ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የክሪፕቶ ወንጀለኞች እንዴት 700 ሚሊዮን ዶላር ሊዘርፉ ቻሉ?
ክሪፕቶከረንሲዎ ሲሰረቅ በጣም ከማሳዘንም በላይ ንዴት ሊፈጥር ይችላል። እያንዳንዱ የገንዘብ ልውውጥ ብሎክቼይን ተብሎ በሚታወቀው መድረክ ተመዝግቦ ይቀመጣል። አንድ ሰው ክሪፕቶዎን ወስዶ ወደ ራሱ ካዝና ቢያስተላልፈው እንኳ ማወቅ ይችላሉ ማለት ነው።
"ለሁሉም ክፍት ብሎክቼይን ላይ ገንዘብህን ታየዋለህ ነገር ግን ምንም ማድረግ አትችልም" ትላለች በዘራፊዎች 315 ሺህ ዶላር የተበላችው ሄለን።
ዩናይትድ ኪንግደም የሚኖሩት ሄለን እና ባሏ ሪቻርድ (ስማቸው የተቀየረ) ለሰባት ዓመታት ያህል ካርዳኖ የተባለ ክሪፕቶ እየገዙ ሲያጠራቅሙ ቆይተዋል።
በድንገት ዋጋው ሊመነድ የሚችል ዲጂታል መገበያያ ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ያስደስታቸዋል። አደጋ እንዳለው ቢያውቁም የደጂታል ቁፋቸውን በጥንቃቄ አስቀምጠዋል።
ነገር ግን 'ሀከሮች' (ዘራፊዎች) ወደ ክላውድ ገፃቸው ገብተው ቁልፉን ሰርስረው በማውጣት ሊዘርፏቸው ችለዋል።
በአውሮፓውያኑ የካቲት 2024 ነው ዘራፊዎቹ በአስደናቂ ፍጥነት ነበር ድርጊቱን የፈጸሙት። መጀመሪያ በትንሽ መጠን ነበር የጀመሩት።
ጥንዶቹ ገንዘባቸው ቀስ በቀስ እየተሸረሸረ ሲዘዋወር እየተመለከቱ ምንም ማድረግ አልቻሉም።
የክሪፕቶከረንሲ እያንዳንዱ የገንዘብ ዝውውር ለሕዝብ ክፍት ቢሆንም ተጠቃሚዎችን አፈላልጎ ማግኘት እጅግ አዳጋች ሊሆን ይችላል።
ሄለን እና ሪቻርድ ሀብታም አይደሉም። ካርዳኖ ላይ ያፈሰሱት መዋዕለ ንዋይ አንድ ቀን ሊጠቅማቸው እንደሚችል እምነት ነበራቸው።
"እነዚህን ሳንቲሞች ለረዥም ጊዜ ስንገዛ ቆይተናል። ከዚህም ያገኘነው ገንዘብ እዚህ ላይ ነበር ምናውለው" ይላል ሪቻርድ።
"ከቤተሰቦቼ ሞት ቀጥሎ ይህ ዘረፋ በሕይወቴ በጣም አስከፊው ክስተት ነው።"
ሄለን ገንዘቡን ለማስመለስ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም። ከፖሊስ እና ካርዳኖን ከፈጠሩት ሰዎች መረጃዎችን ስትሰበስብ ቆይታለች። ምንም እንኳ የዘራፊዎቹን የካዝና መለያ ብታገኝም ማንነታቸውን ማጣራት ግን አልቻለችም።
ጥንዶቹ አሁን ዕቅዳቸው በቂ ገንዘብ አሰባስበው የግል መርማሪ በመቅጠር የሀከሮቹን ማንነት ማጣራት ነው።
"ደካማ የመሆን ስሜት ላይ ነው የሚጥለው" ትላለች። "ነገር ግን ሙከራዬን እቀጥላለሁ።"
የክሪፕቶ ወንጀል መስፋፋት
ፋይናንሻል ኮንዳክት አውቶሪቲ እንደሚለው ከብሪታኒያ ሕዝብ 12 በመቶ ያህሉ ክሪፕቶ አለው። ይህም ቁጥር 7 ሚሊዮን ሰዎችን ይይዛል ማለት ነው።
በዓለም አቀፍ ደረጃ 560 ሚሊዮን ሰዎች ክሪፕቶ እንዳላቸው ይገመታል። የተጠቃሚዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ የወንጀለኞችም ቁጥር ጨምሯል።
በርካቶች የክረፕቶ ባለቤት የሆኑት ሰዎች በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ነው። ወንጀሉም የተስፋፋው በዚሁ ጊዜ ነው።
በተጠናቀቀው የአውሮፓውያን ዓመት ከ3.4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የክሪፕቶ ዝርፊያ ተፈፅሟል ይላል ቼይንአናሊሲስ የተሰኘው የብሎክቼይን ተንታኝ ድርጅት።
አብዛኛው ገንዘብ የሚሰረቀው የክሪፕቶ ኩባንያዎች ላይ በሚፈፀም ሰፋ ያለ የሳይበር ወንጀል አማካይነት ነው። ለምሳሌ ሰሜን ኮሪያዊያን ሀከሮች ባይቢት ከተባለው ኩባንያ 1.5 ቢሊዮን ዶላር ዘርፈዋል።
እንዲህ ያሉ ዘረፋዎች ሲፈፀሙ ኪሳራውን የሚሸፍኑት የክሪፕቶ ኩባንያዎች እንጂ ተጠቃሚዎች አይደሉም። ነገር ግን በ2025 በርካታ ግለሰቦች ላይ የክሪፕቶ ዝርፊያ የተፈፀመበት ዓመት ሆኗል።
ቼይንአናሊሲስ እንደሚለው በ2022 ግለሰቦች ላይ የተፈፀመው ጥቃት 40 ሺህ ነበር። ይህ ቁጥር በ2025 ወደ 80 ሺህ ከፍ ብሏል።
20 በመቶ ወይም 713 ሚሊዮን ዶላር የሚሆነው ዝርፊያ የተፈፀመው ሀክ በማድረግ፣ በማጭበርበር አሊያም ግለሰቦችን በማስገደድ ነው።
ኩባንያው አክሎ የዝርፊያ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ሁሉም ሪፖርት ሊያደርጉ ስለማይችሉ ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ይጠቁማል።
ባይናንስ በዓለማችን ግዙፉ የክሪፕቶ መገበያያ መድረክ ነው። በዩናይትድ ኪንግደም ብቻ 1.4 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ይገመታል። ቢሆንም ክሪፕቶ በዩኬ አሁንም ቁጥጥር የማይደረግበት እና ከፍተኛ ስጋት ያለው መገበያያ ነው።
ባይናንስ ከ2023 ጀምሮ ዩኬ ውስጥ አዲስ ደንበኞችን መመዝገብ አቁሟል። ይህ የሆነው በሀገሪቱ ፋይናንስ ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤት ፈቃድ ስላልተሰጠው ነው።
የክሪፕቶ ዋጋ ከፍ እያለ ሲመጣ ወደ ዲጂታሉ መገበያያ ዓለም የሚመጡ ሰዎች ቁጥርም ይጨምራል። በተለይ በርካታ ክሪፕቶከረንሲ ያላቸው እና ሀብታቸውን ለሕዝብ ይፋ ያደረጉ ሰዎች ዒላማ የመደረጋቸው ነገር ከፍ ያለ ነው።
ዘራፊዎቹ የት ነው ያሉት?
ዘራፊዎቹ በየትኛው የዓለም ክፍል ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ።
ባለፈው ጥቅምት ኤሊፕቲክ የተባለው የክሪፕቶ ተንታኝ ድርጅት የሰሜን ኮሪያ ሀከሮች በመንግሥት ተደግፈው ጠቀም ያለ ገንዘብ ያላቸውን ተጠቃሚዎች ዒላማ እያደረጉ ነው ብሏል። ነገር ግን በሌሎችም ሀገራት በርካታ ወጣት ሀከሮች ይገኛሉ።
ባለፈው ታኅሣሥ በአሜሪካ የ22 ዓመቱ ኢቫን ታንጅማን 260 ሚሊዮን ዶላር ያጭበረበረው ሶሻል ኢንጂነሪንግ ኢንተርፕራይዝ የተባለው ቡድን አባል መሆኑን አምኗል።
ዐቃቤ ሕግ ይህ ቡድን ሀክ የተደረገ የመረጇ ቋት በመጠቀም በርካታ ክሪፕቶ ያላቸውን ሰዎች እየመረጠ ሲያጭበርበር ነበር ይላል።
አብዛኞቹ የቡድኑ አባላት ወጣት ወንዶች ሲሆኑ የሚገኙት ደግሞ በአሜሪካ ነው። ወጣቶቹ በዘረፉት ገንዘብ የግል አውሮፕላን፣ ውድ መኪኖች እና ቦርሳዎች ይገዛሉ። ወደ መሸታ ቤት በመሔድ ገንዘባቸውን ይረጫሉ።
ዐቃቤ ሕግ እንደሚለው ወንጀለኛው ቡድን አንዳንድ ጊዜ ቤት ሰብሮ በመግባት ክሪፕቶ ያለባቸውን የኮምፒውተር ሀርድዌሮች ይሰርቃል።
በክሪፕቶው ዓለም ክሪፕቶ አለባቸው የተባሉ የኮምፒውተር ቁሶችን መዝረፍ እና መስረቅ እየተለመደ መጥቷል።
ባለፈው ሚያዝያ በስፔን ጥንዶች በክሪፕቶ ዘራፊዎች ታግተው ተወስደው ሴቷ ስትለቀቅ ወንዱ ከቆይታ በኋላ አስከሬኑ ጫካ ውስጥ ተገኝቷል። በዚህ ወንጀል የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች ስፔን ውስጥ ሲያዙ ዴንማርክ ውስጥ ደግሞ አራት ሰዎች ክስ ቀርቦባቸዋል።
በፈረንሳይም በተመሳሳይ ዘራፊዎች እገታ ሊፈፅሙ ሲሞክሩ የሚያሳይ ቪድዮ ወጥቶ ነበር።
በ2025 መጀመሪያ በፈረንሳይ የክሪፕቶከረንሲ ደኅንነት ኩባንያ የሆነው ሌጀር ባለቤት ዴቪድ ባላንድ እና ሚስቱ ታግተው በፖሊስ ነፃ መውጣታቸው ይታወሳል። ዘራፊዎች ባላንድ መረጃ እንዲሰጣቸው ለማስገደድ ጣቱን ቆርጠውታል።
ባለፈው ወር ደግሞ የዩኬ ፖሊስ መኪና አስቁመው 1.5 ሚሊዮን ፓውንድ ክሪፕቶ አስገድደው አስተላልፈዋል ያላቸውን 6 ሰዎች በቁጥጥር ሥር አውሏል።