ሰሜን ኮሪያ አሜሪካንን መምታት የሚችል አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተነገረ

ሰሜን ኮሪያ አህጉር የሚያቋርጥ አይሲቢኤም የተሰኘውን የሚሳኤል አይነት ወደ ባሕር በማስወንጨፍ ሙከራ ማድረጓን ጃፓን አስታወቀች።

የፒዮንግያንግ የሞከረችው ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል የአሜሪካ ግዛት ድረስ መጓዝ ይችላል።

የጃፓን የጠረፍ አካባቢዎች ጥበቃ ባለሥልጣን ሚሳኤሉ ከሆካይዶ ምዕራባዊ ክፍል በ210 ኪሎ ሜትር ርቀት ባሕር ላይ መውደቁን ይፋ አድርጓል።

የሰሜን ኮርያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ቾዬ ሶን ሁዊ አሜሪካ በአካባቢው ያላትን ወታደራዊ ኃይል ለማጠናከር ማሰቧን ከግምት ውስጥ በመክተት ''ጠንካራ'' ምላሽ እንደምትሰጥ ገልጸው ነበር።

በተመሳሳይ ቀን ፒዮንግያንግ አጭር ርቀት የሚወነጨፍ ሚሳኤል ሞክራም ነበር።

ሙከራው ባለፈው እሁድ የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን፣ የደቡብ ኮርያው መሪ ዩን ሱክ-ዮኤል እና የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዎ ኪሻ በካምቦዲያ በነበረ ጉባኤ ተጓዳኝ ተገናኝተው ከተካሄዱ በኋላ የተደረገ ነው።

ባይደን ስብሰባውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ሦስቱ አጋር አገራት "ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሰሜን ኮሪያ ተንኳሽ ባህሪይ ዙሪያ" ተመሳሳይ አቋም ላይ እንዳሉ ገልጸው ነበር።

ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ50 በላይ ሚሳይሎችን አስወንጭፋለች። አብዛኞቹ አጭር ርቀት የሚጓዙ ናቸው።

የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎቹ ሙከራ ግን አልፎ አልፎ የሚካሄድ እና የትኛውንም የአሜሪካ መሬት ለመምታት የሚያስችል ሆነው የተገነቡ ብሎም የኒውክሌር መሳሪያን መሸከም የሚችሉ ናቸው።

በዚህ ሳምንት የተሞከረው ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል በሰሜን ኮሪያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 4 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ከዋና ከተማዋ ፒዮንግያንግ መተኮሱን የሴኡል ወታደራዊ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።

የጃፓን የመከላከያ ሚኒስትር ሚሳኤሉ እስከ 15 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚጓዝ እና አሜሪካን ለመምታት የሚችል መሆኑንም ገልጸዋል።

''ለፒዮንግያንግ እንዲህ ያለ ባህርይን በፍጹም እንደማንታገስ አሳውቀናታል'' ሲሉ ሚኒስትሩ በታይላንድ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ሰሜን ኮርያ ባለፉት ጥቂት ወራት ያደረገቻቸው የሚሳኤል ሙከራዎች አሜሪካ በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ ለምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ ምላሽ የሰጠ ነው።

ፒዮንግያንግ ሁዋሶንግ-17 የተሰኘ አዲስ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል እየገነባች ሲሆን፣ እስከዛሬ ከተሞከሩ ረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤሎች ይልቅ የበለጠ መጠን ያለው ነው።

የዘርፉ ባለሞያዎች እንደሚሉት ከሆነ እስከሁን ድረስ ሁዋሶንግ-17ን ለማስወንጨፍ የተደረጉ ሙከራዎች ከሽፈዋል።

የደቡብ ኮርያ መከላከያ ይፋ ባደረገው መሰረት በያዝነው ወር መጀመሪያ የተሞከረ የረጅም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳኤል ከሽፏል።

በጥቅምት ወርም ሰሜን ኮርያ ከአምስት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በጃፓን ላይ ያለፈ የባልስቲክ ሚሳኤል ሙከራ አካሂዳለች።

ምንም እንኳን በርካታ ማዕቀቦች ቢጣሉባትም ፒዮንግያንግ እኤአ ከ2006 እስከ 2017 ድረስ ስድስት የኒውክሌር ሙከራዎችን ያካሄደች ሲሆን ለሰባተኛው እየተዘጋጀች መሆኑንም ታውቋል።