ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቬንዙዌላዋ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሜዳሊያቸውን ለትራምፕ በስጦታ ሰጡ
የቬንዙዌላ ተቃዋሚ መሪ ማሪያ ኮሪና ማቻዶ ሐሙስ ዕለት በዋይት ሃውስ በተካሄደ ስብሰባ ላይ የኖቤል የሰላም ሽልማት ሜዳሊያቸውን ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ መስጠታቸውን ተናገሩ።
"ዛሬ ለእኛ ቬንዙዌላውያን ታሪካዊ ቀን ይመስለኛል" ሲሉ ትራምፕን ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ካገኙ በኋላ ተናግረዋል። ይህ የሆነው የአሜሪካ ወታደሮች የቬንዙዌላ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ማዱሮን በካራካስ ከያዟቸው እና በአደንዛዥ ዕፅ ዝውውር ክስ ከተመሰረተባቸው ከሳምንታት በኋላ ነው።
ትራምፕ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ምስጋናቸውን ገልጸዋል፣ እርምጃው "የመከባበር አስደናቂ ምልክት" ነው ብለዋል።
ፓርቲያቸውን የ2024ቱን ምርጫ ማሸነፉን የገለጹትን ማቻዶን አዲሷ የቬንዙዌላ መሪ አድርገው የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ለመደገፍ ፈቃደኛ አልሆኑም።
ትራምፕ በቬንዙዌላ ከሚገኙት ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት እና የቀድሞው የማዱሮ ምክትል ዴልሲ ሮድሪጌዝ ጋር እየተነጋገሩ ነው።
ማቻዶን መግኘታቸውን ግን "ታላቅ ክብር" እንደሆነ በመግለጽ "ብዙ ነገሮችን ያሳለፈች ድንቅ ሴት" ሲሉ ጠርተዋታል።
ማቻዶ ከዋይት ሐውስ ከወጡ በኋላ በር ላይ ለተሰበሰቡት ደጋፊዎቻቸው "በፕሬዝዳንት ትራምፕ ላይ መተማመን እንችላለን" ብለዋል።
"ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት የኖቤል የሰላም ሽልማት ሜዳሊያዬን አበርክቻለሁ" ሲሉ ማቻዶ በኋላ ላይ ለጋዜጠኞች ተናግረው "ለነፃነታችን ላሳዩት ልዩ ቁርጠኝነት ዕውቅና" ነው በማለት አክለዋል።
የኖቤል የሰላም ሽልማት ለመሸለም ያላቸውን ፍላጎት ደጋግመው የሚናገሩት ትራምፕ፤ ሽልማቱ ለማቻዶ ሲሰጥ ቅር እንደተሰኙ ገልጸው ነበር።
ቢቢሲ በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት ለማግኘት ለዋይት ሐውስ ጥያቄ አቀርቦ ነበር።
ማቻዶ ባለፈው ሳምንት ሽልማቱን ከትራምፕ ጋር እንደሚጋሩ ቢገልጹም የኖቤል ኮሚቴው ግን ዕውቅናው ሊተላለፍ እንደማይችል ግልጽ አድርጓል።
ኮሚቴው ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ "የኖቤል ሽልማት አንዴ ከተገለጸ በኋላ ሊሻር፣ ሊጋራ ወይም ለሌሎች ሊተላለፍ አይችልም። ውሳኔው የመጨረሻ እና ለዘላለም የሚጸና ነው" ብሏል።
ለማቻዶ አስተያየት ምላሽ እንዲሰጥ የተጠየቀው ኮሚቴው ቢቢሲን ቀደም ሲል ወዳወጣው መግለጫ መርቶታል።
ሐሙስ ዕለት በዋይት ሐውስ ከተደረገው ስብሰባ በፊት የኖቤል የሰላም ማዕከል በኤክስ ላይ "ሜዳሊያ ለሌላ ሰው ሊተላለፍ ይችላል፣ ነገር ግን የኖቤል የሰላም ሽልማት ተሸላሚ ማዕረግ አይለወጥም" ሲል አስፍሯል።
ማቻዶ በአሜሪካ አብዮታዊ ጦርነት የተዋጉት ማርኪውስ ደ ላፋዬት የጆርጅ ዋሽንግተንን የሚመስል ሜዳሊያ ለዘመናዊቷ ቬንዙዌላ መስራች አባቶች አንዱ ለሆኑት ለሲሞን ቦሊቫር እንዴት እንደሰጡ ተናግረዋል።
ስጦታው በአገሯ እና በአሜሪካ መካከል "አምባገነንነትን ለመዋጋት በሚያደርጉት ትግል" መካከል ለነበረው "የወንድማማችነት ምልክት" ነበር ብለዋል ማቻዶ።
"እናም ከ200 ዓመታት ቦኋላ የቦሊቫር ህዝቦች ለዋሽንግተን የኖቤል የሰላም ሽልማት ሜዳሊያ እየሰጡ ነው። ይህም ለነፃነታችን ላሳዩት ልዩ ቁርጠኝነት እውቅና ለመስጠት" ሲሉ ተናግረዋል።
ማቻዶ በዋሽንግተን ባደረጉት ጉብኝት የአሜሪካን ሴናተሮችን ለማግኘት ኮንግረስን ጎብኝተዋል። በወቅቱ ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ደጋፊዎቻቸው "ማሪያ ፕሬዝዳንት" እያሉ በመጮህ እና የቬንዙዌላ ባንዲራ በማውለብለብ ድጋፍ ሲሰጧቸው ታይተዋል።
ማቻዶ ከትራምፕ ጋር በነበራቸው ቆይታ የሮድሪጌዝን ጊዜያዊ መንግስት መደገፍ ስህተት እንደሆነ እና የተቃዋሚ ጥምረታቸውን ይህንን ሽግግር ኃላፊነት መውሰድ እንዳለበት ለማሳመን እንደምትሞክሩ ይጠበቃል።
የዋይት ሀውስ የፕሬስ ኃላፊ ካሮሊን ሊቪት ስብሰባው እየተካሄደ ባለበት ወቅት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ማቻዶ "ለብዙ የቬንዙዌላ ህዝብ አስደናቂ እና ደፋር ድምጽ" እንደሆኑ እና ትራምፕ "ይህንን ስብሰባ በጉጉት እንደሚጠባበቁ እና በቬንዙዌላ ስላለው የአሁናዊ እውነታዎች ግልጽ እና አዎንታዊ ውይይት እንደሚጠብቁ" ተናግረዋል።
ትራምፕ ቀደም ሲል ማቻዶን "የነጻነት ታጋይ" ሲሉ ገልጸዋቸዋል። ነገር ግን ማዱሮ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ በቂ የሀገር ውስጥ ድጋፍ እንደሌላቸው በመግለጽ ቬንዙዌላን እንዲመሩ የመሾም ሃሳብን ውድቅ አድርገዋል።