ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የአውሮፓ ግራ መጋባት ደስታን ይፈጥራል" - በግሪንላንድ ጉዳይ የሩሲያ አቋም ምን ይመስላል?
ዶናልድ ትራምፕ የሚናገሩትን ሲሰሙ ሩሲያ እና ቻይና ኃይላቸውን አጠናክረው ግሪንላንድ ጠረፍ ላይ እየተጠባበቁ ያሉ ሊመስልዎት ይችላል ይላል የቢቢሲው ተንታኝ ስቲቭ ሮዘንበርግ።
"የሩሲያ አጥፊ የጦር መሣሪያዎች አሉ፤ የቻይናም አጥፊ መሣሪያዎች አሉ። ከዚህም በላቀ የሩሲያ ሰርጓጅ መርከቦች በየቦታው ሰፍረዋል" ሲሉ ፕሬዝደንቱ በቅርቡ ተናግረዋል።
ለዚህ ነው ግሪንላንድን መቆጣጠር አስፈላጊ የሆነው ሲሉ የአሜሪካው ፕሬዝደንት መከራከሪያ ያቀርባሉ።
ሩሲያ ግሪንላንድን ለመቆጣጠር እያቀደች ሳለ በአሜሪካ ዕቅዷ ከሽፎባታል የሚል ወቀሳ ሲቀርብባት ምን ሊሰማት ይችላል? ሩሲያዊያን በሁኔታው ደስተኞች አይደሉም ብላችሁ ካሰባችሁ ተሳስታችኋል ይላል ሮዘንበርግ።
የሩሲያ መንግሥት ጋዜጣ ግሪንላንድ ለመገንጠል በሚደረገው ጥረት ጉዳይ ትራምፕን አድንቆ፤ የአውሮፓ መሪዎችን ደግሞ አጣጥሎ የሚያቀርብ ፅሑፍ አትሟል።
"የአሜሪካው ፕሬዝደንት ሊፈፅሙት ላቀዱት ታሪካዊ ውሳኔ ደንቃራ የሆኑት ኮፐንሀገን እና ራሳቸውን የአሜሪካ አጋር ብለው የሚጠሩት ብሪታኒያ እና ፈረንሳይ ናቸው" ይላል ሮዚስካያ ጋዜጣ።
"ትራምፕ እያስተዋወቁ ያሉትን ታላቅነት አውሮፓ አትፈልገውም። ብራሰልስ በሚመጣው የአሜሪካ አጋማሽ ምርጫ ትራምፕ 'እንዲዘቅጡ' ይፈልጋሉ። በሕይወቱ ትልቁን ስኬት እውን ከማድረግ እንዲገታ ነው የሚሹት።"
ዘገባውን ሲያነቡ የሩሲያ መንግሥት ጋዜጣ ሳይሆን የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ የሆነ ግለሰብ የፃፈው ፅሑፍ ሊመስልዎት ይችላል።
"ትራምፕ አሜሪካ 250ኛ ዓመት የነፃነት በዓሏን በምታከብርበት ቀን (በአውሮፓውያኑ ሐምሌ 4/2026) ግሪንላንድን የሚገነጥሉ ከሆነ የአሜሪካን ታላቅነት እውን ያደረጉ ታላቁ መሪ ይሆናሉ" ይላል ጋዜጣው።
"ከግሪንላንድ ጋር አሜሪካ ከሩሲያ ቀጥላ ካናዳን በመብለጥ ሁለተኛዋ ትልቋ ሀገር ትሆናለች" እያለ ይቀጥላል።
"ምስጋና ለትራምፕ ይሁንና ግሪንላንድ የአሜሪካ አካል ስትሆን የአሜሪካ ሕዝብ መቸም ይህን ታላቅ ሥራ የሚረሳው አይሆንም።"
የሩሲያ ዘጋቢ ለአሜሪካ መንግሥት የሚያስተላልፈው አንድ መልዕክት አለው፡ 'በፍፁም እንዳታፈገፍግ' የሚል።
"ትራምፕ በግሪንላንድ ጉዳይ የሚያፈገፍጉ ከሆነ አደጋ ይኖረዋል። በአጋማሽ ምርጫ ሪፐብሊካን ፓርቲ ሊሸነፍ ይችላል። ይህ ደግሞ ካፒቶል ሂል በዲሞክራቶች ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ያደርጋል። ነገር ግን ግሪንላንድ ከምርጫው በፊት የምትገነጠል ከሆነ ፖለቲካዊ አካሄዱ ሊለወጥ ይችላል።"
የሩሲያ መንግሥት ጋዜጣ የአሜሪካው ፕሬዝደንት ግሪንላንድን ለመገንጠል የሚያደርጉትን ጥረት አጠናክረው እንዲቀጥሉ ይጎተጉታል።
ሞስኮ የትራምፕን ድርጊት የምታበረታታው ለምን ይሆን?
ምክንያቱ ሩሲያ አሁን ካለው ሁኔታ የምታገኘው ጥቅም ቀላል ስላልሆነ ነው።
ግሪንላንድ ለመያዝ ቆርጠው የተነሱ የሚመስሉት ትራምፕ ይህን ውሳኔያቸውን የሚቃወሙ የአውሮፓ ሀገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸው አሜሪካ ከአውሮፓ ጋር ያላት ግንኙነት ላይ ጥላሸት ያጠላ እና በኔቶ ሀገራት መካከል ውጥረት የፈጠረ ነው።
ይህን የምዕራቡን ዓለም ጥምረት የሚያዳክም አሊያም የሚከፋፍል የትኛውም ነገር ለሩሲያ ትልቅ ድል ነው።
"አውሮፓ ግራ ገብቷታል። እውነት ለመናገር ይህን መመልከት ትልቅ ደስታን ይፈጥራል" ሲል የሩሲያው ሞስኮቭስኪ ኮምሶሞሌትስ ጋዜጣ ፅፏል።
የክሬምሊን ደጋፊዎች ትራምፕ ግሪንላንድን ለመገንጠል የሚያደርጉትን ጥረት ሩሲያ ዩክሬን ላይ ካወጀችው ጦርነት ጋር እያመሳሰሉት ነው።
ክሬምሊን አሁንም ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ በዩክሬን ላይ ድል መቀዳጀት ነው።
ሞስኮው ይህን ለማሳካት ከትራምፕ ጋር መልካም ግንኙነቷን ማጠናከር እንዳለባት ታምናለች። ለዚህ ነው አውሮፓን ተችታ ትራምፕን የምታደናንቀው ይላል ሮዘንበርግ።