አሜሪካ የደቡብ አፍሪካው ንግግር አንዱ ዓላማ የኤርትራን ጦር ከኢትዮጵያ ማስወጣት ነው አለች

አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች በደቡብ አፍሪካ እያደረጉት ያሉት ውይይት አንዱ ዓላማ የኤርትራን ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ ማስወጣት ነው አለች።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት ሰኞ ጥቅምት 21/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ላይ የርስ በርስ ጦርነቱ ተፋላሚዎች የሚካሂዱት ንግግር አራት ጉዳዮችን ለማሳካት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ የውይይቱ አላማዎች ናቸው ብለው የጠቀሷቸው፤ በአስቸኳይ ግጭት ማቆም፣ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን በሙሉ ማቅረብ፣ የሰላማዊ ዜጎችን ደኅንነት ለማረጋገጥ ተጨማሪ እርምጃዎችን መውሰድ እና የኤርትራን ጦር ከሰሜን ኢትዮጵያ ማስወጣት ነው ብለዋል።

ሲጠበቅ የቆየው የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች የዛሬ ሳምንት ጥቅምት 15 የጀመሩት የሰላም ንግግር እስከ ነገ ረቡዕ ጥቅምት 23/2015 ዓ.ም. ቀጥሎ እንደሚካሄድ ምንጮች ለቢቢሲ መግለጻቸው ይታወሳል።

ምንም እንኳ ሁለቱ ተዋጊ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በንግግር ለመፍታት በዝግ ስብሰባቸውን እያደረጉ ይገኛሉ። እስካሁን የድርድሩ አጀንዳዎችም ሆነ የሰላም ንግግሩ ሂደት የደረሰበት ደረጃ በይፋ ምን እንደሆነ አይታወቅም።

ቃል አቀባዩ ግን በደቡብ አፍሪካ እየተደረገ ያለው ንግግር በአራቱ ግቦች ላይ ልዩነቶችን ለማጥባብ እንደሚረዳ ተናግረዋል።

ኔድ ፕራይስ በመግለጫቸው ላይ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በደቡብ አፍሪካው ንግግር ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ገልጸዋል።

አሜሪካንን ጨምሮ የተባበሩት መንግሥታት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) የታዛቢነት ሚና ኖሯቸው በደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር ላይ እየተሳተፉ መሆናቸውን የአፍሪካ ኅብረት መግለጹ ይታወሳል።

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር በደቡብ አፍሪካ እየተካሄደ ባለው ውይይት ‘ተሳታፊ እና ታዛቢ’ ሆነው ይቀጥላሉ ያሉት ኔድ ፕራይስ፤ ይህ ንግግር ሁለቱ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን ለማጥበብ እና አራቱ ግቦች ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲያመጡ ዕድል ይሰጣቸዋል ብላ አሜሪካ ተስፋ እንደምታደርግ ተናግረዋል።

የውይይቱ መራዘም ምክንያት

በደቡብ አፍሪካ ማክሰኞ ጥቅምት 15/2015 ዓ.ም. የጀመረው የሰላም ንግግር ከትናንት በስቲያ እሁድ ጥቅምት 20/2015 ዓ.ም. ይጠናቀቀል ተብሎ የተጠበቀ ቢሆንም፣ ውይይቱ በታቀደለት ጊዜ ባለማብቃቱ ለተጨማሪ ቀናት እንደሚቀጥል መገለጹ ይታወሳል።

ውይይቱ በታቀደለት ጊዜ አለመጠናቀቁ የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች “የተራራቀ” አቋም ይዘው ወደ ደቡብ አፍሪካ ማምራታቸውን የሚጠቁም ነው ሲሉ ኔድ ፕራይስ ተናግረዋል።

የውይይቱ መራዘም “[ሁለቱ] ተወያይ አካላት በመካከላቸው የተራራቀ አቋም ይዘው ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸውን ያመላክታል” ያሉት ኔድ ፕራይስ፤ የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ውይይታቸውን መቀጠላቸው ደግሞ “ለመነጋገር ያላቸውን ፍላጎት ያሳያል” ብለዋል።

“ተቀምጦ ለመወያየት ፈቃደኛ ሆነው መቀጠላቸውንም ልዩነታቸውን የሚነጋገሩበት እና በመካከላቸው ያለውን ርቀት ለማጥበብ የሚነጋገሩበት ይሆናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን” ሲሉ ኔድ ፕራይስ ትናንት ሰኞ ጥቅምት 21/2015 ዓ.ም. ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ያገረሸውን ጦርነት ተከትሎ አሜሪካ ተኩስ አቁም እንዲደረግና ንግግር እንዲካሄድ ስትወተውት ቆይታለች።

ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ ሦስት የተለያዩ ልዩ መልዕክተኞችን ለአፍሪካ ቀንድ በመሰየም ሰላም እንዲወርድ ጥረት ስታደርግ የቆየችው አሜሪካ፣ ተገቢ ያልሆ ጫና በመንግሥት ላይ እያሳረፈች ነው በሚል ስትተች ቆይታለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ስም ሳይጠቅሱ ለቻይና ዓለም አቀፍ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት፣ በድርድሩ ሂደት ከተለያዩ ወገኖች ጣልቃ ገብነቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ችግራቸውን በራሳቸው መፍታት ይችላሉ በማለት ለሰላም ተስፋ መኖሩን ገልጸዋል።

በመጪው ሐሙስ ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም. ሁለት ዓመት የሚሆነው ደም አፋሳሹን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት አማካይነት ሲደረግ የቆየው ጥረት ተኩስ በማቆም ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።