ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ በግልባጭ እንድታውቀው የተደረገው የትራምፕ የሕዳሴ ግድብ ድርድር ጥሪ ደብዳቤ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይ በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል ስምምነት እንዲደረስ መሞከራቸው ይታወሳል። ወደ ሥልጣን ዳግም ከተመለሱ በኋላም በተለያዩ ጊዜያት ስለግድቡ ከኢትዮጵያ ፍላጎት ተቃራኒ የሆኑ ግብፅን የሚደግፉ ንግግሮች ሲያደርጉ ተሰምተዋል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ጥር 8/2018 ዓ.ም. ደግሞ ፕሬዚዳንቱ በቀጥታ ለግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል ሲሲ በጻፉት ደብዳቤ "ባለን የግል ወዳጅነት መንፈስ እና አሜሪካ ለግብፅ ሕዝብ ሰላም እና ደኅንነት ባላት ቁርጠኝነት" የሕዳሴ ግድብን የተመለከተ ድርድርን ለመጀመር እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ "በግብፅ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለውን 'የአባይን ውሃ መጋራት' ጥያቄ ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ በኃላፊነት መንፈስ ለመፍታት ዝግጁ ነኝ" ሲሉ በገለጹበት ደብዳቤ ላይ ገለልተኝነትን ጨምሮ የተለያዩ ጥያቄዎች እየተነሱበት ይገኛሉ።
ደብዳቤውን ተከትሎ የግብፅ ፕሬዝዳንት እና በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የሚገኙት የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ አብደል ፋታህ አል ቡርሐን ፕሬዝዳንት ትራምፕ ያቀረቡትን ጥሪ እንደሚቀበሉት ወዲያውኑ ምላሽ ሲሰጡ ኢትዮጵያ ግን እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።
በደብዳቤው ላይ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ለበርካታ ዓመታት ባለመግባባት ውስጥ የቆዩትን አገራት ጉዳይ ለመፍታት ፍላጎታቸውን በመግለጽ "በቀጠናው የትኛውም አገር የአባይን ውሃ በተናጠል መቆጣጠር እና በሂደቱ ጎረቤቶቹን መጉዳት የለበትም" ሲሉ አስፍረዋል።
ፈቅ አሕመድ በአባይ ወንዝ እና በሕዳሴ ግድብ ድርድር ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት በውሃ ሀብት ልማት እና በድበንር ተሻጋሪ ወንዞች እና በሃይድሮ ዲፕሎማሲ አማካሪ ናቸው። ስለደብዳቤው እና በውስጡ ስለያዛቸው ጉዳዮች ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ኢትዮጵያ ምን ማድረግ አለባት?
አቶ ፈቅ የማደራደር ሀሳባቸውን በደብዳቤ የገለጹት ትራምፕ የመረጧቸው ቃላት እና አገላለጾች በከፍተኛ ደረጃ ለግብፅ ያደሉ ናቸው በማለት የደብዳቤው እና የደርድሩ ማጠንጠኛ የግብፅን ፍላጎት ለማሳካት የታለመ ይመስላል ብለዋል።
ለዚህም ከዚህ ቀደም ብዙ ያከራከረው እና ከስምምነት እንዳይደረስ ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ የሆነው ኢትዮጵያ ከግድቡ ኤሌክትሪክ ማመንጭት እንጂ በውሃው የመጠቀም መብቷን የማያውቅ ነው ያሉት አቶ ፈቅ፤ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት የሚያመለክት እንዳልሆነ አመልክተዋል።
"ሱዳን እና ግብፅ የአባይ ውሃ በጣሙን ስለሚያስፈልጋቸው፤ በተለይ ድርቅ በሚሆንበት ጊዜ ኢትዮጵያ ውሃውን መልቀቅ እንዳለባት የሚያመለክት መልዕክት በደብዳቤው ውስጥ አለ።"
በትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በአሸማጋይነት ተከታታይ ድርድሮች መደረጋቸው ይታወሳል። ነገር ግን ከስምምነት ተደርሶ ይፈረማል በተባለበት በመጨረሻው ሰዓት ኢትዮጵያ አልፈርምም በማለቷ ጉዳዩ በእንጥልጥል ቀርቷል።
ኢትዮጵያ ከስድስት ዓመት በፊት የቀረበውን ስምምነት ሳትቀበለው የቀረችው "ወደፊት በአባይ ውሃ የመጠቀም መብቷን ስለሚነፍግ ነው" ሲሉ አቶ ፈቅ ያስታውሳሉ።
አሁንም ወደ ድርድር ከተገባ ግብፅ እና ሱዳን በተደጋጋሚ ሲጠይቁት የነበረው አስገዳጅ ስምምነት እንዲፈረም አሁንም መጠየቃቸው እንደማይቀር ያምናሉ። ዶናልድ ትራምፕም ቢሆኑ ያ የስምምነት ሰነድ አሁንም ቀርቦ እንዲፈረም መጠየቃቸው አይቀርም።
ከ2019 አስከ 2020 ድረስ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን አሜሪካ እና ዓለም ባንክ መጀመሪያ በታዛቢነት በኋላ ደግሞ በአደራዳሪነት ገብተው ያረቀቁት የስምምነት ሰነድ አሁኑም ሊቀርብ ይችላል።
ነገር ግን በዚያ ሰነድ ውስጥ ኢትዮጵያ ውድቅ ያደረገችው የውሃ አሞላል እና ዓመታዊ የውሃ አለቃቀቅን በተመለከተው ክፍል በውስጡ "በድብቅ የተሰገሰጉ፤ ለግብፅ እና ለሱዳን የውሃ ድርሻ ኢትዮጵያ እውቅና እንድትሰጥ የሚያደርጉ ሃሳቦችን የያዘ" መሆኑን አቶ ፈቅ ይተቅሳሉ።
አጣብቂኝ አማራጮች
አሜሪካ እና የዓለም ባንክ ሲያደርጉት በነበረው ጥረት የቀረበው የስምምነት ሰነድ ኢትዮጵያ ጥቅሜን የሚያስጠበቅ አይደለም ብላ ወጥታ ትራምፕም በምርጫ ተሸንፈው ከዋይት ሐውስ ከተሰናበቱ በኋላ በአፍሪካ ኅብረት እና በዩናይትድ አረብ ኤምሬትስ አማካይነት ሌላ ዙር ሙከራ ቢደረግም ለፍሬ ሳይበቃ ቀርቷል።
አሁን ደግሞ ከአራት ዓመት በኋላ ትራምፕ ወደ ሥልጣን በተመለሱ በዓመታቸው ግብፅ እና ሱዳን ፍላጎታቸውን ለማሳካት ከዓመታት በፊት በእንጥልጥል የቀረው ስምምነት በአሜሪካ በኩል እንዲፈረም ጥረት እያደረጉ ነው የሚል እምነት አቶ ፈቅ አላቸው።
አሁን ግን ከትራምፕ በኩል የሚቀርበው አማራጭ ፈታኝ ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ። ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ "ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋታል" በማለት ያሳስባሉ።
"እንዲህ ያለውን ስምምነት መፈረም ብሔራዊ ጥቅምን የሚነካ ነው። አልደራደርም ማለት ደግሞ ከአሜሪካ በኩል ከፍተኛ ጫናን ሊያስከትል ይችላል።
"ትራምፕ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጠው ይህንን አድርጉ ወይም ተቀበሉ በማለት ያ ካልሆነ ሌሎች እርምጃዎችን እና ጫናዎችን እንደሚወስዱ ሊገልጹ ይችላል።"
ይህ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ ችግር የሚፈጥር በመሆኑ አቶ ፈቅ የሚመክሩት "ኢትዮጵያ ነገሮችን በጥንቃቄ በመያዝ ጥበብ እና ብልጠት በተሞላበት ሁኔታ ምላሽ መስጠት" እንዳለባት ነው።
"በሁለቱም በኩል ኢትዮጵያ አጣብቂኝ ውስጥ ነው ያለችው። ምክንያቱም ስምምነቱን መቀበል ያራሱ ችግር አለው፤ አልደራደርም ማለትም የራሱ ችግር አለው" በማለት ትራምፕ ባሉት መሠረት ድርድሩ የሚካሄድ ከሆነ ኢትዮጵያ በአጣብቂኝ አማራጮች ውስጥ ልትሆን እንደምትችል አመልክተዋል።
በድርድሩ ኢትዮጵያ ፍላጎቷን ማሳካት ትችላለች?
ትራምፕ ከመነሻው ለግብፅ ፍላጎት ያደላ ደብዳቤ መጻፋቸው እንዲሁም ከዓመታት በፊት የመሩት ድርድርም እንዲሁ በኢትዮጵያ ተቀባይነት አለማግኘቱን በመጥቀስ አሁንም ምን ዓይነት ሀሳብ እንደሚቀርብ ይታወቃል ይላሉ አቶ ፈቅ።
"የትራምፕ ሁኔታ የታወቀ ነው፤ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጥ ይህንን ተቀበሉ ካልሆነ ይህንን አደርጋለሁ ነው የሚሉት። ስለዚህ መደረግ ያለበት ትራምፕን አስቆጥቶ ወደ ፍጥጫ ሳይገባ የድርድሩን አቅጣጫ ማስቀየር ቢቻል የተመረጠ ነው" ሲሉ ይመክራሉ።
አቶ ፈቅ ይህንን በምሳሌ ሲያስረዱ ትራምፕ በደብዳቤያቸው ላይ የውሃ ድርሻ የሚል ነገር ስለጠቀሱ የውሃ ክፍፍል ጉዳይን ያነሳል "ስለዚህ ክፍፍሉ በተፋሰሱ 11 አገራት መካከል እንዲካሄድ ግፊት በማድረግ" ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሚጠቅማት መንገድ ልትመራው ትችላለች።
ሌላው ያነሱት ነገር የኤሌክትሪክ ኃይል ንግድ አቅርቦትን ነው። ለዚህም በአውሮፓውያኑ 2015 በኢትዮጵያ፣ በሱዳን እና በግብፅ መሪዎች መካከል በተፈረመው የመርሆች መግለጫ ስምምነት ላይ ግብፅ እና ሱዳን ከግድቡ የሚመነጨውን ኃይል መግዛት ቅድሚያ ይሰጣቸዋል ይላል።
ስለዚህም ኢትዮጵያ ይህንን መሠረት አድርጋ በኃይል ንግድ ላይ ከአገራቱ ጋር በመደራደር ከትራምፕ በኩል የመጣውን የድርድር ሀሳብ ኢትዮጵያን በሚጠቅም አቅጣጫ ለመምራት መሞከር አስፈላጊ መሆኑን ይመክራሉ።
ትራምፕ ለምን የሕዳሴ ግድብ ነገር አስጨነቃቸው?
ትራምፕ ከግብፅ በተለይም ከፕሬዝዳንት አል ሲሲ ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቻው የሚሉት አቶ ፈቅ፣ በቅርቡም ሲሲ ወደ ዋሺንግተን አቅንተው እንደነበር ጠቅሰዋል።
በአውሮወያኑ 2019 ትራምፕ ወደ ሕዳሴው ግድብ ሽምግልና የገቡት በግብፅ ጥያቄ መሠረት ነው። አሁንም አል ሲሲ ከጋዛው ጦርነት ማብቃት በኋላ ግፊት በማድረጋቸው ትራምፕ ጉዳዩን በድጋሚ አንስተው የአሸማጋይነት ሚናቸውን ለመያዝ ተነስተዋል።
ምንም እንኳን በኢትዮጵያ እና በግብፅ መካከል የተካሄደም ሆነ ሊካሄድ የነበረ ጦርነት ባይኖርም ትራምፕ ደጋግመው በአገራቱ መካከል ጦርነት ማስቀረታቸውን ሲናገሩ ተሰምተዋል።
በዚህም የዘወትር ፍላጎታቸው የነበረውን የኖቤል ሽልማት ለማግኘት ከሚጠቅሷቸው ስምንት ግጭቶች መካከል የሁለቱ አገራትን ስም ሲጠቅሱ ተሰምተዋል።
አቶ ፈቅ እንደሚሉትም ትራምፕ በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ ስምምነት ለማምጣት ድጋሚ ተነሳሽነቱን ማሳየታቸው ለቀጣይ የኖቤል ሽልማት አሸናፊነት ህልማቸው ማሳኪያ አንድ አካል ሊሆን ይችላል።
ጉዳዩ ለኢትዮጵያ በግልባጭ መገለጹ ምን መልዕክት አለው?
የትራምፕ ደብዳቤ የተጻፈበት ሁኔታ የተነሳሽነታቸውን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ከከተቱ የደብዳቤው ክፍሎች መካከል አንዱ ነው።
በሚካሄደው ድርድር ዋነኛዋ አካል የሆነችው ኢትዮጵያ በደብዳቤው ላይ በተገቢው ሁኔታ አልተጠቀሰችም። ደብዳቤው በቀጥታ ለግብፁ ፕሬዝዳንት የተጻፈ ሲሆን ኢትዮጵያ በግልባጭ ነው እንዲደርሳት የተጠቀሰችው።
ይህም መልዕክት ያዘለ ነው የሚል ዕምነት ያላቸው አቶ ፈቅ "በትክክለኛው የዲፕሎማሲ አካሄድ ደብዳቤው መጻፍ የነበረበት ለኢትዮጵያ፣ ለግብፅ እና ለሱዳን ካስፈለገም ለሳዑዲ እና ለኤምሬትስ ግልባጭ ማድረግ ይገባ ነበር" ይላሉ።
ነገር ግን ደብዳቤው በቀጥታ ለግብፅ ተጽፎ ኢትዮጵያ እንደዋነኛ ባለጉዳይ በቀጥታ ሳይሆን የተጠቀሰችው ከማይመለከታቸው አገራት ጋር "እንድታውቀው" በሚመስል ሁኔታ በግልባጭ ነው እንዲደርሳት የተደረገው።
ስለዚህም አቶ ፈቅ ኢትዮጵያ በጉዳዩ ላይ እንድትሳተፍ በቀጥታ ባለመጠየቋ "አልተጠየቅኩም" በማለት ምንም ዓይነት ምላሽ ከመስጠት ልትቆጠብ ትችላለች የሚል እምነት አላቸው።
ግብፅ እና ሱዳን ድጋቸፋውን በፍጥነት ሲገልጹ የኢትዮጵያ መንግሥትም እስካሁን ዝምታን እንደመረጠ ነው።
ይህም ሆነው በቀጥታ ስላልተጠየቀ ወይም ጉዳዩ ውስብስብ እና የተለያዩ ገጽታዎች ሊኖሩት ስለሚችሉ ምን ዓይነት አቋም መያዝ እንዳለበት እየመከረ ሊሆን ይችላል የሚለውን ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
ከኢትዮጵያ በኩል በግልባጭ የድርድር ሀሳቡን እንዲያውቁት የተደረጉት ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በምን ምክንያት እንደተካተቱ የታወቀ ነገር የለም።
አቶ ፈቅ በበኩላቸው ስለ ውይይቱ ማወቅም ሆነ ተሳታፊ የሚሆኑ አገራትን መምረጥ ያለባቸው ተደራዳሪዎቹ አገራት አንጂ ትራምፕ መሆን አልነበረባቸውም ይላሉ።