ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለኢትዮጵያ የተጫነውን እህል ጨምሮ 12 መርከቦች ከዩክሬን ወደብ ተነሱ
ሩሲያ ከሰሞኑ በጥቁር ባህር ወደቦች ላይ ጥቃት ደርሷል በሚል እህል ከዩክሬን ለማስወጣት ከተደረገው ዓለም አቀፍ ስምምነት ራሷን ብታገልም ዩክሬን እህል የጫኑ መርከቦች ከወደቦቿ መነሳቱን አስታወቀች።
ዩክሬን 12 እህል የጫኑ መርከቦች ትናንት ሰኞ ወደቦቿን ለቀው መውጣቱን ገልጻ፣ ከዚህም ውስጥ አንዱ መርከብ ለኢትዮጵያ የተላከ እህል ጭነት የያዘ ነው።
አንድ ከፍተኛ የዩክሬን ባለስልጣን እንደገለጹት 40 ሺህ ቶን እህል የጫነ መርከብ በኢትዮጵያ ረሃብን እየተጋፈጡ ላሉ ነዋሪዎች የሚዳረስ ነው።
“በኢትዮጵያ በርካቶች የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል” ብለዋል።
ከዚህ ቀደምም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካኝነት ለኢትዮጵያ ከዩክሬን የተገዛው እህል ባለፈው ዓመት መጨረሻ ጳጉሜ 2፣ 2014 ወደ አገሪቱ መግባታቸው ይታወቃል።
ይህ የእርዳታ ስንዴ ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አፍሪካ የተላከ እህል መሆኑም በወቅቱ ተገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያን የእርዳታ ስንዴ ጭና ጂቡቲ የደረሰችው ይህች መርከብ የሊባኖስ ባንዲራ ያላትና ብሬቭ ኮማንደር የምትሰኝ ሲሆን፣ 23 ሺህ ቶን ስንዴ ጭናም ነበር።
ኢትዮጵያ የደረሰው የስንዴ አቅርቦት ከአንድ ሚሊዮን ተኩል በላይ በችግር ላይ ያሉ ሰዎችን ለአንድ ወር ለመመገብ የሚረዳ መሆኑን የአለም ምግብ ፕሮግራም ለቢቢሲ ተናግሯል።
ከሰሞኑም ሩሲያ እህል በጥቁር ባህር በኩል ደኅንነቱ በተጠበቀ መተላለፊያ እንዲተላለፍ ከተፈራረመችው ዓለም አቀፍ ስምምነት ራሷን ማግለሏን ተከትሎ ዩክሬን እርምጃውን አውግዛለች።
“ሩሲያ ዓለምን በረሃብ እያስፈራራች ነው” ስትልም ወርፋለች።
ሩሲያ ይህ ዓለም አቀፍ ስምምነት ለመቋረጡ ምክንያት ያለችው ባሳለፍነው ቅዳሜ ዩክሬን መጠነ ሰፊ የድሮን ጥቃት በጥቁር ባሕር መርከቦች ላይ አድርሳለች በሚል ነው።
ይህ ጥቃት የደረሰው በሴባስፖል ክሬሚያ መሆኑም ተነግሯል።
ጥቃቱ ደረሰ ከተባለበት ከሰዓታት በኋላ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ “ሩሲያ በጥቁር ባሕር ለሚመላለሱ የጭነት መርከቦች ደኅንነት ዋስትና ልትሰጥ አትችልም ስለዚህም ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆም ተላልፏል” ብሏል።
ትናንት ሰኞ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ሩሲያ ከስምምነቱ ሙሉ በሙሉ እንዳልወጣችና መቋረጡን ብቻ ገልጸዋል።
ዩክሬን በበኩሏ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን ያልተቀበለች ሲሆን ሩሲያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተደረሰው ስምምነት ለመውጣት ጥቃቱን እንደ ሽፋን እየተጠቀመችበት ነው ብለዋል።
ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ የባህር ኃይሏ ከጥቁር ባህር ወደቦች በኩል እህል እንዳይወጣ እግድ ጥሎ ነበር።
በዚህም 20 ሚሊዮን ቶን የሚጠጋ ወደ ውጭ የሚላክ እህል እንዲሁም ምግብና ዘይት መውጫ አጥቶም ነበር። ሩሲያ ከወራት በኋላም በወደቦቹ ላይ ጥላው የነበረውን እገዳ አንስታለች።
የዩክሬን የመሠረተ ልማት ሚኒስትር ኦሌክሳንደር ኩብራኮቭ 12 እህል የጫኑ መርከቦች የዩክሬንን ወደቦች ሰኞ እለት ለቀው መውጣታቸውን በትዊተር ገጻቸው አስፍረዋል።
የፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃለ አቀባይ ዩክሬን እህል መላኳን መቀጠሏ በጣም አደገኛ ነው ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ቃል አቀባይ ዩክሬን እህልን ወደ ውጭ መላክ እንድትቀጥል በጣም አደገኛ መሆኑን አስጠንቅቀዋል።
“በእነዚህ አካባቢዎች ሩሲያ የነዚህን የመርከብ ደህንነቶች ማረጋገጥ የማይቻል መሆኑን ስትናገር ስምምነቱ ፈጽሞ ተፈጻሚ የማይሆን ደረጃ ላይ መድረሱን ነው። በአሁኑ ወቅት በነዚህ ወደቦች እህል መላክ የበለጠ አደገኛ ነው፤ ዋስትናም መስጠት የማይቻልበት ነው” ብለዋል ዲሚትሪ ፔስኮቭ
የሩሲያ ከስምምነቱ መውጣት በአሜሪካ የተወገዘ ሲሆን ሞስኮ “ምግብን መሳሪያ እያደረገችው ነው” ስትልም ወቅሳታለች።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፕ ቦሬል በበኩላቸው ሩሲያ ውሳኔዋን እንድትቀይር አሳስበው፣ እህልና ማዳበሪያን ወደ ውጭ መላክ አደጋ ላይ መሆኑ በዓለም የምግብ ቀውስ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል ብለዋል።
ሩሲያ እና ዩክሬን ከተባበሩት መንግሥታት እና ቱርክ ጋር በጥቁር ባሕር ደኅንነቱ የተጠበቀ መተላለፊያ (ኮሪደር) ለመክፈት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
የስምምነቱ ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ነበሩ?
- ከኦዴሳ እና ሁለት አጎራባች ወደቦች ወደ ኢስታንቡል የባሕር ዳርቻ መተላለፊያ (ኮሪደር) 310 ማይል የባሕር ርዝመት (357 ማይል) እና ሦስት የባሕር ማይል ስፋት ያለው
- መሣሪያ በተጠመደባቸው የወደብ ውሃ ውስጥ የዩክሬን መርከቦች ወደ ውጭ የሚገቡ እና የሚወጡ የእህል ጭነት መርከቦችን እንዲያጅቡ
- ጭነቶች በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሩሲያ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምታለች
- የሩሲያ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ስጋት ለማስወገድ ቱርክ መርከቦችን እንድትመረምር
- ሩሲያ በጥቁር ባሕር በኩል እህል እና ማዳበሪያ ወደ ውጭ መላክ ተፈቅዶላታል
- ስምምነቱ ከ120 ቀናት በኋላ ማለትም በኅዳር አጋማሽ ያበቃል