግሞ ከአመራርነታቸው መነሳታቸው ታውቋል።

አብዛኞቹ በእስር የቆዩና ጡረታ ወጥተው የነበሩ የትግራይ ተወላጅ የፌደራል ሠራዊት አዛዦች በጦርነቱ ወቅት የትግራይ ኃይሎችን ተቀላቅለዋል።

የትግራይ ኃይሎች አደረጃጀት ምን ይመስላል?

በጦርነቱ ወቅት በትግራይ በኩል "ማዕከላዊ ዕዝ" በሚል የሚጠራው አደረጃጀት ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሲሆን፤ ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ በሌላ መዋቅር ተተክቷል።

'ወታደራዊ ካውንስል' የተባለው ይህ ከፍተኛ አደረጃጀት በጀነራል ታደሰ ወረደ የሚመራ ሲሆን፤26 ወታደራዊ አዛዦች የያዘ ነው።

አሁን ላይ የትግራይ ኃይሎች የተደራጁት በሦስት ግንባሮች ማለትም በምዕራብ፣ በደቡብ እና በደቡብ ምሥራቅ ሲሆን 17፤ አርሚዎች አሉ። እያንዳንዳቸውም ሦስት ኮሮች አሏቸው።

ከታጣቂዎቹ በተገኘ መረጃ መሠረት፤ እያንዳንዳቸው በአርሚዎች እና ኮሮች በሚጠሩት ዕዞች ውስጥ እያንዳንዳቸው ሦስት ኣዛዦች (ኮማንደር፣ ምክትል ኮማንደር እና ኮሚሳር/የሎጂስቲክስ ኃላፊ) አላቸው።

ኮሚሳሮቹ [ምክትል ኣዛዦቹ] በፖለቲካው እንቅስቃሴ ውስጥ ቀጥተኛ ተሳትፎ አላቸው።

በእያንዳንዱ አዛዥ ስር የተዋቀረው ኮሚሳር ከህወሓት ጋር ቀጥተኛ ግንኙት ያለው ሲሆን፤ የፖለቲካ ግንባታ እና ስርፀት [ኢንዶክትሪኔሽን] ለማስኬድ የተፈጠረ መዋቅር እንደሆነ ይነገራል።

ብዙ ታጣቂዎች በአሠራሩ ደስተኛ እንዳልነበሩ ቢገልፁም፤ በወቅቱ ግን "የውጭ ጠላቶችን መዋጋትን" ቅድሚያ በመስጠት ቅድሚያ የሰጡት ጉዳይ እንዳልነበር ተናግረዋል።

በትግራይ ኃይሎች እና በፌራል መንግሥቱ መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ በትግራይ ከ275,000 በላይ ተዋጊዎች እንደነበሩ መገለጹ ይታወሳል።

በብዛት ነባር የህወሓት ታጋዮች አመራር ላይ ሲሆኑ ወጣት ተዋጊዎች ከሥራቸው ይገኛሉ።