ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ፡ ግሪንላንድ ለመቆጣጠር ኃይል አንጠቀምም. . . አይሆንም ካላችሁን ግን አንረሳችሁም
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሰዊትዘርላንድ ዳቮስ ተገኝተው በዓለም የምጣኔ ሀብት ፎረም ላይ ንግግር አድርገዋል።
ትራምፕ በንግግራቸው መጀመሪያ ባለፉት 12 ወራት የሥልጣን ዘመናቸው በአሜሪካ በምጣኔ ሀብት እና በድንበር ጥበቃ ስኬት እንዳመጡ ተናግረዋል።
በግሪንላንድ ጉዳይ ከአውሮፓው መሪዎች ጋር እሰጣገባ ውስጥ ያሉት ትራምፕ የዴንማርክ ክፍል የሆነችው ግዙፏ ደሴትን በተለመከተ ረዘም ያለ ንግግር አድርገዋል።
"ግሪንላንድ መጠበቅ የምትችለው ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ናት" ብለዋል።
የአሜሪካ ፕሬዝደንቶች ግሪንላንድን ለመግዛት ለሁለት ክፍለ ዘመናት ሞክረዋል ያሉት ትራምፕ፤ ዴንማርክ በደሴቷ ላይ እያፈሰሰች ያለችው መዋዕለ ንዋይ በጣም አነስተኛ ነው ሲሉ ተደምጠዋል።
"አሜሪካ ብቻ ናት ይህን ግዙፍ መሬት መጠበቅ፣ ይህን ግዙፍ የበረዶ ምድር ማልማት እና ማሻሻል የምትችለው። ለዚህ ነው ግሪንላንድን ለመቆጣጠር አፋጣኝ ድርድር የምንሻው" ብለዋል።
በተደጋጋሚ ግሪንላንድን መቆጣጠር ለአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ወሳኝ ነው የሚሉት ትራምፕ "ግሪንላንድ ውስጥ ብርቅዬ የሚባሉ ማዕድናት አሉ የሚባለው" ሐሰት ነው የሚል ንግግር አሰምተዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ረዘም ባለ ንግግራቸው የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን አሊያም ኔቶን ተችተዋል።
በርካታ ሐሳቦችን በዳሰሰው ንግግራቸው ኔቶ የአሜሪካን እርዳታ ቢፈልግ "መቶ በመቶ እንደርስላቸዋለን፤ እነሱ ግን ለእኛ መድረሳቸውን እጠራጠራለሁ" ብለዋል።
ኔቶ በዩክሬን ያለውን ጦርነት ማስቆም እንዳለበት ያሳሰቡት ትራምፕ፤ ፑቲን እና ዜሌንስኪ ከስምምነት መድረስ እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል።
ይህን ለማድረግ አውሮፓ እና ኔቶን ለማገዝ ቁርጠኛ እንደሆኑ አሳውቀው በምትኩ የሚፈልጉት "የበረዶ መሬት" ነው በማለት የግሪንላንድ ጉዳይ ላይ አፅንዖት ሰጥተዋል።
"ምናልባት ከባድ ኃይል ካልተጠቅምኩ የምፈልገውን አላገኝም። ኃይልን ከተጠቀምን የሚያቆመን የለም፤ ነገር ግን አናደርገውም።"
በተደጋጋሚ ኃይል አንጠቀምም ያሉት ትራምፕ አሜሪካ የምትፈልገው "ግሪንላንድ የሚባል ቦታን" ነው ብለዋል።
ትራምፕ አሜሪካ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት "ግሪንላንድ የአሜሪካ ነበረች፤ ነገር ግን መልሰን ለዴንማርክ ሰጠናት" ብለው ሀገራቸው "መልሳ መስጠት አልነበረባትም" ሲሉ ዴንማርክ "ምስጋና ቢስ" እንደሆነች ተናግረዋል።
በዳቮስ ለተሰበሰቡት የዓለም መሪዎች ግሪንላንድ ምርጫ እንዳላት የተናገሩት ትራምፕ "እሺ ካላችሁን በጣም እናመሰግናለን፤ አይሆንም ካላችሁን ግን አንረሳችሁም" የሚል ማስጠንቀቂያ መሰል መልዕክት አስተላልፈዋል።
ግሪንላንድ በሰሜን አሜሪካ እና አርክቲክ መካከል የምትገኝ ቦታ ስትሆን፤ የሚሳዔል ጥቃት ሲመጣ ቀድሞ ለማስጠንቀቅ እና በአካባቢው የሚንቀሳቀሱትን መርከቦችን ለመቆጣጠር ስትራቴጂካዊ ቦታ እንደሆነች ይታመናል።
ዴንማርክ እና አሁን በግሪንላንድ 100 ያህል ወታደሮች ያሏት አሜሪካ ባላቸው ስምምነት መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ በደሴቷ የትኛውንም ዓይነት ቁጥር ያለው ወታደር ማስፈር ትችላለች።
ከተመደበላቸው ጊዜ 20 ደቂቃ አሳልፈው ለአንድ ሰዓት ያክል ንግግር ያደረጉት ትራምፕ ኔቶ ላይ ያሰሙት ተቃውሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን ተንታኞች ይናገራሉ።
አሜሪካ ላይ ከደረሰው የመስከረም 11 ጥቃት በኋላ ዴንማርክን ጨምሮ በርካታ የኔቶ አባል ሀገራት ወደ አፍጋኒስታን ወታደሮቻቸውን የላኩ ሲሆን፣ በጠቅላላ ከኔቶ ሀገራት 44 ወታደሮች እንደሞቱ ይታወሳል።
የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ እና የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮንን የሚተች ዓረፍተ ነገር በንግግራቸው ጣል ያደረጉት ትራምፕ በዳቮስ ከምዕራባዊያን መሪዎች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።