ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከሰሜን ኮሪያ ጋር ግንኙነት ያላቸው መዝባሪዎች የ1.7 ቢሊዮን ዶላር ክሪፕቶ መስረቃቸው ተነገረ
በሰሜን ኮሪያ የሚደገፉ ናቸው የተባሉ የበይነ መረብ ሰርሳሪዎች (ሀከርስ) ባለፈው የፈንጆች ዓመት 1.7 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ክሪፕቶ መዝረፋቸውን በዘርፉ ላይ ትንተና የሚሰጠው ቼይናሊስት የተባለው ተቋም ገለጸ።
ይህም በቀደመው ዓመት በሰሜን ኮሪያ ተሰርቋል ተብሎ ከሚታመነው 429 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የክሪፕቶከረንሲ በበርካታ እጥፍ የሚበልጥ ነው።
ይህ ዝርፊያም ባለፈው ዓመት በክሪፕቶከረንሲ ከተፈጸመው የ3.8 ቢሊዮን ዶላር ዝርፊያ ውስጥ 44 በመቶውን የሚሸፍን ሲሆን፣ “እስካሁን ካጋጠሙት ስርቆቶች ትልቁ ነው” ብሏል ተቋሙ።
ባለሙያዎች እንዳሉት ሰሜን ኮሪያ ከባድ ማዕቀብ ውስጥ በመሆኗ፣ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን ለመደጎም ፊቷን ወደ ክሪፕቶ ከረንሲ ስርቆት አዙራለች።
“ለምሳሌ ሰሜን ኮሪያ በ2020 (እአአ) ወደ ውጭ የላከችው አጠቃላይ ምርት 142 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው ነው። ስለዚህ የክሪፕቶከረምሲ ዝርፊያ በምጣኔ ሀብቷ ውስጥ ሰፊ ቦታን ይሸፍናል ቢባል ማጋነን አይሆንም” ሲል ጥናቱን ያካሄደው የቼይናሊስ ሪፖርት አመልክቷል።
ሰሜን ኮሪያ የኑክሌር ጦር መሳሪያ ግንባታዋን በኪም ጆንግ ኡን የሥልጣን ዘመን ከሌላው ጊዜ በበለጠ አስፋፍታዋለች።
ባለፈው ዓመት ስድስት የኑክሌር ሙከራዎችን ያደረገች ሲሆን በዚህ የፈረንጆች ዓመትም ሰባተኛውን ታደርጋለች ብለው ተንታኞች ይጠብቃሉ።
በተጨማሪም ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የተወንጫፊ እና ሌሎች አይነት ሚሳኤሎችን ሞክራለች።
ይህ ሁሉ የከፍተኛ ጦር መሳሪያዎች ግንባታ እና ሙከራ የሚደረገው በተጣለባት ተደራራቢ ማዕቀቦች የተነሳ ኢኮኖሚዋ በተዳከመበት ወቅት ነው።ስለዚህም የክሪፕቶ ዝርፊያው ያሉባትን ጉድለቶች ለመሸፈን በእጅጉ እንደሚጠቅማት ተንታኞች ይናገራሉ።
እነዚህ የበይነ መረብ ገንዘብ መዝባሪዎች ክሪፕቶውን ወደ መደበኛው የግብይት መስመር ለማስገባት ከተጠቃሚዎች የክሪፕቶከረንሲዎች ጋር በመቀላቀል የተሰረቁት መነሻቸው እንዳይታወቅ ያደርጋሉ።
በተጨማሪም ሰሜን ኮሪያ የተሰረቁ ክሪፕቶከረንሲዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የተለያዩ ዘዴዎችን እንደምትጠቀም፣ ከእነዚህ ውስጥም ቻይና ውስጥ የሚገኙ ደላሎችን ትጠቀማለች።
ባለፈው ወር የአሜሪካ የፌደራል የወንጀል መከላከል መሥሪያ ቤት(ኤፍቢአይ) እንዳረጋገጠው፣ ከሰሜን ኮሪያ ጋር ግንኙነት አለው የተባለው ላዛረስ ግሩፕ በብሎክ ቼይን ትስስር አማካይነት 100 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጣ የክሪፕቶ ዝርፊያ ፈጽሟል።
በአጠቃላይ ለስርቆት ከተዳረጉት ክሪፕቶዎች መካከል 82 በመቶውን የሚሸፍኑት ዲኢኤፍአይ የተባሉት ሲሆኑ፣ አጠቃቀማቸው ለስርቆት ተጋላጭ እንዳደረጋቸው ተገልጿል።