ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሰሜን ኮሪያ ‘ጠንካራ እርምጃ’ እወስዳለሁ ስትል አሜሪካ ላይ ዛተች
አሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የምታደርገውን የጋራ ወታደራዊ ልምምድ የማታቆም ከሆነ “ጠንከራ እርምጃ” እወስዳለሁ ስትል ሰሜን ኮሪያ አስጠነቀቀች።
ሰሜን ኮሪያ ኃያሏ አሜሪካንን ያስጠነቀቀችው ዋሽንግተን እና ሶል ከትናንት ሰኞ ጀምሮ ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቆይ ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ መጀመራቸውን ተከትሎ ነው።
ይህ የአየር ላይ የጋራ ወታደራዊ ልምምድ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ካደረጓቸው ግዙፍ የጦር ልምምዶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል።
ሁለቱ አገራት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያካሂዷቸውን ልምምዶች ያጠናከሩ ሲሆን፤ ለዚሁ ምላሽ እንዲሆን ሰሜን ኮሪያ በርካታ ሚሳኤሎችን ስታስወነጭፍ ነበር።
በአሁኑ ወቅት ሰሜን ኮሪያ ከእአአ 2017 ወዲህ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራ ታደርጋለች የሚሉ የደኅንነት መረጃዎች እየወጡ ይገኛሉ።
“አሜሪካ ጠብ አጫሪ በሆኑ ወታደራዊ እርምጃዎቿ የምትቀጥል ከሆነ፤ [ሰሜን ኮሪያ] ከዚያ በላይ ጠንካራ በሆኑ ርምጃዎች ምላሽ ለመስጥት አማራጮችን ታጤናለች” ብሏል የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት።
አሜሪካ ከደኅንነት ፍላጎቷ ተቃራኒ የሆኑ ነገሮች እንዳይከሰቱ የምትፈልግ ከሆነ፤ “ረብ የለሽ እና ውጤታማ ያልሆነው የጦር ልምምድ ማድረጓን በአንድ ጊዜ ማቆም አለባት። ካልሆነ ግን ተከትሎ ለሚመጣው መዘዝ ሙሉ ኃላፊነት መውሰድ አለባት” ብሏል የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ።
አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ፤ “ቪጂላንት ስቶርም” ሲሉ በሰየሙት የአየር ላይ ውጊያ ልምምድ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሁለቱ አገራት አውሮፕላኖች በቀን ለ24 ሰዓታት ልምምድ እያደረጉ ይገኛሉ።
ከአንድ ወር ገደማ በፊት አሜሪካ የኒውክለር ኃይል የታጠቀ አውሮፕላን መሸከም የሚችል አውሮፕላን በኮሪያ ባሕረ ሰላጤ አሰማርታ፤ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የባሕር ላይ የጦር ልምምድ አድርጋ ነበር።
አሜሪካ ይህን ግዙፍ መርከብ ለጦር ልምምድ ማሰማራቷ ለሰሜን ኮሪያ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ተደርጎ የተወሰደ ሲሆን፤ ሶል በበኩሏ በአይነቱ ልዩ የሆነው ልምምድ “ለየትኛውም ዓይነት የሰሜን ኮሪያ ግጭት ቀስቃሽ ተግባራት ጠንካራ ምላሽ የሚሰጥ የደቡብ ኮሪያ እና የአሜሪካን ጠንካራ ወዳጅነት መሳያ ነው” ብላለች።
ፒዮንግያንግ ከወር በፊት ሚሳኤል አስወንጭፋ፤ የሚሳኤል የተኮስኩት በደቡብ ኮሪያ ላይ የሚፈጸም የኒውክሌር ጥቃት ልምምድ ነው ብላ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ በዚያ ልምምዷ የደቡብ ኮሪያ አየር ኃይል ጣቢያዎች፣ ወደቦች እና አየር ማረፊያዎች ተመስለው የቀረቡ ዒላማዎችን በተሳካ ሁኔታ መምታቷን እና ለልምምድ የተጠቀመችው ሚሳኤል የኒውክሌር አረረ መሸከም የሚችል መሆኑን ጨምራ ገልጻ ነበር።
ሰሜን ኮሪያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሙከራ የምትተኩሳቸው ሚሳኤሎች ቁጥር የጨመረ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ብቻ 40 ተኩሳለች። ይህም እስካሁን በአንድ ዓመት ከተመዘገቡት ከፍተኛው ነው።
ፒዮንግያንግ ጠንካራ ማዕቀቦች ሥር ብትገኝም ከእአአ 2006 እስከ 2017 ድረስ ስድስት የኒውክለር ሙከራዎችን አከናውናለች።