የአውሮፓ ኅብረት ከአሜሪካ ጋር ለነበረው የንግድ ስምምነት የሰጠውን ፈቃድ ሰረዘ

የአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ባለፈው ዓመት ነሐሴ ከአሜሪካ ጋር ተደርሶ ለነበረው የንግድ ስምምነት የሰጠውን ፈቃድ ሰረዘ።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግሪንላንድን ለመጠቅለል መወሰናቸውን በመቃወም ስምምነቱ እንዲሰረዝ መወሰኑ የዓለም የምጣኔ ሃብት ፎረም ላይ ተገልጿል።

የትራምፕ ውሳኔ የፋይናንስ ገበያ ቀውስ ከማስከተሉ ባሻገር በአውሮፓ እና አሜሪካ መካከል ያለውን የንግድ ውጥረት አባብሷል።

ትራምፕ በበኩላቸው በግሪንላንድ ጉዳይ ስምምነት በሚደረስበት ጉዳይ ላይ ከኔቶ አባላት ጋር መነጋገራቸውን እና የአውሮፓ አገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ ማንሳታቸውን ተናግረዋል።

ነሐሴ ላይ አሜሪካ እና የአውሮፓ አገራት የደረሱበት ስምምነት ትራምፕ ጥለውት የነበረውን ታሪፍ ከ30% ወደ 15% ዝቅ ያደረገ ነው።

አውሮፓ ታሪፉ ከተቀነሰ በኋላ በምላሹ አሜሪካ ውስጥ ኢንቨስት ለማድረግ እና የአሜሪካ የውጭ ንግድ እንዲጨምር ለማገዝ ተስማምታለች።

ስምምነቱ እንዲተገበር ከአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ ፈቃድ ሊሰጠው ይገባ ነበር።

ትራምፕ አዲስ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸውን ተከትሎ ግን ምክር ቤቱ "አማራጭ ስለሌለን የስምምነቱን ፈቃድ ሰርዘናል" ብሏል።

የንግድ ስምምነቱ ትግበራ "አሜሪካ ወደ ትብብር መንገድ እስከምትመጣ ድረስ" ተፈጻሚ እንደማይሆን አስታውቋል።

ባለፈው የአውሮፓውያኑ ዓመት ትራምፕ ጥለውት ለነበረው ታሪፍ ምላሽ የአውሮፓ ኅብረት 109 ቢሊዮን ዶላር በሚያወጡ የአሜሪካ ሸቀጦች ላይ ታሪፍ ለመጣል ዝተው ነበር። የንግድ ስምምነቱ የተሰጠው ፈቃድ መሰረዙን ተከትሎ ይህ የአውሮፓ ታሪፍ ተግባራዊ ሊደረግ ይችላል።

ትራምፕ በአውሮፓ ኅብረት አባል አገራት ላይ ታሪፍ ለመጣል መዛታቸውን በመጥቀስ "ማስፈራራቱ እስካልቆመ ድረስ አቋማችንን የምንለውጥበት ዕድል የለም" ብለዋል።

ትራምፕ በማኅበራዊ ሚድያ ገጻቸው ከሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) ጋር "በጣም ገንቢ" ያሉትን ውይይት ማድረጋቸውን ቢያስታውቁም ዝርዝር መረጃ አልሰጡም።

ስለ ግሪንላንድ ስምምነት በሚደረስበት ጉዳይ ላይ ከኔቶ አባላት ጋር ማውራታቸውን እና የአውሮፓ አገራት ላይ የጣሉትን ታሪፍ ማንሳታቸውን ቢገልጹም፤ ስምምነቱ ግሪንላንድን የአሜሪካ ንብረት በማድረግ ጉዳይ ላይ ምን እንደሚል የሚታወቅ ነገር የለም።

ትራምፕ በትሩዝ ሶሻል ገጻቸው "በግሪንላንድ እና በአርክቲክ ቀጣና ጉዳይ ወደፊት ከስምምነት የምንደርስበትን ማዕቀፍ አዘጋጅተናል" ብለዋል።

የቢቢሲ የአውሮፓ ኅብረት ምንጭ ትራምፕ ታሪፍ ላለመጣል መወሰናቸውን በተመለከተ ተጠይቀው እምብዛም ለውጥ የማያመጣ መሆኑን ጠቁመዋል።

በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ሲቢኤስ ከምንጮቹ ለማወቅ እንደቻለው ከሆነ አሜሪካ የዴንማርክ ክፍል የሆነችውን ራስ ገዝ ደሴት ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠሯ ጉዳይ ከስምምነት አልተደረሰም።

ትራምፕ በዓለም ምጣኔ ሃብት ፎረም ላይ ባሰሙት ንግግር ግሪንላንድን "መቆጣጠር" አማራጭ የሌለው ነገር መሆኑን ጠቁመው "ወታደራዊ ኃይል" እንደማይጠቀሙ ቃል ገብተዋል።

"ኃይል መጠቀም አያስፈልገኝም። ኃይል መጠቀም አልፈልግም። ኃይል አልጠቀምም" ብለዋል።